ለኢየሱስ ቀላል ነው
ሁለቱ ማርያሞች በአንድነት ሆነው
የከበረ ሽቶ በዋጋቸው ገዝተው
የጌታን ሬሳ ሊቀቡት ፈልገው
የናርዶሱን ሽቶ በጉያቸው ይዘው
በአትክልቱ ውስጥ በመቃብሩ ሥፍራ
ሳይሽቀዳደሙ ሆነው በአንድ ተራ
መጡ ወደ መቃብሩ ከሰሎሜ ጋራ
ገና ከቤታቸው ሳሉ ከመንደራቸው
እንዲህ ተባባሉ እርስ በራሳቸው
በልባቸው ሆኖ ያብሰለሰላቸው
ሲገምቱት ደግሞ በጣም የከበደው
ረዳት ለማግኘት አወጡት ካፋቸው
እኛ ሶስታችንም ፍጹም የማንችለው
የመቃብሩ ድንጋይ ሐውልት የመሰለው
ሽቶውን እንዳንቀባው ተደንቅሮ ያለው
የመቃብሩን ደጃፍ መግቢያውን የያዘው
ወደውስጥ እንድንገባ ማነው ሚያንከባልለው?
ድንጋዩን ለማንሳት ማነው የሚችለው ?
ይህንን ተናግረው ጉዞአቸውን ቀጥለው
ወዲያውኑ ሲደርሱ ከመቃብሩ ሥፍራ
በሃሳብ ሲገምቱት የሆነው ተራራ
ድንጋዩ ተንከባሎ
ደጃፉንም ጥሎ
ከሥፍራው ላይ ጠፍቶ
ተገኘ ትከፍቶ
ነገራችሁ ሁሉ የሆነ የሚያስፈራ
ችግርና ሀዘን እንዲሁም መከራ
ያልቻላችሁት ነገር ልትሰጡት አደራ
እንደሚከብድ ድንጋይ የተጫነባችሁ
ፊት ለፊት ለግጥሚያ የተጋረጠባችሁ
ገለል በል ብትሉት አልርቅም ያላችሁ
ጌታን ተማጸኑት ድል ታገኛላችሁ
ችግሩ ሲጠፋ በውን ታያላችሁ
ለመክፈት ለመዝጋት ስልጣን በእጁ ያለው
ሸክምን ለማራገፍ ለኢየሱስ ቀላል ነው።
በቸር ይግጠመን!!
ኃይሉ ነኝ!
No comments:
Post a Comment