ዜግነት
ገና በሕጻንነት ሳለሁ በት/ቤቴ
ፊደል አስቆጣሪዬ የት/ቤት አባቴ
የሕብረተሰቡ አካል እንዲሆን መሰረቴ
ፊደል አስቆጠረኝ እንዳውቅ ስለዜግነቴ
አስተማሪው ሲያስተምረኝ
እንደዚህ ብሎ አለኝ
ደሙን ያፈሰሰ ልቡ የነደደ
በአገር ፍቅር ስሜት ጠላት ያስወገደ
ጠላትህ መሀይምነት ነው
ሕዝቡ እንዳያውቅ ያደረገው
ባለጋራህ በሽታ ነው
ሕዝቡን በሞት የሚቀስፈው
አንተ ተምረህ ካስተማርከው
ዜግነት ማለት ያ ነው
ዜጋ ዜግነት የሚባለውን
የአገር መሰረት የሆነውን
እንደ ማህተሜ በጉያዬ
በደረቴ ላይ አንጠልጥዬ
አስተማሪው ባስተማረኝ
ዜግነትን ስለተረዳሁኝ
በስርዓቱ ስለሄድኩኝ
ሕዝቡን ስላስተማርኩኝ
አቅጣጫውን ስለነገርኩኝ
በሽታውን ታምሜ ቁስሉን ስለጠገንኩኝ
የሚራበውን ተርቤ ሕዝቡን ስላስተማርኩኝ
አንዱ መጥቶ ሲያስረኝ
ሌላው ደግሞ ሲፈታኝ
ዘመኔን አሳለፍኩኝ
ዜጋ እሱ ብቻ መሰለኝ
ዜግነት እንደሌለኝ ቆጠርኩኝ
ስለዚህ መናገር ካልቻልኩኝ
ሕዝቡን ካላስተማርኩኝ
የቁም እስረኛ ከሆንኩኝ
ዜግነትን ከተገፈፍኩኝ
አገሬን የማገለግልበት ሰዓት
እስኪ መጣ የምፈለግበት ዕለት
ለአገሬ አንድ ቀን ብቆይላት
ይህንን ከልቤ ጋር አስቤበት
ሄድኩኝ ወደ ባዕድ መሬት
የደረስኩበት ምድር
አሁን የምኖርበት አገር
እትብቴ የልተቀበረበት
ዘር ምንጅላቴ የልኖረበት
የዘር ዐረጌ የሌለበት
ሰጠኝ የመኖር ነፃነት
ስናፍቀው የነበረው ዜግነት
ተምሬ እንዳስተምር
ሰርቼ እንድከብር
ከአንዱ ቦታ ወደ አንዱ ለመዘዋወር
በነጻነት በሁሉም ቦታ እንድኖር
አለኝ ነጻነት የተሟላ
ሥራ ቢሆን ከለላ
ምን ያደርጋል !!!
ሁሉም ነገር ቢሟላልኝ
ተትረፍርፎ ሁሉን ባገኝ
የሰላም አየር ብተነፍስ
ሁሉም ቢቀየር እንደአዲስ
አገሬ ትናፍቀኛለች እትብቴ የተቀበረበት
አያት ቅድመ አያቴ የሞቱላት
እናትና አባቴ የኖሩበት
አፈር ፈጭቼ ያደግኩበት
በየኔታ ቤት የተማርኩት
ፊደል የቆጠርኩበት
አገሬ ትዝ ትለኛለች
የታሪክ ቁንጮ የሆነች
ወሎ ላሊበላ ጎንደር
አክሱም እንደዚሁም ሐረር
ሉሲ የተፈጠረችበት
የታሪክ ምዕራፍ የተገለጸበት
አባይ አዋሽ ያለበት
የተከዜ ፏፏቴ የሚፈስበት
ዘርዝሬ የማልገልጸው
አውርቼ የማልጠግበው
በየትም ቦታ የማላፍርባት
በአደባባይ የምናገርላት
ባንዲራዬን የማውለበልብላት
አሁንም እናፍቃታለሁ
ኢትዮጵያነት ለእኔ ዜግነት ነው
ኃይሉ ገቢ Oct 25/2007
No comments:
Post a Comment