ተስፋዬ እግዚኣብሔር ነው።
ያኔ በለጋነት ያኔ በልጅነት
ሕይወቴን ሲነካት ነፍሴን ሲያስጨንቃት
አምላኬን አወቅሁት ጌታን ተረዳሁት
ልቤን ከፈትኩለት በልቤ አስገባሁት
እኔ ልገዛለት ራሴን ሰጠሁት
በፊቱ ተንበርክኬ በፀሎት ጠየቅሁት
መድኔን ላልክደው ቃሌን ገባሁለት
ዓለም አሳይታኝ ሳቅና ፈገግታ
ያላት መስሎኝ ደስታ የምትሰጥ እርካታ
ወዲያ ወዲህ ስትል ነገር ስታስመስል
ያላት መስሎኝ ፍቅር እኔኑን ስትሰልል
ዓለምን ተጠጋኋት እርሷን ተከተልኳት
ለካስ እሳት አላት የምትፋጅ ናት
የምታቃጥል ናት የምታደርስ ከሞት
እንዲህ አደረገችኝ ወደእርሷ ሳበችኝ
ፈገግታ አሳይታኝ በእጅዋ አስገባችኝ
በውስጥዋ አስገብታ የምትሰጥ መስላ ደስታ
እንደኳስ ለግታ በሥጋዬ ተጫውታ
ሞራሌንም መትታእኔን አንገላታ
ምልክቷን ትታ ስጦታዋን ሰጥታ
ለፍርድ በአደባባይዋ ቁም ስቅሌን አሳይታ
አንተ የእኔ አይደለህም ለእኔ አትጠቅምም
ጤና አትሰጠኝም ፍፁም አትሆነኝም
በአዋጅ በነጋሪት ይህንን ስትገልጽልኝ
ጌታን በመንበርከክ ንስሐ ጠይቅሁኝ
ለዘለዓለሜ ማገልገል ጀመርኩኝ
ጌታ እንደዚህ አለኝ ዳግም ተናገረኝ
አንተ የእኔ ነህ እኔም የአንተው ነኝ
በቅዱሱ ደሜ አንተን የገዛሁኝ
በዘመንህ ሁሉ አንተን እጠብቃለሁ
በምትሄድበት መንገድ እኔ በዚያ አለው
መልካምነቴንም በፊትህ አሳያለሁ
ጊዜ ዘመን አልፎ ዘመንን ተክቶ
የሕይወት ውጣ ውረድ ኑሮዬን አዛብቶ
ብረር ብረር አለኝ ካናዳ ሊያኖረኝ
የኑሮ ሐዲዱ መሪው አሻገረኝ
በቤት በአደባባይ ሰው እያደረገኝ
እስከዛሬ ድረስ እኔም ከእርሱ ጋር ነኝ
ሌላውን የተስፋ ቃል እጠብቃለሁኝ
ዓመት ሁለት ዓመት ከነፉ ዓመታት
አምላኬ ለእኔ ቃሉን የሰጠበት
በአምላኬም ፈቃድ ጉዞ የጀመርኩበት
እምባዬን አብሼ ቅኔ የተቀኘሁበት
ሙሉ ነጻነቴን የተቀዳጀሁበት
ወደ ዓለም አልሄድም ወይ እርሷ አትመጣም
ቃለ መሐላዬን ከእንግዲህ አታጠፋም
ዓለምን ፈልጋ ወደምድርዋ አልጓዝም
እርሷም አትመጣም እኔም አልሻትም
ጌታ የሰጠኝን በእርሷ ፊት አልጥልም
ቃል የገባልኝን ፍፁም አልዘነጋም
እንደሚፈጽምልኝ ምንጊዜም አልረሳም
ለእኔ የተናገረው ወደፊት ሊያደርገው
ታማኙ ጌታዬ ሁልጊዜም ታማኝ ነው
ሸለቆ ባይሞላ ሐሩር ቢያደርቀው
ከብቶች ባይኖሩኝ በእምነት የማግደው
በእጆቼ የያዝኩት ወርቅ አልማዝ ምቆጥረው
ቤቶች ባልገነባ ጎጆዬ ነው የምለው
ሁሉን እስኪያደርግልኝ እሱ እስኪፈጽመው
በመጠበቂያዬ በአምባዬ እቆማለሁ
አንድ ነገር ብቻ እኔ እረዳለሁ
ሁሉን የሚያደርገው ተስፋዬ እግዚኣብሔር ነው
በቸር ይግጠመን!!!
ኃይሉ ነኝ!! 5/12/2006
No comments:
Post a Comment