ምክንያቴ ብዙ ነው
ዘርዝሬ ልገልጸው በአፌ ልናገረው
ምሥጋና አቅርቤ ፍጹም የማልችለው
እግዚኣብሔር አምላኬን የማመሰግነው
ምክንያቴ ብዙ ነው
ምክንያቴ ብዙ ነው ጌታን የማነግስበት
ለጌታ አምላኬ ክብር የምሰጥበት
በገናዬን ይዤ ቅኔ የምቀኝበት
በእጆቼ አጨብጭቤ ስለት የማገባበት
ምክንያቴ አይቆጠር ጌታን የማከብርበት
ጠላቴ ሊጥለኝ እንደአመድ ሊረግጠኝ
አለቀለት በቃ ልገድለው ነው ሲለኝ
ዕድሜውን ልቀጨው
ወደ ሞት ልወስደው
ይህንን ቃል ዝቶ ወጥመድ አዘጋጅቶ
ሕይወቴ ሊያጠፋ ጠላት ተዘጋጅቶ
ስላስበው ድንገት እኔን አዘናግቶ
መሣሪያ አበላሽቶ
ብሎኖቹን ፈትቶ
ሊገድለኝ ሲያደባ
ሊከተኝ ከጉድባ
የመሞቴን አዋጅ በጉራ ሲያውጅ
ጌታ ኢየሱሴ አወጣኝ ከሞት ደጅ
ከመሞት አድኖኝ በክብር ላቆመኝ
ለዚህ ድንቅ ጌታ ክብር እሰጣለሁኝ
ድምፄን ከፍ አድርጌ ላዚም ለጌታዬ
ልደርድረው እኔ ይናገር በገናዬ
ላደረገው ሁሉ ላቅርብ ምሥጋናዬ
ሌላ ምንም የለኝ ይህ ነው ችሎታዬ
ጠላቴ ዒላማው ሁለት እጆቼን ጎምዶ
በሚሆነው ነገር እኔኑን አናዶ
እጆቼ እንዳይጽፉ
ቃሉን እንዳያስፋፉ
የደካከሙት ተስፋ የቆረጡት
በሚጽፈው ቃላት እንዳይጽናኑበት
ነበረ ሃሳቡ የሰው ልጆች ጠላት
ጌታ አድኖኛል ከሞት አትርፎኛል
ምን ብዬ ልበለው ምሥጋና ያንሰኛል
መሰንቆዬን ልቀኝ እስቲ ዜማ ላውጣ
ከበሮው ይከበር ክብርን እንዲያመጣ
ላሸብሽብ ልጨፍር ላምላኬ ለጌታ
እሱን ካስደሰተው ለሰራው ውለታ
የጠላቴ ሃሳብ የእሱ ፍላጎቱ
በእኔ ሊፈጽመው ነበረው ምኞቱ
መጻፍ መናገሬን ይህንን ተመልክቶ
የእጆቼን ውጤት በክፉ ዓይኑ አይቶ
ሰዎች በመባረክ ስላገኙ ትምህርት
ጠላቴ እንዲህ አለ እጁን ብቆርጥለት
የአመልካች ፤ የአውራ ጣት ሁሉን ብጎምድለት
ከሥራ አስወጥቼ እንዳትጽፍ ባደርጋት
ሞራሉ እንዲነካ ችግር ብፈጥርበት
ፋይሉ ይዘጋል
ነገሩ ይቆማል
ነበረ ምኞቱ
አልሆነም ድርጊቱ
ጠላቴ በእኔ ላይ ደግሞም በሰውነቴ
አንዳችም አልቻለም ሊያደርግ በሕይወቴ
ዛሬ ለጌታዬ እጆቼ ይጽፋሉ
በአደባባዩ ክብርን ይሰጣሉ
ያጨበጭባሉ ቅኔን ይቀኛሉ
ዛሬ የእኔ ጌታ ዕረፍትን ሰጥቶኛል
ምሥጋና ብሰጠው ለእርሱ ያንስበታል
አፌን እከፍታለሁ ቅኔን እቀኛለሁ
ማዕሌተ ቅኔን ለእርሱ አቀርባለሁ
እግዚኣብሔር ይመስገን ብዬ እናገራለሁ
ሌላ ምንም የለኝ ምሥጋናዬ ይኽው
ምክንያቴ ግን ብዙ ነው
በቸር ይግጠመን!!
ኃይሉ ነኝ!
Mar 31/2006
No comments:
Post a Comment