Sunday, March 16, 2014

አዋጅ ለባለጆሮዋ ቤተ ክርስቲያን

                                        አዋጅ ለባለጆሮዋ ቤተ ክርስቲያን
         በቅርብ ለዘመን መለወጫ አንድ ቀን ሲቀረው ከፌስ ቡክ ጓደኞቼ በአሜሪካ ሲልቨር ስፕሪንግ ማሪላንድ ከምትኖር እህቴ አዋጅ ለባለጆሮዋ ቤተክርስቲያን በሚል ርዕስ ኤሜል ደረሰኝ በቀጥታ ለእኔ የተፃፈ ስለነበረ አነበብኩት፤ ደግሜ አነበብኩት ለሶስተኛ ጊዜ ካነበብኩት በኋላ ይህንን አዋጅ ሌላውም ሊያነበው ይገባል ብዬ አንዳንድ ሃሳቦችን ጨምሬ ጻፍኩት። ሙሉ ለሙሉ ሃሳቡ የእህቴ ነው።
      ( ንቂ ንቂ ዲቦራ ንቂ ንቂ  ቅኔም ተቀኜ ) መሳፍንት 5፡12
 ንቂ ፥ንቃ ፥ ንቁ ፥ መንቃት የሚለውን ግስ ስንመለከት የከሰቴ ብርሃን ተሰማ መዝገበ ቃላት እንዲህ ይላል ዕውቀትን ለመሰብሰብ አህምሮውን የሰነገለ ፣ የወለወለ ሲለው ። የነቃ ፥ በዕውቀት የተባ ፥ ጥበብን ለመስማት የልቡናውን ጆሮ ቀቅሮ የሚያዳምጥ ይለዋል።
ሳባ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ ነቃ ተቀሰቀሰ፣ ተጠነቀቀ፣ ተጋ ይላል።
   ዲቦራና ባራቅ በዘመሩት መዝሙር ላይ የእግዚኣብሔር ሕዝብ ከከተሞቻቸው ተሰልፈው ወረዱ ይላል። ወርደው አልቆሙም ከላይ “ ዲቦራ ሆይ! ንቂ! ተነሺ! መዝሙር እየዘመርሽ ወደፊት ቀድመሽ ምሪ” ብለው ዘመሩ በነገራችን ላይ ዲቦራ የዕብሩ ትርጉም ንብ ማለት ነው ታዲያ የሕዝቡን መዝሙር ሰማች መጽሐፉን ስናነበው ምን ያህል የእግዚኣብሔርን ስራ እንደሰራች ታሪኳን ስናነብው ይገልጸዋል ። በዚህ ላይ የተጠቀሰው ጥቅስ ለእሷ የእግዚኣብሔርን ስራ ለመስራት ዋና መስረት ነው የሆናት ።  መንቃት በቀጥታ ከመጠቀም ጋር የተያያዘ ነው ። መጠቀም የሚቻለው ከሙሉ መንቃት ጋር ነው ።እንደ ዲቦራ።
     ግማሽ መንቃት ለተጠቃሚነት አያበቃም የከሰቴ ብርሃን መዝገበ ቃላት ዕውቀትን ለመሰብሰብ አህምሮውን የሰነገለ፥ ጥበብን ለመስማት የልቡናውን ጆሮ ቀቅሮ የሚያዳምጥ ይለዋል የተኛና በግማሽ መንቃት ለተጠቃሚነት አያበቃም የመኃልየን ቆንጅዬ ሴት “እኔ ተኝቻለሁ ልቤ ግን ነቅቶአል” አይደለም ያለችው። የመኃልዬ ቆንጆ ሙሉ ለሙሉ አለመንቃቷ ፍቅረኛዋን ልታገኝ ያለመቻሏን ትናገራለች። እግዚኣብሔር ለቤተ ክርስቲያን በሰጣት ትሩፋት ተጠቃሚ ለመሆን አንድ ነገር ግድ ይላታል ። መንቃት!! ለመንቃት ደግሞ ምን ያስፈልጋታል? ቤተ ክርስቲያን ለመንቃት ስነ-ጽሑፍ ያስፈልጋታል ምክንያቱም አንዱ የመንቂያ መንገድ ስነ-ጽሑፍ ነው። ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ለስነ-ጽሑፍ ግድ የለሽ ናት ። ስነ-ጽሑፍ ምኗም አይደለም ። ስነ-ጽሑፍ ለቤተ ክርስቲያን ቢኖርም ባይኖርም የማይጠቅምም የማይጎዳም ነው ። እንደ ምንም ነገር ነው። ስነ-ጽሑፍ ለእግዚኣብሔርም ለሰይጣንም ጠቃሚያቸው ነው ።
       እግዚኣብሔር ለሰው ልጅ ሶስት ታላላቅ ስጦታዎችን ሰጥቶአል። በምንም የማይተኩ ከምንም የማይወዳደሩ ልጁን፤ መንፈሱንና ቃሉ ናቸው ። ከእነዚህ ሶስቱ ደግሞ አንደኛው (ቃሉ) በመጽሐፍ ደረጃ በእያንዳንዱ ክርስቲያን እጅ ይገኛል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ያነባል ፤ ይማራል፤ያስተምረዋል፤ ያስነብበዋል፤ ያነበዋል፤ ያጠናዋል፤ ያስጠናዋል፤ ይሰብከዋል……..ይህ እጅግ ታላቅና ውድ ስጦታ ለሰው ልጆች ይደርስ ዘንድ እግዚኣብሔር የስነ-ጽሑፍ ችሎታውን በውስጣቸው ያሳደረባቸውን ሰዎች ተጠቅሞአል። ይህ ማለት ደግሞ እግዚኣብሔር ታላቅ ስጦታ የሆነውን ወደ ሕዝቡ ለማድረስ ስነ-ጽሑፍን ዋነኛ መሣሪያው አድርጎ ተጠቅሞአል ማለት ነው ። በድንቅ ድንቅ ስነ-ጽሑፍ የእግዚኣብሔር ታላቅ ሥራ የተገለጸው በስነ-ጽሑፍ ባለሙያዎች ነው ።
      በሌላ ጎኑ ደግሞ ሰይጣንም ታላላቅ የክህደት አስተምህሮችንም ያሰራጨው በስነ-ጽሑፍ አማካይነት ነው ።የስነ-ጽሑፍ ችሎታ ያላቸውን አድኖና አሳድዶ ተጠቅሞባቸዋል። በሃይማኖት ሽፋን ኢየሱስን “ሰው ብቻ” አድርገው በማስቀመጥ ቁጥር ስፍር የሌላቸውን ሰዎች ወደጥፋት የነዱ የስነ-ጽሑፍ ሰዎች ናቸው ። በቅርባችን ደግሞ ገድላትና ድርሳናትን በየስርቻውና በየቤታቸው በማዘጋጀት መጽሐፍ ቅዱስን ይዘው እንኳን ወደ ተረት እንዲሳቡ ለማድረግ የበቁት ሰይጣን የስነ-ጽሑፍ ሰዎችን በመጠቀም ነው ።
      ቤተ ክርስቲያንስ እንዴት ታድርግ? እግዚኣብሔር የስነ-ጽሑፍ ሰዎችን በስስት የሚያያቸው ለመሆናቸው ቅንጣት ያህል የምትጠራጠር አይመስልም !!ስለዚህ የስነ-ጽሑፍ አቅም ያላቸውን ልታበረታታቸው፤ አገልግሎቱን ልትደግፍና የእግዚኣብሔርን ሥራ እንዲሰራ ከጎን ልትቆም ይገባል ።

     ዲቦራዋ ቤተ ክርስቲያን ሆይ ንቂ!! እንቁዎችሽን አክብሪ ብዙ መስራትና መጥቀም ሲችሉ እንደ መኃልዬ ቆንጆ ባለመንቃት በችለተኛነት እንቁዎቻቸውን እንደታቀፉ አይጥፉብሽ አይሙቱብሽ። ቤተ ክርስቲያን ማለት ደግሞ እኔም ፤ አንቺም ፤ አንተም ፤ እሱም ፤ እሷም ፤ እነርሱም ፤ ሁላችንም ስለሆንን የእግዚኣብሔርን ሥራ ልንሰራ እንነሳ ቤተ ክርስቲያን ያለ ስነ-ጽሑፍ ግማሽ መንቃት ስለሆነ ነቅተን ለማንቃት እንድንችል አገልግሎቱን እንደግፍ    

No comments:

Post a Comment