የመስቀል ወፍ
በአገራችን በምድራችን
በወንዛችን ተራራችን
ያኔ ሳንመጣ ካናዳ
እንደዛሬ ሳንሆን ባዳ
ለነገሩ ሳንሆን እንግዳ
በአበሾቹ ቀዬ መንደር
የምናስታውሰው ያለ የነበር
ዘመን አልፎ ሲመጣ ዘመን
ሁልጊዜም የሚታሰበን
በሕልማችን በሃሳባችን
በምናባችን የሚታየን
አሮጌው ዘመን አልፎ
አዲስ ዘመን አሸንፎ
ከዘመን ዘመን አልፈን
አዲስ ዓመት እውን ሲሆን
ሐምሌ ነሐሴ ክረምቱ
ሲያልፍ ጭጋግ ወራቱ
ያኔ በአገራችን በቀያችን
በገጠር ከተማ መንደራችን
በአንድነት ሆነው ሴቶቻችን
የኮባ ግልድም አገልድመው
ፀጉራቸውን ሳዱላ ተሰርተው
ቅቤ በአደስ ተቀብተው
ወርቀ ዘቦ ካባ ደርበው
ተመራርጠው በዕድሜያቸው
ጎራ ከፍለው እንደእኩያቸው
እርስ በእርሳቸው
ሴቱ በአንድነት ሆነው
ዘመን ሲለወጥ በዕለቱ
ሰው ከሰው ሳይገናኝ
በጠዋቱ
እማማና አባባ ሳይነሱ ከመኝታ
እንደተሰማ የወፍ ጫጫታ
ሳምንት ወር የተሟሸውን
በእሳት በቅቤ የቀለጠውን
ሴትዋ እየደለቀች ከበሮዋን
ለተቀባያዋ ስታቀነቅን ዜማዋን
ታቅፋው አደይ አበባዋን
ቄጠማ አክርማውን
እንኳን አደረሳችሁ ለማለት
ሲሽከረከሩ በየሰዉ ቤት
ያዜሙ ነበር እንደዚህ በማለት
አበባዮሽ ለምለም
በአባብዬ ቤት ለምለም
ቁሙ በተራ ለምለም
አበባ ለምለም ወሸባ ለምለም
እንደርስዎ ጌታ የለም
ከብረው ይቆዩ ከብረው
ለዓመት ወንድ ልጅ ወልደው
ሰላሳ ጥጃ አስረው
ከብረው ይቆዩ ከብረው
ይህንን ብለው አዜመው
የመልካም ምኞት ገልጸው
ምርቃት ለሕዝብ ሁሉ ሰጥተው
ወር ሳምንት ሳይሞላው
ክረምቱን መውጣቱን አስልታ
የአደይ አበባውን መፍካት አይታ
የደመራውን እሳት ተመልክታ
ውብ ዜማዋን እያዜመች
መምጣቷን እየተናገረች
ትመጣ ነበር የመስቀል ወፌ
እንድኖር ክረምት ወጣ ብዬ አርፌ
ዛሬ ዘመን ቢያልፍም
ክረምቱ ቢፈጸምም
ብሩህ ሰማይ ቢታይም
ፀሐይዋ እንኳንብትወጣም
ከዘመን ዘመን ብንሻገርም
ወፌን አላየዋትም
ወፌን አላያችሁም ወይ እንዳልል
ሁሉም ይናፍቃታል
ለራሱ ይመኛታል
መምጣቷን ይጠብቃል
ቢያያት ያከብራታል
ለሚስጢር ይፈልጋታል
በቤቱ ያስቀምጣታል
ወፌ የዘንባባ ዝንጣፌ አላት
ሰላምን የምታበስርበት
ፍቅርን የምትገልፅበት
ብትመጣ ጊዜዋን ጠብቃ
እንደዚህ እላታልሁ በቃ
እነሆ ክረምት አልፎአል
ዝናቡ ቆሞ በጋ መጥቶአል
በየመስኩ ኣዳይ አበባ አብቦአል
የአበባው ሽታ ምድርን ሞልቶአል
የአዝመራው ጊዜ ደርሶአል
የመስቀል ወፌ ከሄድሽበት
ርቀሽ ከኖርሽበት
ድምፅሽን ልስማው
ዜማሽን ላዳምጠው ስላት
ብትሰማኝ ብትመጣልኝ ልንገራት
ወፌ የመስቀል ወፍ
ኃይሉ ገቢ Jan 7/2007
No comments:
Post a Comment