Sunday, March 16, 2014

የጀርባው ነገር

   የጀርባው ነገር
አውቀዋለሁኝ እሱም ያውቀኛል
አስተዳደጌን ማን ይነግረዋል
ከተራ ሥፍራ ከታች ጀምሬ
አስተዳደጌን  ምን ዓይነት ፍሬ
በሥራ ውጤት በምድሬቱ ዛሬ
ነግሬዋለሁ በጥብቅ አብክሬ
በእርከን ቢበልጠኝ ያዘና ወንበር
ሆንኩበት ለእሱ ፋርጣ ባላገር
ቋንቋው ልዩ ነው ጉራማሌኛ
ይመስላል እሱ የሆነ ሕልመኛ
ያጣጣል  ዘይቤ ያነጋገሩ
ስላልተራዳው የውን የምሩ
ግራ መሆኑን ስለተረዳሁት
ቀኝ መሆኔን እኔም ነገርኩት
ቀኝ ሲነሳበት ተቃወሰበት
ቁርጡን በመንገር በማስፈራራት
በእኔ ጎዳና በእኔ አቅጣጫ
መሄድ አለብህ ቢሆን በሩጫ
ለዚህ ትህዛዙ መልሴን ሰጠሁት
ስለዓላማዬ በግልጽ ነገርኩት
በማረጋገጥ ማንነቴን ሲያውቅ
ይናገር ጀመር እኔን በመናቅ
ወዳጅ ዘመዱን በጎኑ ላሉት
ይናገር ጀመር እንዲህ በማለት
ቀኝ ቀኝ በማለት ስላስቸገረኝ
ፈራሁት ጓዴን ከየት እንደሚገኝ
የጀርባው ነገር አከራካሪ
ውስጠ ወይራ በጣም አስፈሪ
ይሻላል ለእኛ ጀርባውን ብናየው
ስልጣን ከያዘ በጣም ችግር ነው
ሰበሰበና ወዳጅ ዘመዱን
ይመክር ጀመር የተቻለውን
የጀርባው ነገር ይጠና ያለኝ
ጀርባዬን አይቶ ሊሳፈርብኝ
ታርጋ ለጣፊ ታክሲ አደረገኝ
የጀርባው ነገር ይጠና ያለኝ
የተገጠበች አህያ አደረገኝ
ወይስ ለሸክም እኔን ፈለገኝ
አጋሰስ መጫኛ በቅሎ አደረገኝ
ለሽምጥ የሚመች ወይ ሰጋር ፈረስ
ሲጋልቡበት የልብ የሚያደርስ
ወደ ጦር ሜዳ ሊፈናጠጥብኝ
በትክሻዬ ላይ እሱ ድል ሊያገኝ
ፍልጎ ይሆን ጀርባህን ያለኝ

    ኃይሉ ገቢ Feb 2008 

No comments:

Post a Comment