እንደዚህ
ነበር!!
ከአገሬ ወጥቼ ከሰው አገር ብገኝ
ከዓመታት በኋላ አገሬ ናፈቀኝ
ከቤተሰቦቼ መልእክት ቢደርሰኝ
አገሬን ለማየት ናፍቆቱ አደረብኝ
ናፍቆቴ ቢታጨቅ በብዙ ነገሮች
ቆርጪ ተነሳሁ ላያቸው ወገኖች
ከዚህ በተረፈ በሚተርፈኝ ጊዜያት
ወዲቱ ኢትዮጵያን አገሬን ለመጎብኘት
ወንዝ ተራራዎችን የታሪክ ገዳማት
የጀግኖች ወገኖቼን የሰማዕታት ዐውልት
ለማየት ጓጓሁኝ የአገሬን አራዊት
በሃሳብ ሆኜ ይህንን ስመለከት
ወስኜ ተነሳሁ ለመሄድ አገር ቤት
ትኬቴን ቆርጪ የምሳፈርበት
ቀጠሮዬን ይዤ ልክ በዚያው ዕለት
ወደኢትዮጵያ ምድር እኔ የምጓዝበት
ለቤተሰቦቼም ስልክ ደውዬላቸው
የምደርስበት ሰዓት በውል ነገርኳቸው
ስጦታዬን ይዤ ሻንጣዬን ቀርቅቤ
ብርድም እንዳይመታኝ ልብሴን ደራርቤ
እንደተዘጋጀው ለመሄድ ለመብረር
ስልክ ተደወለልኝ በአጋጣሚ ነገር
ዚስ ኢዝ ኃይሉ ስፒክ
ለደወለልኝ መልሴ ለወዲያኛው መድረክ
ዩር ፕሮግራም ትራንስፈር
ዋት? ዉ ኢዝ ስፒከር
መልስ ሳይሰጠኝ ድርግም አደረገው
ከእንቅልፌ ባንኜ ጉዳዩን ሳስበው
በውኔ ሳይሆን ለካስ በሕልሜ ነው
የዚያን ዕለት እንደዚህ ነበር
ለወሬ የማይመች ደግሞም ለመናገር
በአየር ተሳፍሬ ልገባ አገሬ
ካርቱምን አልፌ ስደርስ ወደምድሬ
የአየር ጎረቤቴ አጠገቤ ያለው
የያዝከው ፓስፖርት የካናዳ ሕዝብ ነው
እንደአነጋገርህ የት ነው የምትኖረው
ከአገርህ ውጪ የቆየህ ትመስላለህ
ኢትዮጵያ ስትገባ ተቀባይ ሰው አለህ?
ወይስ ከተማውን በደንብ ታውቀዋለህ
የማታውቀው ከሆነ እኔ አውቀዋለሁ
መኪናም ስላለኝ እኔ አደርስሃለሁ
በጉዳዩ ተስማምተን ዕቃ ተቀብለን
ከመኪናው ሥፍራ እየገፋን ደርሰን
ከመኪናው ጀርባ ዕቃችንን ጭነን
ተሽቀዳድሞ ሮጦ ጋቢና ገባና
ሞተሩን አሙቆ ማርሹን አስገባና
መንገዱን ቀጠለ እኔን ተወኝና
እጆቼን ዘርግቼ እየሮጥኩ በፍጥነት
አምቧርቅ ጀመረ ሌባ ያዙ በማለት
የጩኸቴ ሲቃ ሕዝቡን አስደንግጦት
እንደዕብደት ያረገኝ ያመመኝ መስሎት
እጆቹን አንስቶ ያዝ ሲያደርገኝ
ከሄድኩበት ዓለም ወዲያው ሲመልሰኝ
እዚያው አይሮፕላን ውስጥ ከጓደኛዬ ጋር ነኝ
የዚያን ዕለት እንደዚህ ነበር
ለወሬ የማይመች ደግሞም ለመናገር
በቸር ይግጠመን!!
ኃይሉ ነኝ!!2008
No comments:
Post a Comment