የመስቀል ሥራ
ዓለም በቃኝ ፤ ዓለም ገና ወይም ዓለም ፀሐይ በተለያየ ስም የሚጠራው እስር ቤት ያሰሩት ንግስት ናቸው
። ዓለም በቃኝ ስምንት ጎንዮሽ ወይም ከርቭ አለው ። ንግሥት ይህንን እስር ቤት ሲያሰሩት ምን አስበው እንዳሠሩት አላውቅም ።
ነገር ግን ከውስጥ በኩል ሆነው ሲያዩት የዘውድ ቅርጽ አለው ። ምናልባት በእስር ቤቱም ላይ ንግሥትነታቸውን ለማረጋገጥ ይሆን ለማንኛውም
እኔም እንደአንዱ እስረኛ አባል ከሆንኩኝ ዘመን አለፈኝ።
በየዕለቱ እንደሚደረገው ዓይነት ስብሰባ ሳይሆን በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚደረገውን ፕሮግራም ከሳምንት በፊት በማስታወቂያ
ቦርድ ላይ ተለጥፎ ነበር ። የጌታችንና የመድሀኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል ስለምናከብር በስፍራው እንዲገኙና የእግዚኣብሔርን
ቃል እንዲያዳምጡ ተጋብዘዋል ። ፕሮግራሙ በምሽት ከቆጠራ በኋላ ነው
ይላል።ሁልጊዜም እንደማደርገው ቃሉን ለመስማት ቆጠራ አልቆአል የሚለውን የጭብጨባ ድምፅ እስከምሰማ ሰዓቱ እስኪደርስ ድረስ በጉጉት
እየጠበቅኩኝ ነኝ ፤ ልክ እንደተጨበጨበ ከክፍሌ አጠገብ በሚገኘው ጎንዮሽ በታጣፊ ወንበር ላይ ቁጭ ብያለው ። የጉባኤው አባላት
ከየክፍላቸው እስኪሰበሰቡ ድረስ የፕሮግራሙን መጀመር ናፍቅሁ።
የጉባኤው አባላት እንደተሰበሰቡ ጉባኤውን የሚመራው ሰው “ እንደምታውቁት ዛሬ የጌታችንና የመድሀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ
የትንሳኤ በዓል ስለሆነ በመጀመሪያ “እዩት ኢየሱስን” የሚለውን መዝሙር እንዘምራለን አላቸው። መዝሙሩን ከመዘመራቸው በፊት ግጥሙን
የፕሮግራሙ መሪ በንባብ ይወጣው ጀመር። በቁም ንባብ አንብቦት እንደጨረሰ ጉባኤው መዝሙሩን መዘመር ቀጠለ “ እዩት ኢየሱስን መስቀሉ
ማማሩ ለተመራመረው ብዙ ነው ሚስጢሩ” ደጋግመው ሲዘምሩት በሃሳብ ማዕበል ከሁለት ሺህ ዓመት በፊት ስለተደረገው የመስቀል የድህንነት
ሥራ ወደተሰራበት ሥፍራ ወሰደኝ ። ሥጋዬ እዚያው እስር ቤት ውስጥ ነው ሀሳቤ ግን እንደወፍ በረሮ ኢየሩሳሌም ከግርግሩ መካከል
አስገባኝ ጉዞው ከሊቀ ካህናቱ ቀያፋ ግቢ ወደ ገዡው ጲላጦስ አደባባይ ነው ።እኔም እግሬ እንዳመጣልኝ ሰዎች ወደሚሄዱበት አቅጣጫ
ሄድኩኝ ጫጫታ ኡካታ አለ አንዳንዱ ይጮሃል አንዳንዱ አዝኖ አንገቱን አቀርቅሮ መንገዱን ወደፊት እየተጓዘ ነው እኔም ዝም ብዬ ከሚጮሁት
ጋር እየጮኹኝ ጉዞዬን ቀጠልኩኝ ። አንገቴን ቀና አድርጌ ሳማትር ከመንገዱ ወጣ ብሎ የሚጓዘውን አንድ ሰው አይቼ እኔም ከሰልፉ
ገንጠል ብዬ ወጥቼ ካየሁት ሰው ጋር ጉዞ ጀመርኩኝ ፤ ወንድም የዚህ ግርግር ምክንያት ምንድንነው? ብዬ ጠየቅሁት ። ወደግርግሩ
እያየ “በኢየሩሳሌም እየኖርክ ስለግርግሩ የምትጠይቀኝ አልሰማህምና ነው የምትጠይቀኝ” አለኝ ። “ አፌ እንዳመጣልኝ እንደሱ አይደለም
እኔ አሁን ከባላገር ከጌተሰማኔ ነው የመጣሁት አልኩት” ወንድሜ የአይሁድ
ንጉሥ ነኝ ባይ ለፍርድ ስለሚቀርብ የሕዝቡ ግርግር በዚህ ምክንያት ነው አለኝ ። እኔም የዚህን ግርግር መጨረሻ ማየት አለብኝ ብዬ
ጉዞዬን ቀጠልኩኝ፤ቀድሞ የደረሰው ሕዝብ ስቀለው!! ስቀለው!!ረጅም እንደቃለ አጋኖ የሚያንጸብርቅ ጩኸት ይጮሃል ጩኽቱ የተደጋገመ
የማያቋርጥ የአድማ የሚመስል ነገር ነው ።ወደ አደባባዩ ስደርስ አንድ የተጎሳቀለ ሰው በመካከል ላይ አቁመውት ይታያል አይናገርም
መልስ አይሰጥም አንገቱን እንደደፋ ቆሞአል። የተሰበሰበው ሕዝብ ግን ይሰቀል!! ይሰቀል!! ይላል በቄሳር ዙፋን ላይ የተቀመጠው
ጲላጦስ “እንግዲያው የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን እንዳደርገው ትፈልጋላችሁ? ስቀለው እያሉ አብዝተው በጣም ጮኹ ። ጲላጦስም
እኔ ከዚህ ሰው ደም ንፁሕ ነኝ ፤ ከእንግዲህ ኃላፊነቱ የራሳችሁ ነው በማለት በሕዝቡ ሁሉ ፊት እጆቹን ታጥቦ አሳልፎ ሰጣቸው።
ትልቅ መስቀል አሸክመውት ወደጎልጎታ ወሰዱት ፤ ያንን ትልቅ መስቀል አሸክመው እየገፈታተሩት ሲያስጨንቁት አንዳችም አልተናገረም
። ከመስቀሉ ጋር ያንን የቀራኒዮን ተራራ ለመውጣት ሲያስቸግሩትና ሲገርፉት የተናገረው ቃል አልነበረም። ጎልጎታ አናቱ ላይ ሲደርስ
በመስቀሉ ላይ ሲያጋድሙትና በትላልቅ ሚስማሮች እግሩንና እጆቹን ሲቸነክሩት እየተሰቃየ ዝም አለ ።በጦር ጎኑን ሲወጉት ጸጥ አለ
።አንዳችም ቃል የተናገረው ነገር አልነበረም ። ሰዓቱ ሲደርስ ግን “ አምላኬ! አምላኬ! ለምን ተውኸኝ!! ብሎ ሲጮኽ ። በምድር
ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ መሬት ተንቀጠቀጠች ነፍሱን ሰጥቶ ጸጥ አለ ። በእውነት የእግዚኣብሔር ልጅ ነበር ብሎ አጠገቤ የነበረው ወታደር
ሲናገር ፤ ጌታ ኢየሱስ ሆይ! ኃጢያተኛ ነኝ ይቅር በለኝ!! ብዬ በኃይል ስጮኽ የጌታ ኢየሱስን የትንሳኤ በዓል ሊያከብር የተሰበሰበው
ጉባኤ ከጩኽቴ በኋላ ጭብጨባውን ሲያቅልጠው ከነበርኩበት ዓለም መለሰኝ ። በመስቀል ሥራ እኔን በፍጹም ለውጦኝ እስከዛሬ በእውነተኛ
መለወጥ ከእርሱ ጋር እኖራለሁ!!እናንተስ የመስቀሉን ፍቅር ቀምሳችሁታል? ። ወደጌታ በእውነት ቅረቡ እውነተኛውን የመስቀሉን ፍቅር
ትቀምሳላችሁ!!!
በቸር ይግጠመን!!
ኃይሉ
ነኝ
No comments:
Post a Comment