Sunday, March 16, 2014

እኔ ግን ሞቻለሁ!!

እኔ ግን ሞቻለሁ
ጌታ ደግነቱን ማዳን ታምራቱን
ፍቅሩን ርህራሄውን ለጋስ ቸርነቱን
አባቶች ነግረውኝ ለእኔ አስተምረውኝ
በመስቀል መሞቱን ይህን ገልጸውልኝ
አረጋግጠው መክረው ስላስጠነቀቁኝ
መንገዱን መርጪ ጌታን ተከተክልኩኝ
በእርግጥ እንደሞተልኝ እኔም ስለተረዳው
መሞትን ፈልጌ ከዓለም ተለየው
ወደመስቀሉ ስር በእምነት ሲያደርስኝ
ድሬቶ ቡትቶ ቀድሞ የነበረኝ
ከላዬ ተገፎ ገደል ውስጥ ገባልኝ
መሞት እንደሚገባኝ በመሞት ወሰንኩኝ
ምንም ስለሌለኝ ከዓለም የማተርፈው
ከጌታዬ ጋራ እኔ ግን ሞቻለሁ
          በቸር ይግጠመን!!
          ኃይሉ ነኝ


እግዚኣብሔር ይጠብቃል

                                 እግዚኣብሔር ይጠብቃል
                                 “የእርሱ ታማኝነት እንደጋሻ ወይም እንደ ከተማ ቅጽር ይሆናል” መዝሙር 91፡4
ስለጋሻ የከሰቴ ብርሃን ተሰማ መዝገበ ቃላት እንዲህ ይላል “ ከጎሽ ቆዳ ወይም ከጉማሬ ቆዳ ተሽጉዶ አርበኛው በጦር እንዳይወጋ መመከቻ ይለዋል ።ጋሻ ከጥንካሬ የተነሳ ምንም ነገር አይበሳውም ጀግናው በጦር ሜዳ ላይ ከጠላት የተወረወረ ጦር መክቶ የሚመልሰው በጋሻው ነው። ጋሻ ብልት የሆኑ አካባቢዎችን ጦሩ እንዳይጎዳው ያደርጋል። የእግዚኣብሔር ታማኝነት እንደጋሻ ነው ። ይጠብቃል ፤ይከላከላል ፤ ነፃም ያወጣል  
ሥልጣኔ ከተስፋፋበት ዘመን ጀምሮ አንዳንድ አገሮች ከጠላት ወረራ አገራቸውን ወይም ከተማቸውን ለመከላከል በዘመኑ ጠንካራ በሆኑ ቁሳቁሶች ማለትም ድንጋይና ጡብ ዙሪያውን ወይም ከድንበር እስከ ድንበር ግንብ ይገነቡ ነበር። የመጣው የጠላት ኃይል የሰራዊቱን የመሳሪያ ብዛትና ኃይል የመጣበትን አቅጣጫ ለማወቅ በግንቡ ጫፍ ላይ ማማ( የመጠበቂያ ግንብ) ዙሪያውን እንደመስኮት ያደረጉለት ነበር። ያ ማማ ደግሞ ለሁለት ነገር ይጠቀም ነበር። ለመከላከልና ለመዋጋት ።ለእኛ መከላከያችን በምን የተመሰረተ ነው?እግዚኣብሔር እንደቃሉ ታማኝ ነው።እግዚኣብሔር ይከላከላል ፤ ይጠብቃል። ድሮ ድሮ በልጅነታችን ጊዜ ግሪን ፕራይመርና ሬድ ፕራይመር የሚባሉ የእንግሊዘኛ መማሪያ መጻሕፍት ነበሩ።እነዚያ መጻሕፍት አዲስ በሚገዛበት ጊዜ በውስጡ እንደምርቃት ትራክት (pamphlet) ይገኝ ነበር ።ከነዚያ ትራክቶች ምንጊዜም የማልረሳው (ዶሮና ጫጩቶችዋ) የሚባለው ነበር። ያ ታሪክ የተጻፈው በግጥም ይሁን በስድ ንባብ ትዝ አይለኝም ምክንያቱም ጊዜው በጣም ረዘም ያለ ስልሆነ ነው ። ታሪኩ ግን እንደዚህ ነው። በአንድ መንደር ውስጥ ዶሮ ከነጫጩቶችዋ ትኖር ነበር። በአንድ በጋ ወራት የተለያየ ነገሮችን እየለቃቀመች ሳታስበው ከመንደር ወጥታ ከመንደሩ አጠገብ ወደአለው ዱር ገባች ። ዶሮዋ ከነጫጩቶችዋ ስታንሳ ፤ስትጥል፤ስትለቃቅም  ወደ ጫካው መካከል ዘልቃ ገባች ።በቁጥቋጦው መካከል ሳለች ድንገተኛ የሰደድ እሳት ተነሳ፤ ሰደድ እሳቱ አውሎ ንፋስ ስለነበረው ፤ዶሮና ጫጩቶችዋ መንቀሳቀስ አልቻሉም ። ስለዚህ ከሰደድ እሳቱ እሷንና ልጆችዋን ለማዳን በክንፏ ስር አድርጋ ጭንቅላትዋን ቀበረች ። ሰደድ እሳቱ ሲያልፍ እርሷ በሰደዱ እሳት ምክንያት ስትሞት ልጆችዋ በሕይወት ተረፉ። በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 15፡13 (ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም) የእግዚኣብሔር ታማኝነት እንደዚህ ነው ። እኛ በኃጢያታችን ምክንያት እንዳንጠፋ ጌታ ኢየሱስ ራሱ ሞቶ እኛን ከሞት አዳነን የሰው ልጅ መሞት የለበትም አለ ስለዚህ ከጠላታችን ጋር ፍልሚያ ገጥሞ ወገኖቼ አይጠፉም ብሎ መከላከያ ጋሻ ሆነና በቅጽሩ ውስጥ ያሉትን ከምርኮ አዳናቸው። ሲድራቅ ፤ ሚሳቅና አብድናጎ ናቡከደነፆር ላሰራው ምስል ስገዱ ባትሰግዱ ግን ወደእሳት ተጥላላችሁ ትሞታላችሁ ብሎ ተነገራቸው ። እኛ አንተ ላቆምከው ምስል አንሰግድም። ከዚህ ከሚነደው እሳት እግዚኣብሔር ያድነናል ባያድነን እንኳን ለዚህ አምላኬ ነው ብለህ ላቆምከው ጣዖት አንሰግድም በማለት ውሳኔያቸውን ነገሩት። ሰባት ጊዜ ከነደደው እሳት ውስጥ ቢጣሉም ግንብ አጥር ሆኖአቸው ዶሮዋ ጫጩቶችዋን እንዳዳነቻቸው እግዚኣብሔር ከለላ ሆኖ አዳናቸው። በዘመናችንስ? እግዚኣብሔር ታማኝ ነው ምንጊዜም ታማኝ ነው። በእርሱ ለታመኑት ታማኝ ነው ። የፌስ ቡክ ገጼን ሳገለባብጥ አንድ ጓደኛዬ ሼር ያደረገውን ፎተግራፍ አየሁኝ ። ባለፎተግራፉ መካከለኛ ዕድሜ ያለ ሰው ነው ። ምን ዓይነት አደጋ እንደደረሰበት አይገልጽም ግን አንገቱ የመሰበር አደጋ ስለደረሰበት (cervical Collar) በሚባለው ፋሻ ተጠግኖአል ከፎተግራፍ ስር እግዚኣብሔር ከሞት ስላዳነኝ ሊመሰገን ይገባዋል ይላል ።ምናልባት ይህ ሰው ከመኪና አደጋ ብዙዎቹ ሞተው እርሱ በትንሽ አደጋ እግዚኣብሔር አድኖት ይሆናል እግዚኣብሔርን ሊያመሰግን የተነሳው ። ታሪክ ቢፈተሽ ቁጥር ስፍር የሌላቸው በተለያየ አደጋ ምክንያት ሆስፒታል ገብተው አይድንም አትድንም እየተባሉ በዶክተሮች ውሳኔ ተሰጥቶባቸው ነገር ግን ወደ እግዚኣብሔር በቀረበ የምዕመን ጸሎት ምክንያት እግዚኣብሔር የዶክተሮችን ውሳኔ ሽሮ ከሞት ነፃ ወጥተው፤አዲስ ፍጥረት ሆነው  እግዚኣብሔርን ሲያመሰግኑ፤ ለእርሱ ለአምላካችን ሲያሸበሽቡለት  ብዙዎችን አይተናል ። እግዚኣብሔር ታማኝ ነው ። እግዚኣብሔር ታማኝ የሚሆነው እኛ ስንታመን ብቻ ነው ።እኛ ስንታመን እግዚኣብሔር ይጠብቀናል። በተደረገልን ሁሉ ታምነናል?
                                                      በቸር ይግጠመን!!
                                                       ኃይሉ ነኝ!          


ይሻለኛል!

ይሻለኛል!
ጌታ በማይፈቅደው መንገዱ ከሰፋው ፤
ሕይወት ከማይገኝበት ሞት ብቻ ከሆነው።
ሰላም ከሌለበት ፤ ከሌለበት ዕረፍት
ይሻለኛል እኔ የክርስትና ሕይወት
ከፍልስጤም ጎራ ጠላት ከበዛበት
ፀጉርን ከሚያስላጭ ከደሊላ ምቾት
ዓይንን ከሚያስወጣ ከፍልስጤም አገር
ይሻለኛል በክብር ከኢየሱስ ጋር መኖር።
ከጶጥፋራ ቤት ጮማ ከሞላበት
ሽንኩርትና በጥሁ የአትክልት ዓይነት
እነዚህን በሙሉ ለሰውነት ምቾት
ተትረፍርፎ ቢገኝ ኃጢያትን ለመስራት
ጌታን በማሳዘን ከመኖር በኃጢያት
ይሻለኛል እኔ ከጌታ ጋር ሕይወት
አልጋ ወራሽ ሆኜ በግብፅ ቤተ መንግሥት
ከፈርዖን ዙፋን ጌታ ባልነገሰበት
የፈርዖን ልጁ ወራሽ ነው ከምባል
ከጌታ ጋር ሆኖ መሰደድ ይሻላል
ኃጢያትና ርኩሰት ከሚደረግበት
ከጥፋት ከተማ ሞት ካንዣበበት
ከሶዶም ጎመራ ወርቅ አልማዝ ካለበት
ይሻለኛል ጌታ ትርፍ ባይኖርበት
ዓለም ከምትሰጠው ምቾትና ድሎት
ብዙ መቀማጠል ግን ባዶ ከሆነበት
ሁሉም ነገር ኖሮኝ ከጌታ ከምርቅ
ይሻለኛል ኢየሱስ በተስፋ መጠበቅ
ለሥጋ ከሚመች ካለበት ብዙ ሀብት
ራሴን ለውርደት ሕይወቴን ከመስጠት
በኃጢያት አረንቋ ራስን ከመክተት
ይሻላል ኢየሱስ ከዘለዓለም ሞት
  
            በቸር ይግጠመን!!
             ኃይሉ ነኝ   


የመስቀል ሥራ

                                                                                                                                                                                  የመስቀል ሥራ
                 ዓለም በቃኝ ፤ ዓለም ገና  ወይም ዓለም ፀሐይ በተለያየ ስም የሚጠራው እስር ቤት ያሰሩት ንግስት ናቸው ። ዓለም በቃኝ ስምንት ጎንዮሽ ወይም ከርቭ አለው ። ንግሥት ይህንን እስር ቤት ሲያሰሩት ምን አስበው እንዳሠሩት አላውቅም ። ነገር ግን ከውስጥ በኩል ሆነው ሲያዩት የዘውድ ቅርጽ አለው ። ምናልባት በእስር ቤቱም ላይ ንግሥትነታቸውን ለማረጋገጥ ይሆን ለማንኛውም እኔም እንደአንዱ እስረኛ አባል ከሆንኩኝ ዘመን አለፈኝ።   
       በየዕለቱ እንደሚደረገው ዓይነት ስብሰባ ሳይሆን በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚደረገውን ፕሮግራም ከሳምንት በፊት በማስታወቂያ ቦርድ ላይ ተለጥፎ ነበር ። የጌታችንና የመድሀኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል ስለምናከብር በስፍራው እንዲገኙና የእግዚኣብሔርን ቃል እንዲያዳምጡ ተጋብዘዋል  ። ፕሮግራሙ በምሽት ከቆጠራ በኋላ ነው ይላል።ሁልጊዜም እንደማደርገው ቃሉን ለመስማት ቆጠራ አልቆአል የሚለውን የጭብጨባ ድምፅ እስከምሰማ ሰዓቱ እስኪደርስ ድረስ በጉጉት እየጠበቅኩኝ ነኝ ፤ ልክ እንደተጨበጨበ ከክፍሌ አጠገብ በሚገኘው ጎንዮሽ በታጣፊ ወንበር ላይ ቁጭ ብያለው ። የጉባኤው አባላት ከየክፍላቸው እስኪሰበሰቡ ድረስ የፕሮግራሙን መጀመር ናፍቅሁ።
       የጉባኤው አባላት እንደተሰበሰቡ ጉባኤውን የሚመራው ሰው “ እንደምታውቁት ዛሬ የጌታችንና የመድሀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል ስለሆነ በመጀመሪያ “እዩት ኢየሱስን” የሚለውን መዝሙር እንዘምራለን አላቸው። መዝሙሩን ከመዘመራቸው በፊት ግጥሙን የፕሮግራሙ መሪ በንባብ ይወጣው ጀመር። በቁም ንባብ አንብቦት እንደጨረሰ ጉባኤው መዝሙሩን መዘመር ቀጠለ “ እዩት ኢየሱስን መስቀሉ ማማሩ ለተመራመረው ብዙ ነው ሚስጢሩ” ደጋግመው ሲዘምሩት በሃሳብ ማዕበል ከሁለት ሺህ ዓመት በፊት ስለተደረገው የመስቀል የድህንነት ሥራ ወደተሰራበት ሥፍራ ወሰደኝ ። ሥጋዬ እዚያው እስር ቤት ውስጥ ነው ሀሳቤ ግን እንደወፍ በረሮ ኢየሩሳሌም ከግርግሩ መካከል አስገባኝ ጉዞው ከሊቀ ካህናቱ ቀያፋ ግቢ ወደ ገዡው ጲላጦስ አደባባይ ነው ።እኔም እግሬ እንዳመጣልኝ ሰዎች ወደሚሄዱበት አቅጣጫ ሄድኩኝ ጫጫታ ኡካታ አለ አንዳንዱ ይጮሃል አንዳንዱ አዝኖ አንገቱን አቀርቅሮ መንገዱን ወደፊት እየተጓዘ ነው እኔም ዝም ብዬ ከሚጮሁት ጋር እየጮኹኝ ጉዞዬን ቀጠልኩኝ ። አንገቴን ቀና አድርጌ ሳማትር ከመንገዱ ወጣ ብሎ የሚጓዘውን አንድ ሰው አይቼ እኔም ከሰልፉ ገንጠል ብዬ ወጥቼ ካየሁት ሰው ጋር ጉዞ ጀመርኩኝ ፤ ወንድም የዚህ ግርግር ምክንያት ምንድንነው? ብዬ ጠየቅሁት ። ወደግርግሩ እያየ “በኢየሩሳሌም እየኖርክ ስለግርግሩ የምትጠይቀኝ አልሰማህምና ነው የምትጠይቀኝ” አለኝ ። “ አፌ እንዳመጣልኝ እንደሱ አይደለም እኔ  አሁን ከባላገር ከጌተሰማኔ ነው የመጣሁት አልኩት” ወንድሜ የአይሁድ ንጉሥ ነኝ ባይ ለፍርድ ስለሚቀርብ የሕዝቡ ግርግር በዚህ ምክንያት ነው አለኝ ። እኔም የዚህን ግርግር መጨረሻ ማየት አለብኝ ብዬ ጉዞዬን ቀጠልኩኝ፤ቀድሞ የደረሰው ሕዝብ ስቀለው!! ስቀለው!!ረጅም እንደቃለ አጋኖ የሚያንጸብርቅ ጩኸት ይጮሃል ጩኽቱ የተደጋገመ የማያቋርጥ የአድማ የሚመስል ነገር ነው ።ወደ አደባባዩ ስደርስ አንድ የተጎሳቀለ ሰው በመካከል ላይ አቁመውት ይታያል አይናገርም መልስ አይሰጥም አንገቱን እንደደፋ ቆሞአል። የተሰበሰበው ሕዝብ ግን ይሰቀል!! ይሰቀል!! ይላል በቄሳር ዙፋን ላይ የተቀመጠው ጲላጦስ “እንግዲያው የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን እንዳደርገው ትፈልጋላችሁ? ስቀለው እያሉ አብዝተው በጣም ጮኹ ። ጲላጦስም እኔ ከዚህ ሰው ደም ንፁሕ ነኝ ፤ ከእንግዲህ ኃላፊነቱ የራሳችሁ ነው በማለት በሕዝቡ ሁሉ ፊት እጆቹን ታጥቦ አሳልፎ ሰጣቸው። ትልቅ መስቀል አሸክመውት ወደጎልጎታ ወሰዱት ፤ ያንን ትልቅ መስቀል አሸክመው እየገፈታተሩት ሲያስጨንቁት አንዳችም አልተናገረም ። ከመስቀሉ ጋር ያንን የቀራኒዮን ተራራ ለመውጣት ሲያስቸግሩትና ሲገርፉት የተናገረው ቃል አልነበረም። ጎልጎታ አናቱ ላይ ሲደርስ በመስቀሉ ላይ ሲያጋድሙትና በትላልቅ ሚስማሮች እግሩንና እጆቹን ሲቸነክሩት እየተሰቃየ ዝም አለ ።በጦር ጎኑን ሲወጉት ጸጥ አለ ።አንዳችም ቃል የተናገረው ነገር አልነበረም ። ሰዓቱ ሲደርስ ግን “ አምላኬ! አምላኬ! ለምን ተውኸኝ!! ብሎ ሲጮኽ ። በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ መሬት ተንቀጠቀጠች ነፍሱን ሰጥቶ ጸጥ አለ ። በእውነት የእግዚኣብሔር ልጅ ነበር ብሎ አጠገቤ የነበረው ወታደር ሲናገር ፤ ጌታ ኢየሱስ ሆይ! ኃጢያተኛ ነኝ ይቅር በለኝ!! ብዬ በኃይል ስጮኽ የጌታ ኢየሱስን የትንሳኤ በዓል ሊያከብር የተሰበሰበው ጉባኤ ከጩኽቴ በኋላ ጭብጨባውን ሲያቅልጠው ከነበርኩበት ዓለም መለሰኝ ። በመስቀል ሥራ እኔን በፍጹም ለውጦኝ እስከዛሬ በእውነተኛ መለወጥ ከእርሱ ጋር እኖራለሁ!!እናንተስ የመስቀሉን ፍቅር ቀምሳችሁታል? ። ወደጌታ በእውነት ቅረቡ እውነተኛውን የመስቀሉን ፍቅር ትቀምሳላችሁ!!!
                                                                                                         በቸር ይግጠመን!!

                                                                                                           ኃይሉ ነኝ     

ያንተ ተስፋ ማነው?

 ያንተ ተስፋ ማነው?
(የእርሱ ታማኝነት እንደ ጋሻ ወይም እንደከተማ ቅጽር ይሆንልህል)
                                  መዝሙር 91፡4
እግዚኣብሔር ተስፋ ገብቶልናል
እኛም በእርሱ ታምነናል
እኛን ሊጠብቀን ሊያድነን
ከሚመጣው መቅሰፍት ሊያወጣን
ካልጠበቅነው ካላሰብነው
ይሆናል ብለን ካልገመትነው
ጠላት በእኛ ላይ ከሸረበው
ሊያጠፋን ካዘጋጀው ካጠመደው
መከራ ሆነ ሀዘን
ለእኛ አቅም ከሚከብደን
ግራ ከሚያጋባ ከሚያስጨንቅ
ወይም ለሌላው ከሚያስደንቅ
በሞት ሸለቆ ብንጓዝ
ቢጠፋ የሚጨበጥ የሚያዝ
ተስፋ ገብቶልናል ሊጠብቀን
እንደጋሻ ሆኖ ሊያድነን
ደግሞም ዙሪያችንን ሊከበን
መከላከያ አምባ ሊሆነን
ያንተስ መታመኛ ማነው?
የሚጠብቅህ የምትጠብቀው
መመኪያ ሥጋ ለባሽ ነው
ያኔውኑ ቅንጥስ የሚለው
መደገፊያ አሸዋ ነው ሸንበቆ
ዛሬ ታይቶ ነገ የሚታየው ደርቆ
ያንተ ተስፋ ምንድነው?
ጉልበቴ ነው የምትለው?
        በቸር ይግጠመን!!
        ኃይሉ ነኝ!



ታማኝ ሆኜ ልኑር!!

ታማኝ ሆኜ ልኑር!!
ለሰጠኋችሁ ሕግና ትህዛዝ ሁሉ ታማኞች ሁኑ
እኔ እግዚኣብሔር ነኝ     ዘሌዋውያን 19፡37

ዳገት ቁልቁለቱን ወንዝ በረሃውን
ለሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚያስቸግረውን
አርባ ቀን በበርሃ የተንከራተትከው
አንተ ሆነ ሳለ ሁሉንም የፈጠረከው
የዓለም መንግሥታት ሁሉን የመሰረትከው
ምድርና ሞላዋን ለአንተ እሰጥሃለሁ
ብሎ የፈተንህ ጥያቄ ያቀረበው
ፈተናውን ሁሉ በቃልህ የመለስከው
የሰይጣንን  ፈተና በድል የፈፀምከው
እኔን ለማዳን ነው ሁሉንም የቻልከው
በሮማን ወታደር ጀርባህ የተገረፍከው
እንደወንጀለኛ በመስቀል የሞትከው
ሥልጣኑ እያለህ ያንን የፈጸምከው
በጠላቴ ላይ ሥልጣን እንዲኖረኝ ነው
ከአስከፊው ሕይወቴ ፍጹም የለወጥከኝ
ሞት ተፈርዶብኝ ነፃ ያወጣህኝ
በችግር ዘመኔ ከለላ የሆንከኝ
ጌታ ያደረግክልኝን ይህንን ረስቼ
ዳግመኛ እንዳልሰቅልህ ከዓለም ተስማምቼ
ዘመኔ ተፈጽሞ ወደአንተ እስክመጣ
በምድር ኑሮዬ አንተን እንዳላጣ
ጌታ ሆይ!! ጠብቀኝ ልኑር በእግርህ ሥር
እንዳላሳዝንህ ታማኝ ሆኜ ልኑር
           በቸር ይግጠመን!!
            ኃይሉ ነኝ!


ከጀርባ ሞት አለ

            ከጀርባ ሞት አለ
ኃጢያት ስለበዛ በሰዶም ጎመራ
አመንዝራ ርኩሰት ቢሆን በዚያ ስፍራ
ዘፈንና ሟርት ሰዶም ቢንሰራፋ
የኃጢያት ዓይነቶች በአገሩ ቢስፋፋ
አምላክ ተመልክቶ የአሕዛብ ርኩሰት
መላእክት ታዘዙ ሰዶምን ሊያጠፉት
አንድ ጻድቅ ቢገኝ በዚህ የሞት መንደር
መላእክት ተላኩ ወደነሎጥ ሰፈር
የእግዚኣብሔር መላአክ ወደሎጥ ቤት ሄዶ
ማስጠንቀቂያ ሰጠው በጥብቅ አስገድዶ
የከተማው ነውር ስለበዛ ርኩሰት
ትልቅ ስለሆነ በእግዚኣብሔር ፊት
በተወሰነ ሰዓት ጸሐይዋ ሳትወጣ
በሰዶም ጎመራ ቅጣት ስለሚመጣ
ቤተሰብህን ይዘህ በአስቸኳይ እንድትወጣ
ምንም ስለሌለ ስለመኖር ተስፋ
በከተማው ክፋት አንተ እንዳትጠፋ
ሎጥ ስማ አንዳች ሳትዘገይ
ልብሴን ቅሌን ሳትል ሳትሆን ወላዋይ
ሚስትና ልጆችህ ያንተ የሆኑትን
ይዘህ እንድትወጣ ሳታይ የኋላህን
መልእክቱን አስታውሶ መላእኩ ያለውን
ሄደ ወደዞዓር ፈልጎ ከተማውን
የሎጥ ሚስት ግን በሃሳብ ተጓዘች
በሰዶም ያለውን ሀብት ንብረት አሰበች
ስለወርቅ ብሩ በጣሙን ተከዘች
ሀብቴና ንብረቴ የደከምኩበት አለች
አውጠነጠነች አወጣች አወረደች
በአገሩ የሚኖሩትን ሁሉንም ገመተች
እንዴት ይህን ያህል ይጠፋል ብላ አለች
ቤታችን የመጡት የእግዚኣብሔር እንግዶች
ማታ  የተናገሩት በሚስጢር ያወሩት
ለራሳቸው ጥቅም ምናልባት ሊይደርጉት
አስበው ይሆናል አትዙሩ ያሉት
ቢሆንም ባይሆንም እውነት ሆነ ውሸት
ቆይ አንድ ጊዜ ብቻ ከተማዋን ልያት
የምትከተለውን ሁሉ ቤተሰቧን ረሳች
ወዲያውኑ ፊቷን ወደሰዶም አዞረች
የሎጥ ሚስት በቅጽበት የጨው ክምር ሆነች
ሁሉን ነገር ትተን ጌታ ይበልጣል ብለን
እንዳልተከተልነው የዓለም ምቾት ረስተን
ዓለም በቃችኝ ትርፉ ሞት ነው እንዳላልን
መሃላችን ረስተን ዛሬ ከየት አለን?
ቀጭኑ ጎዳና የጠበበው ሕይወት
ይሻልሃል እርሱ ጌታ የሚገኝበት
የሰፊው ጎዳና ጠላት የነገሰበት
ከጀርባው ሞት አለ ለዘለዓለም ሞት
ከጀርባ ሞት አለ የጨው ዓምድ መሆን
ተመለስ ወንድሜ ከንቱ እንዳትሆን
                  
                    በቸር ይግጠመን!!

                     ኃይሉ ነኝ!