Sunday, March 16, 2014

ጊዜ ወርቅ ነው።

                                                  ጊዜ ወርቅ ነው ።
        ድሮ ድሮ አገር ቤት አዲስ አበባ አንዳንድ ትላልቅ ሰዎች ቤት ስትገቡ በትልቅ መስተዋት ፍሬም በጥሩ የእጅ ሥራ ዙሪያውን ጽጌረዳ አበባ ተለጥፎበት ከበሩ ፊት ለፊት በግርግዳ ላይ ተሰቅሎ ይታይ ነበር ። በአሁኑ ጊዜ ይኑር አይኑር አላውቅም ። ከንጉሡ መንግሥት በኋላ ያለ አይመስለኝም ። ምክንያቱም ያ ቃል ከንጉሡ ንግግር የወጣ ጥቅስ ነው ይባል ነበር ። ያንን ቃል እንደዚያ አሳምሮ የሰቀለው ሰው በጊዜ ወርቅነት  ይጠቀምበት አይጠቀምበት ባላውቅም ነገር ግን በዘመኑ የሂሳብ ስሌት ለመስታወቱና ለጥቅሱ ብዙ ገንዘብ የወጣበት ይመስለኛል ። ጊዜን ዛሬ ለጽሁፌ ስለምጠቀምበት አነሳሁት ። ጊዜ ምንድነው ? ጊዜ የሚለውን ፊደል ስናየውና ቃሉን ስናነበው ለዓይናችንና ለምላሳችን በጣም ቀላል ነው ። ግን በተግባር ስናየው ከወርቅና ከአልማዝ የሚከብድ አቅም አለው ፤ ወርቅና አልማዝ በገንዘብ እንገዛቸዋለን ፣ ጊዜን ግን ዋጋ ብንከፍልም ልንገዛው አንችልም ። ስለጊዜ በእግዚኣብሔር ቃል በብዙ ሥፍራ ተጠቅሶ ይገኛል ። በኦሪት ዘፍጥረት 1፥5 እግዚኣብሔር ብርሃንን ቀን ብሎ ጠራው ፤ ጨለማውንም ሌሊት ብሎ ሰየመው ። ቀኑ መሸ ሌሊቱም ነጋ ይህም አንድ ቀን ሆነ ይላል። እግዚኣብሔር በመጀመሪያ በመፍጠር ፤ ለፈጠረው ጨለማና ብርሃን ፣ ቀንና ሌሊት በማለት የጊዜ ገደብ አደረገላቸው ። ጨለማው አይሎ ብርሃኑን እንዳይውጠው በተነፃፃሪው ብርሃኑ አይሎ ጨለማውን እንዳያስቀረው ለፈጠረው ነገር ቀንና ሌሊት በማለት እየተፈራረቁ እንዲኖሩ ጊዜን ወሰነላቸው ። እግዚኣብሔር የፈጠረውን የጊዜ ገደብ በመጠቀም ፤ እግዚኣብሔር አንድ ቀን ያለውን ባቢሎናውያን እኩል ለሶስት ከፍለው ለቀንና ሌሊት ጊዜ አድርገውለት ይጠቀሙበት ነበር ። ግብፃውያን ደግሞ በበኩላቸው ከፀሐይ መውጫ  እስከ ፀሐይ መጥለቂያ ሰዓት፤ ለአስራ ሁለት እኩል ከፍለውት ጊዜን ሲጠቀሙበት በመቆየታቸው ለአሁኑ የምንጠቀምበት የጊዜ አቆጣጠር አስተዋጽዖ አድርገዋል ። ኅብራውያን ደግሞ በባቢሎን በምርኮ በነበሩበት ጊዜ የጊዜን አቆጣጠር ከባቢሎናውያን በመማር የራሳቸውን ቀመር አውጥተው ፤ ጊዜን ይለኩት የነበረው በሰዓት ፤ በቀን ፤ በሳምንት ፤በወርና በዓመት ነበር ። ዛሬም ዓለማችን በጊዜ ላይ ሴኮንድና ደቂቃ ጨምሮበት ጊዜን እንደሚገባ ይጠቀምበታል ። በጊዜ ቀልድ የለም ጊዜ ወርቅ ነው ። ንጉስ ሰሎሞን በመክብብ መጽሐፍ ምዕራፍ 3 ፥ 1 ለሁሉም ነገር ዘመን አለው ፤ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው…. ይላል ። ንጉሥ ሰሎሞን ለሁሉም ጊዜ አለው ሲል ሁሉም በጊዜ ምዕዋር ላይ ይሽከረከራል ማለቱ ነው ። ማንም ከጊዜ ውጭ ሊሆን አይችልም ፤ ወደደንም ጠላን ተቀበልንም አልተቀበልንም ለምናደርገውና በሕይወታችን ሊሆን የሚሆነው ነገር ሁሉ የሚፈጸመው በጊዜ ነው ። ዓለም ሥራውን የሚሰራው በጊዜ ነው ። እግዚኣብሔር የፈጠረለትን ጊዜ እንዳያመልጠው ፤ ጊዜን እንደሚገባው ከመጠቀሙ የተነሳ ጊዜ እንዳያመልጠው ከጊዜ ቀድሞ ለመሄድ ይሞክራል ። ጊዜን የሚጀምሩት ከሴኮንድ ነው ስለዚህ ለሰው ልጅ ሴኮንድ ዋጋ አላት ። ዓለም በብዙ የሚጠቀምበት ኮምፒውተር እንኳን ስራውን የሚሰራው በጊዜና በሰዓት ነው ። ከተመደበለት ሴኮንድና ደቂቃ ወጭ እንዲሰራ ብናዘው አይሰራም ። ለኮምፒውተሩ ጊዜ ያበጀለት ሰው ነው ። እግዚኣብሔር ሰውን ሲፈጥርው በጊዜና በሰዓት ገምቶ እንዲኖር ነው ። በዓለማችን ያደጉ አገሮችና አዳጊ አገሮች የሚባሉ አሉ ፤ ያደጉ አገሮች ተብለው የሚጠሩት ለምንድነው ? ምክንያቱም እነዚያ አገሮች ያደጉት ሕዝቡና መንግሥታቸው ጊዜን እንደሚገባው ስለሚጠቀሙበት ነው ። በአደጉ አገሮች ማንኛውም ተግባሮች የሚተገብሩት በጊዜ በተከፋፈለ ሁኔታ ነው ። ሴኮንድ አትዛነፍም ለጊዜ ክብርን ይሰጣሉ ፤ ስለዚህም በሁሉም አቅጣጫ አድገዋል ። ታዳጊ ወይም ድሃ አገሮች የሚባሉት ለምን ድሃ በመሆን ያዘግማሉ ? የተለያየ ነጥቦች ቢኖርም ዋናው ነጥብ በጊዜና በስራ አምነው ተቀብለው ተግባራዊ ስላላደረጉ ብቻ ነው ። ለምን ጊዜን እንሰርቃለን ? ምክንያታችንስ ምንድነው? ጊዜን በመስረቃችን የሚጎዳው ማነው ? ሁልጊዜም የሚገርመኝ አጋጣሚ አለኝ ፤ ወደ ካናዳ እንደመጣሁኝ ከጥቂት ወራት በኋላ ታመምኩኝና የቤተስብ ሐኪሜ ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ሆስፒታል አስተላለፈኝ ፤ የምጠራበትን ጊዜ ስጠባበቅ ቆይቼ አንድ ቀን በአድራሻዬ በዚህ ቀንና ሰዓት እንድትገኝ የሚል ደብዳቤ ደረስኝ ፤ በቀጠሮው ዕለት ከሥራ ቀርቼ ወደ ሆስፒታል ለመሄድ አለቃዬን አስፈቀድኩኝ ፤ የቀጠሮ ሰዓት ከመድረሱ በፊት ወደ ሆስፒታል ጉዞዬን ጀመርኩኝ ፤ ወደ ሆስፒታል አካባቢ ስደርስ ወረፋ ሊኖር ስለሚችል ትንሽ ነገር ቀመስመስ ላድርግ ብዬ ወደ አንደኛው ካፍቴሪያ ጎራ አልኩኝ ፤ ከልቤ ጋር ደግሞ ተጠርቼ የመጣሁት በደብዳቤ ስለሆነ አስር ደቂቃ ቢያልፍም ወረፋም ስለሚኖር የእኔ ተራ እስኪደርስ ድረስ ምንም አይደለም ብዬ በእኔ ግምትና ሃሳብ ቆየውኝ ። ከሻይ ቤት ወጥቼ የቀጠሮ ቦታውን ፈልጌ እስከማገኝ፤ ቦታው ስደርስ ሃያ ደቂቃ አልፎአል ። በሥፍራው ተራ የሚጠብቅ ሰው የለም በጣም ጭር ብሎአል ፤ የሚገባም ሆነ የሚወጣ የለም ፤ በሩን አንኳኩቼ እንዳልገባ በሩ ተዘግቶአል ። ከጥቂት ሴኮንድ በኋላ የሕክምና ልብስ የለበሰች ከውስጥ ብቅ አለች ፤ የእኔ እህት ቀጠሮ ነበረኝ አልኳት ወረቀቱን ተቀብላኝ የቀጠሮውን ሰዓት ተመለከተች እንደገና በእጇ ላይ ያለውን ሰዓት ተመለከተች የቀጠሮ ሰዓት ማለፉን ነገረችኝ ፤ በተጎለዳደፈ እንግሊዘኛም ምክንያቴን ብናገርም በተባለው ሰዓት ስላልተገኘህ ሌላ ቀጠሮ እንሰጥሃለን ብላ ወደውስጥ ገብታ ሌላ የቀጠሮ ወረቀት ይዛ መጣች፤ የቀጠሮውን ወረቀት ስትሰጠኝ በሚቀጥለው ቀጠሮ ቀደም ብለህ እንድትገኝ በቀጠሮው ዕለት ካልመጣህ እንዳልፈለግክ ተቆጥሮ ፋይሉ ወደ መዝገብ ቤት ይመለሳል አለችኝ ፡ ተመልከቱ ቀጠሮዬን በማስተጓጎሌ ማን ተጎዳ ? በብዙ የተጎዳሁት እኔ ነኝ የሆስፒታሉንም ስራ አዛንፌአለሁ ፤ ሥራዬን ፈትቻለሁ ፤ ሕክምና አላገኘሁም ፤ ገንዘብ አጥቻልሁ ፤ ገንዘብ ከስሬአልሁ ፤ የዚያን ዕለት ቀጠሮ ማስተጓጎሌ ለእኔ ትምህርት ሆኖኛል ። ከዚያ በኋላ ግን የትም ቦታ ቢሆን ከቀጠሮዬ አስቀድሜ መድረስ እንዳለብኝ ተረድቻለሁ ። በጊዜ አለመጠቀም ብዙ ጎጂ ጎን አሉት ። ታማኝነት እናጣለን ፤ ተደማጭነት አይኖረንም ፤ እኛ ለጊዜ ክብር እንደማንሰጥ ለእኛ ክብር የሚሰጠን የለም ። አብክረን ልናስበው የሚገባው ነገር ቢኖር የሌላውን ወገን ጊዜ ብቻ ሳይሆን የእኛንም ጊዜ ማጥፋታችንን መረዳት አለብን ፤ በሌላ አቅጣጫ ስንመለከት በማንኛውም የአበሻ ቤተ ክርስቲያን ስብሰባው የሚጀመረው በዚህ ሰዓት ነው ተብሎ በየሳምንቱ ስብሰባ የሚጀመርበትን ሰዓት በተደጋጋሚ ይነገራል ፤ ስለስብሰባ ፕሮግራም ያልተነገረበት ዕለት ያለ አይመስለኝም ። ለምሳሌ ስብሰባው የሚጀመረው ሶስት ሰዓት ነው ፤ በሰዓቱ ተገኙ ይባላል ። ብዙዎቻችን የስብሰባው ፕሮግራም የሚጀመረው በአራት ሰዓት ነው የተባለ ይመስል ከቤታችን የምንወጣው በሶስት ሰዓት ተኩል ነው ። የመጣው ሕዝብ ጥቂት ስለሆነ አገልጋዮች ደግሞ ብዙ ሰው ስላልመጣ እስኪመጣ በማለት ስብሰባውን ወደኋላ ይጎቱታል በዚህ ምክንያት ሁሉም ፕሮግራሞች ይዛነፋሉ ። ለምሳሌ ከአምስት ዓመት በፊት ወደ አንድ የካናዳውያን ቤተክርስቲያን እሄድ ነበር ። ታዲያ ያ ቤተክርስቲያን በየሰንበቱ ሁለት ፕሮግራሞች አሉት ፤ ፕሮግራሞቹ በጊዜ የተገደቡ ናቸው ። የመዝሙሩ ፤ በመካከሉ ያለው አገልግሎትና ስብከቱ (ትምህርት) በተመሳሳይ ጊዜ የሚያልቁ ናቸው ። በሰዓቱ ሁሉም ነገር ይፈጸማል ፤ አንዱ ከአንዱ አይምታታም ። አገልጋይም ሆነ ተገልጋዩ ሕዝብ የጊዜን ጥቅም ተረድቶ በጊዜው ይጠቀማል አገልጋዮች ሰዓታቸውን ነው የሚያዩት ፤ ሰዓታቸው ሲደርስ አገልግሎታቸውን ይጀምራሉ ፤ ሰዓታቸው ሲደርስ ጨርሰው  ለሚቀጥለው አገልግሎትና አገልጋይ ያስረክባሉ ።  ይህ ጊዜ የጌታ ነውና በምንም ዓይነት ማንም አገልጋይም ሆነ ተገልጋዩ ሕዝብ ጊዜውን አይሰርቅም፤ጊዜውን አክብሮ ይገለገላል ። እኛስ ? ልናስብበት የሚገባ ጉዳይ ይመስለኛል ። በስብሰባ ፤ በቀጠሮ …  ምክንያት ብዙ ፕሮግራሞች ይዛነፋሉ እንመልከት አንዳንዶቻችን ከቤታችን የምንነሳበት ሰዓት ወደ ፀሎት ቤት ፤ ወደ ፕሮግራም የምንሄድ አይመስልም ፤ ከቤታችን ስንነሳ ከተነገርው የፕሮግራም ሰዓት በጣም አርፍደን ነው ። ዘግይተን በመምጣታችን ፕሮግራሙ ዘግይቶ ይጀመራል ፤ ፕሮግራም ሲዘገይ መዘምራን ሳምንት ያጠኑትን ሕዝቡን ሲያስመልኩበት ጊዜው ይሄዳል ፤ ሰባኪውም የተረከበው አርፍዶ ስለሆነ እርሱም ያዘጋጀሁትን መልእክት ልጨርስ ሲል ጊዜው ያልፋል ። ሁላችንም በጊዜአችን አልተጠቀምንም ። እንዴት ነው ተብሎ ሲጠየቅ የሀበሻ ነገር ነው ይባላል ። ሀበሻ ከዘር ማንዘሩ የወረሰው ይመስል ተረቱ ሁሉ የሀበሻ ነገር ነው ። እኛ ደግሞ ከዝባዝንኬ ወጥተን በክርስቶስ የምናምን ክርስቲያኖች ነን ፤ እንደ ክርስቲያንነታችን ታማኝና ቀጠሮ የምናከብር መሆን አለብን ፤ ጊዜያችንን እኛ ካላከበርን ማን ያከብርልናል ። ንጉስ ሰሎሞን ለሁሉም ጊዜ አለው ብሎናል ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ጌታ ኢየሱስ ስለጊዜ እንደሚገባው በምሳሌዎቹ ሁሉ አስተምሮናል ።ጌታ ኢየሱስ ስለአስር ቆንጃጅት ሲናገር ፤ አምስት ብልህና አምስት ሰነፍ ቆንጃጅት የሙሽራውን መምጣት መብራታቸውን አብርተው ይጠብቁ እንደነበር ይገልጽልናል ። ብልህ ቆንጃጅት በትጋት የቀጠሮ ጊዜውን ሲጠብቁ ፤ ሰነፎች ቆንጃጂት ግን ቀጠሮአቸውን በመዘንጋት ማንቀላፋት ጀመሩ ። ሙሽራው በመጣ ጊዜ ግን ወደ ተጠሩበት እድሞ መግባት ሲገባቸው ዘይት ለመግዛት ወደ ከተማ ሄዱ ። ሙሽራው  በሰዓቱ የመጡትን እንግዶች ካስገባ በኋላ በሩን ዘጋው ። ጊዜውን አሳልፈው የመጡት ግን ሊገቡ አልተፈቀደላቸውም ። ዛሬ በሰዓት ምክንያት የሚቆጣጠረን ባይኖርም ከሁሉም በላይ የሕሊና ወቀሳ እንዳይደርስብን ልንጠነቀቅና ጊዜን መጠበቅ ባህላችን አድርገን ልንወስድ ይገባል ። አንድ ጊዜ  ብዙ ሕዝብ የተጋበዘበት ስብሰባ ተጠርቼ ነበር ። ወደ ስብሰባው አዳራሽ ስደርስ የመጡት ሰዎች በጣም ጥቂት ናቸው ። ሰብሳቢዎችም አልተገኙም ። ስብሰባው ሲዘገይ አጠገቤ ከሚገኘው ሰው ጋር ጨዋታ ጀመርን ፤ የስብሰባው ያለመጀመር የገረመው ሰው ሰዓት ስንት ነው አለኝ ? ሰዓቱን ነገርኩት ፤ ከተነገረው ጊዜ ሩብ ሰዓት ያለፈ ይመስለኛል አለኝ ፤ በተቀጠረበት ሰዓት አይደለም የሚጀመረው ፤ እንደአበሻ አቆጣጠር ከአንድ ሰዓት በኋላ ቢጀመር መልካም ነው አልኩት ፤ አንዱም ሰዓት አለፈ ግን አልተጀመረም ። በጊዜ ያለመጀመር ምክንያት የተገረመው የስብሰባ ጎረቤቴ እንደዚህ ብሎ አጫወተኝ ፤ ወደዚህ ከተማ ከመምጣቴ በፊት የምኖረው ቶሮንቶ ከተማ ነበር ። በዚያ ከተማ ዶከተር ማክቪት የሚባሉ የቤተ ክርስቲያን  እረኛ አሉ ። በከተማው የሚኖሩ ሀበሻ ክርስቲያኖች በቤተክርስቲያናቸው እንዲገለገሉ ቢጠይቋቸው ፤ እናንተ ታድጋላችሁ በማለት አምልኮ እንዲያመልኩበት ፈቀዱላቸው ። ታዲያ ከመግባባታቸው የተነሳ ለስብሰባም ሆነ ለአንዳንድ ጉዳይ ሲቀጥሩቸው  ሃያ ደቂቃ ፤ ግማሽ ሰዓት ወዘተ ……  ኢትዮጵያውያኑ እያረፈዱ ዘግየተው ይመጡ ጀመር ። ዶክተር ማኪቪትም  ምነው ወዳጄ አረፈድክ ብለው ሲጠይቁት ፤ ምክንያት እየፈጠረ ያልፋል ። ዶክተር ማክቪቲ የሚቀጥሩአቸው በሙሉ አንዳቸውም  በተቀጠሩበት ሰዓት የሚመጡ አይደሉም ። በቀጠሮ ሰዓት የማይመጡት ደግሞ ጥሩ ጥሩ ሰዓት ያላቸው ሰዎች ናቸው ። ዶክተር ማክቪት ነገሩ ሰልቸት ሲላቸው እንደዚህ በማለት ( የሀበሻ ሕዝብ ጊዜ የሚቆጥርበት ሰዓት አለው ፤ ግን ጊዜን አይጠቀምበትም ) ተናገሩ ብሎ አጫወተኝ ። መቼም ጊዜን የመጠበቅ ነገር ልናስበውና ልንጠነቀቅበት የሚገባ ጉዳይ ነውና ማሰተዋል ያለብን ጉዳይ ጊዜን ስንሰርቅ ከዕድሜያችን ላይ እንደምንሰርቅ አውቀን ፤ ጊዜን የመጠበቅና ቀጠሮን የማክበር ባህላችን ለማድረግ መለማመድ ይገባናል ። ለዚሁም የሰራዊት ጌታ እግዚኣብሔር ይርዳን ። 
                                                                     በቸር ይግጠመን!!!  
                                                                     ኃይሉ ነኝ!!




ኃይሉ ገቢ
403 402 4669


No comments:

Post a Comment