Sunday, March 16, 2014

እኔም አልፈርድብሽም

                                          እኔም አልፈርድብሽም
      “እኔም አልፈርድብሽም” በሚለው ዓረፍተ ነገር ውስጥ አንድ ባለቤትና አንድ ማሰሪያ አንቀጽ ወይም ግስ አለው ። በሌላ አባባል ደግሞ ሁለት አካላት እንዳሉ የአማርኛችን የሰዋሰው አወቃቀር ይገልጸዋል። እኔም የሚለው ባለቤት ፈራጅና ምሕረት ሰጪና በሌላ ጎኑ የሚፈረድባት ወይም ምሕረት የተሰጣት በዚህ ዓረፍተ ነገር ውስጥ እናገኛለን ። ይህንን ርዕስ ያመጣሁት ቀጥታ ከዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 8 ሲሆን ፤ጌታ ኢየሱስ በማለዳ በጠዋት ሕዝቡ በዙሪያው ተሰብስበው ወንጌል እያስተማራቸው ነበር። ከሳሾች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን አንድ ስታመነዝር የተያዘችን ሴት ይዘው ፤ጌታ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር በመተባበር እንዲፈርድባት ወደእርሱ አመጡአት ። የሙሴ ሕግ አዋቂዎች “አባታችን ሙሴ በሰጠን ሕግ ላይ ማንም ሰው ሲያመነዝር የተያዘ በሞት ይቀጣ ” ብሎ አዞአል። እኛ ደግሞ የሕጉ ባለአደራዎች ስለሆንን ኃጢያት ሲሰራ ዝም ብለን ማየት ስለማንችል በሕጋችን መሰረት መገደል አለባት ።ሙሴ ያዘዘው ትህዛዝ ይህችን ሴት ለብቻዋ ጉዳዩ ይመልከታት አይመልከታት ሳይገናዝቡ ነበር ይዘዋት የመጡት፤ምክንያቱም ሕጉ በተለያየ ሁኔታ ስለሚገልጸው አንተስ ስለዚህች አመንዝራ ሴት ምን ትላለህ? ብለው ጌታ ኢየሱስን ጠየቁት። ጌታ ኢየሱስን ሊፈትኑት በሌላ ጎኑ ተባባሪ ሊያደርጉት እንዳሰቡ ተገንዝቦ ። የሰውን ልጅ ከሕግና ከኃጢያት ነፃ ለማውጣት ወደዚህ ምድር የመጣው ጌታ ኢየሱስ ጎንበስ ብሎ መፃፍ ጀመረ ። በቃ እሱም እንደኛ ጥቅሱን ጠቅሶ ሊፈርድባት ነው ብለው እርስ በእርሳቸው ሲጠቃቀሱ ፤ ጽሁፉን ጽፎ ጨርሶ ሲነሳ “ከእናንተ መካከል ኃጢያት የሌለበት በመጀመሪያ አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት” አላቸው ። የተጻፈውን ጽሑፍ ሲያነቡ ሐፍረታቸውን ተከናንበው አንድ በአንድ ቦታውን ለቀው መሄድ ጀመሩ። ጻድቅ ነን ብለው የሚኮፈሱት የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ድንጋዩን በመጀመሪያ ከማንሳት የተቆጠቡት ኃጢያት መስራታቸውን የራሳቸው ሕሊና ስለፈረደባቸው ነው።እኛስ በአንድ ቤተስብ ኑሮ ፤ትዳር  ፤አገልግሎት ላይ የመጀመሪያውን ድንጋይ አንስቶ ለመወረውር ቅዱስ ነን?     
      ባለፈው ዓመት ከሥራ ወደቤት ለመመለስ ዳውን ታውን (Down Town) ባቡር ስጠብቅ ፤ አንድ በቅርብ ሩቅ የማውቀው ባቡር ጣቢያ ተገናኝተን ሰላምታ ከተሰጣጣን በኋላ ፤ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን አላይህም ምነው አገልግሎትም ቀረ እንዴ? ብዬ ጠየቅሁት ። ጌታ ሲፈቅድ እጀምራለሁ አለኝ ። ምነው ብዬ አጥብቄ ብጠይቀው ሁኔታውን ገልጾ ነገረኝ ። ሁኔታውን ካዳመጥኩት በኋላ “ የእኔ ወንድም አንተ እንደነገርከኝ በተመሳሳይ ሁኔታ እኔም ችግር ደርሶብኝ ነበር ። ቅስሜ ተሰብሮ ሞራሌ ደቆ ሞት እስከሚያስመኘኝ ድረስ ተስፋ ቆርጪ ነበር ። የፈራጆችን ፍርድ ቁብ ሳልሰጣቸው ። በቤተ ክርስቲያን ተሳትፎና አገልግሎት ቀጠልኩኝ የጠላቴ ሽረባ እንዲወገድልኝ በጾምና በፀሎት ተጋሁኝ ያ እንደጉም ጨፍግጎ የያዘኝ ችግር ብንን አለ ይህው እንደምታየኝ ዛሬም በጌታ ቤት አለው ። ወንድሜ ሆይ! ጠላትን ማሸነፍ የምትችለው በእንደዚህ መንገድ ነው አልኩት ። በጉዳዩ ተስማምተን ሁለታችንም በየፊናችን ሄድን።  
      የእግዚኣብሔር ቃል “ ይቅር በሉ እናንተም ይቅርታን ታገኛላችሁ” ይላል ። ሁልጊዜም አንድ ሰው አጠፋ፤ ኃጢያተኛ ነው ፤ ወንጀለኛ ነው ፤ የውሸት ክርስቲያን ነው እያልን ለመፍረድ ይዳዳናል ያ ደግሞ ሚስጢር ነው ለማንም አትናገር በሚል የውሸት ካባ እንደ ሙሴ የሕግ ሰዎችና እንደፈሪሳውያን የምንፈርድባቸው ብዙዎች ነን እንደዚህ ከሆነ የክርስቶስ ተከታይነታችን በምን ይገለጻል ። እንዲያውም ያንን ሰው በጌታ ፍቅር መክሮና ወደንስሐ እንዲመጣ ማበረታታት እንጂ ጭራሹኑ ከጌታ ቤት እንዲወጣ መገፋፋት ተገቢ ነው?!! ያ ሰው ለእኔና ለአንተ ጌታ ኢየሱስ እንደሞተልን ለርሱም ሞቶለታል ። ጴጥሮስ ወደ ጌታ ኢየሱስ ቀርቦ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው ሰባት ጊዜ ነውን ብሎ ጴጥሮስ ለማረጋገጥ  ሲጠይቀው አይደለም አለ ጌታ ኢየሱስ ሰባት ጊዜ ሰባ ነው አለው እዚህ ላይ እንደምንመለከተው እንዲያውም የተበደልን ብንሆን እንኳን ሰባ ጊዜ ሰባ ይቅር በሉት ነው የሚለው ስለዚህ የጌታ ኢየሱስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን ጥፋት አጥፍተዋል የምንላቸውን ሰዎች ይቅርታ በማድረግ ልባቸውን ወደጌታ እንዲመለሱ ብናደርግ መዝገባችን በሰማይ ይጻፍልናል ። ጌታ ኢየሱስ እንዲሰቀል የሚፈልጉት የካህናት አለቆች ነበሩ ። ሌላው በቄሳራዊው ጴላጦስ አደባባይ ቆመው ስቀለው!! ስቀለው!! ብለው የሚጮሁት ግማሹ ከአምስት ሺ ተመጋቢዎች ውስጥ ነው፤ ሌላው ፈውስን ከጌታ ኢየሱስ የተቀበለ ነው ፤ ቢያንስ ቢያንስ ታአምራት ሲደረግ አይቶአል። የእነዚህን ስዎች ሁኔታ ስንመለከት በደፈናው የሚያደርጉትን የማያውቁ ብቻ ስቀለው ስቀለው የሚሉ ናቸው ። መሐል ሰፋሪ የሆኑት አንዳንዶቹ የመንደር ሰዎች ገፋፍተዋቸው የመጡ ናቸው ። አንዳንዱም እንደይሁዳ የመጮያ ገንዘብ ተከፍሎት ነው ። የውስጥ ሚስጥሩን አያውቁም ብቻ ስቀለው ስቀለው ይሉ ነበር። ኃጢያት የሰራውን ያንን ሰው ስቀለው ስቀለው እያልን ከጌታ ቤት ከምናስወጣው በፍቅር ተቀብለነው በኃጢያቱ ተናዞ በቤቱ እንዲኖር ብናደርገው የእግዚኣብሔር ቃል እንደሚናገረው ገንዘብ አደረግከው ስለሚል የእግዚኣብሔርን መንግስት ያሰፋን ይመስለኛል። ነገር ግን ምንም ምክንያት ሳይኖረን ስቀለው ስቀለው የምንል ከሆነ ለእኛም አስቸጋሪ ዘመን ሊመጣብን ይችላል ። ለማንኛውም በሰው ፊት እንደምንታየው ጻዴቅ መምሰል ሳይሆን ሕይወታችን፤ ኑሮአችን ፤ ስልካችንና አነጋገራችን የተቀደሰ ሊሆን ይገባል ። እንዳይፈረድባችሁ በማንም ላይ አትፍረዱ ብሎ ጌታ ኢየሱስ እንዳስተማረን ። በሁሉም ነገር ላይ ፈራጅ ሆነን ሳለ ድንገት ጌታ ኢየሱስ ቢመጣ የተመካንበት ጽድቃችን ከንቱ እንዳይሆን እንጠንቀቅ!!!
                                                                                           በቸር ይግጠመን!!
                                                                                               ኃይሉ ነኝ     

   

No comments:

Post a Comment