Sunday, March 16, 2014

እግዚኣብሔር ይጠብቃል

                                 እግዚኣብሔር ይጠብቃል
                                 “የእርሱ ታማኝነት እንደጋሻ ወይም እንደ ከተማ ቅጽር ይሆናል” መዝሙር 91፡4
ስለጋሻ የከሰቴ ብርሃን ተሰማ መዝገበ ቃላት እንዲህ ይላል “ ከጎሽ ቆዳ ወይም ከጉማሬ ቆዳ ተሽጉዶ አርበኛው በጦር እንዳይወጋ መመከቻ ይለዋል ።ጋሻ ከጥንካሬ የተነሳ ምንም ነገር አይበሳውም ጀግናው በጦር ሜዳ ላይ ከጠላት የተወረወረ ጦር መክቶ የሚመልሰው በጋሻው ነው። ጋሻ ብልት የሆኑ አካባቢዎችን ጦሩ እንዳይጎዳው ያደርጋል። የእግዚኣብሔር ታማኝነት እንደጋሻ ነው ። ይጠብቃል ፤ይከላከላል ፤ ነፃም ያወጣል  
ሥልጣኔ ከተስፋፋበት ዘመን ጀምሮ አንዳንድ አገሮች ከጠላት ወረራ አገራቸውን ወይም ከተማቸውን ለመከላከል በዘመኑ ጠንካራ በሆኑ ቁሳቁሶች ማለትም ድንጋይና ጡብ ዙሪያውን ወይም ከድንበር እስከ ድንበር ግንብ ይገነቡ ነበር። የመጣው የጠላት ኃይል የሰራዊቱን የመሳሪያ ብዛትና ኃይል የመጣበትን አቅጣጫ ለማወቅ በግንቡ ጫፍ ላይ ማማ( የመጠበቂያ ግንብ) ዙሪያውን እንደመስኮት ያደረጉለት ነበር። ያ ማማ ደግሞ ለሁለት ነገር ይጠቀም ነበር። ለመከላከልና ለመዋጋት ።ለእኛ መከላከያችን በምን የተመሰረተ ነው?እግዚኣብሔር እንደቃሉ ታማኝ ነው።እግዚኣብሔር ይከላከላል ፤ ይጠብቃል። ድሮ ድሮ በልጅነታችን ጊዜ ግሪን ፕራይመርና ሬድ ፕራይመር የሚባሉ የእንግሊዘኛ መማሪያ መጻሕፍት ነበሩ።እነዚያ መጻሕፍት አዲስ በሚገዛበት ጊዜ በውስጡ እንደምርቃት ትራክት (pamphlet) ይገኝ ነበር ።ከነዚያ ትራክቶች ምንጊዜም የማልረሳው (ዶሮና ጫጩቶችዋ) የሚባለው ነበር። ያ ታሪክ የተጻፈው በግጥም ይሁን በስድ ንባብ ትዝ አይለኝም ምክንያቱም ጊዜው በጣም ረዘም ያለ ስልሆነ ነው ። ታሪኩ ግን እንደዚህ ነው። በአንድ መንደር ውስጥ ዶሮ ከነጫጩቶችዋ ትኖር ነበር። በአንድ በጋ ወራት የተለያየ ነገሮችን እየለቃቀመች ሳታስበው ከመንደር ወጥታ ከመንደሩ አጠገብ ወደአለው ዱር ገባች ። ዶሮዋ ከነጫጩቶችዋ ስታንሳ ፤ስትጥል፤ስትለቃቅም  ወደ ጫካው መካከል ዘልቃ ገባች ።በቁጥቋጦው መካከል ሳለች ድንገተኛ የሰደድ እሳት ተነሳ፤ ሰደድ እሳቱ አውሎ ንፋስ ስለነበረው ፤ዶሮና ጫጩቶችዋ መንቀሳቀስ አልቻሉም ። ስለዚህ ከሰደድ እሳቱ እሷንና ልጆችዋን ለማዳን በክንፏ ስር አድርጋ ጭንቅላትዋን ቀበረች ። ሰደድ እሳቱ ሲያልፍ እርሷ በሰደዱ እሳት ምክንያት ስትሞት ልጆችዋ በሕይወት ተረፉ። በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 15፡13 (ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም) የእግዚኣብሔር ታማኝነት እንደዚህ ነው ። እኛ በኃጢያታችን ምክንያት እንዳንጠፋ ጌታ ኢየሱስ ራሱ ሞቶ እኛን ከሞት አዳነን የሰው ልጅ መሞት የለበትም አለ ስለዚህ ከጠላታችን ጋር ፍልሚያ ገጥሞ ወገኖቼ አይጠፉም ብሎ መከላከያ ጋሻ ሆነና በቅጽሩ ውስጥ ያሉትን ከምርኮ አዳናቸው። ሲድራቅ ፤ ሚሳቅና አብድናጎ ናቡከደነፆር ላሰራው ምስል ስገዱ ባትሰግዱ ግን ወደእሳት ተጥላላችሁ ትሞታላችሁ ብሎ ተነገራቸው ። እኛ አንተ ላቆምከው ምስል አንሰግድም። ከዚህ ከሚነደው እሳት እግዚኣብሔር ያድነናል ባያድነን እንኳን ለዚህ አምላኬ ነው ብለህ ላቆምከው ጣዖት አንሰግድም በማለት ውሳኔያቸውን ነገሩት። ሰባት ጊዜ ከነደደው እሳት ውስጥ ቢጣሉም ግንብ አጥር ሆኖአቸው ዶሮዋ ጫጩቶችዋን እንዳዳነቻቸው እግዚኣብሔር ከለላ ሆኖ አዳናቸው። በዘመናችንስ? እግዚኣብሔር ታማኝ ነው ምንጊዜም ታማኝ ነው። በእርሱ ለታመኑት ታማኝ ነው ። የፌስ ቡክ ገጼን ሳገለባብጥ አንድ ጓደኛዬ ሼር ያደረገውን ፎተግራፍ አየሁኝ ። ባለፎተግራፉ መካከለኛ ዕድሜ ያለ ሰው ነው ። ምን ዓይነት አደጋ እንደደረሰበት አይገልጽም ግን አንገቱ የመሰበር አደጋ ስለደረሰበት (cervical Collar) በሚባለው ፋሻ ተጠግኖአል ከፎተግራፍ ስር እግዚኣብሔር ከሞት ስላዳነኝ ሊመሰገን ይገባዋል ይላል ።ምናልባት ይህ ሰው ከመኪና አደጋ ብዙዎቹ ሞተው እርሱ በትንሽ አደጋ እግዚኣብሔር አድኖት ይሆናል እግዚኣብሔርን ሊያመሰግን የተነሳው ። ታሪክ ቢፈተሽ ቁጥር ስፍር የሌላቸው በተለያየ አደጋ ምክንያት ሆስፒታል ገብተው አይድንም አትድንም እየተባሉ በዶክተሮች ውሳኔ ተሰጥቶባቸው ነገር ግን ወደ እግዚኣብሔር በቀረበ የምዕመን ጸሎት ምክንያት እግዚኣብሔር የዶክተሮችን ውሳኔ ሽሮ ከሞት ነፃ ወጥተው፤አዲስ ፍጥረት ሆነው  እግዚኣብሔርን ሲያመሰግኑ፤ ለእርሱ ለአምላካችን ሲያሸበሽቡለት  ብዙዎችን አይተናል ። እግዚኣብሔር ታማኝ ነው ። እግዚኣብሔር ታማኝ የሚሆነው እኛ ስንታመን ብቻ ነው ።እኛ ስንታመን እግዚኣብሔር ይጠብቀናል። በተደረገልን ሁሉ ታምነናል?
                                                      በቸር ይግጠመን!!
                                                       ኃይሉ ነኝ!          


No comments:

Post a Comment