ምክንያቴ ብዙ ነው!!!
ዘርዝሬ ልገልጸው በአፌ ልናገረው
ምሥጋና አቅርቤ እኔ የማልጨርሰው
ያደረገልኝ በቁጥር የማልገልጸው
እግዚኣብሔር አምላኬን የማመሰግነው
የውለታው ብዛት ቁጥር ሥፍር የለው
ለጌታ ለአምላኬ ክብር የምሰጥበት
በገናዬን ይዤ ቅኔ የምቀኝበት
በእጆቼ አጨብጭቤ ስለት የማገባበት
ፅናጽሉን ለእርሱ ሿሿ የማሰኝበት
ምክንያቴ ብዙ ነው ጌታን የማከብርበት
ጠላቴ ሊጥለኝ እንደአመድ ሊረግጠኝ
አለቀለት በቃ ልገድለው ነው ሲለኝ
ዕድሜውን ልቀጨው ወደሞት ልወስደው
ይህንን ቃል ዝቶ ወጥመድ አዘጋጅቶ
ሕይወቴን ሊያጠፋ ጠላት ተዘጋጅቶ
መሣሪያ አበላሽቶ ብሎኖቹን ፈትቶ
ሳላስበው ድንገት እኔን አዘናግቶ
ሊገድለኝ ሲያደባ
ሊከተኝ ከጉድባ
የመሞቴን አዋጅ በጉራ ሲያውጅ
ጌታ ኢየሱሴ አወጣኝ ከሞት ደጅ
ከመሞት አድኖኝ በክብር ላቆመኝ
ይህንን ስላደረገ ክብር እሰጣለሁኝ
ድምጼን ከፍ አድርጌ ላዜም ለጌታዬ
ልደርድረው እኔ ይናገር በገናዬ
እርሱ እንዲቀበለው ላቅርብ ምሥጋናዬ
ሌላ ምንም የለኝ ይህ ነው ችሎታዬ
ጠላቴ ዔላማው ሁለት እጆቼን ጎምዶ
በሚሆነው ነገር እኔኑን አናዶ
እጆቼ እንዳይጽፉ
ቃሉን እንዳያስፋፉ
የደካከሙት ተስፋ የቆረጡት
በሚያወጣው ቃላት እንዳይጽናኑበት
ነበረ ዕቅዱ የሰው ልጆች ጠላት
ጌታ አድኖኛል ከሞት አትርፎኛል
ምን ብዬ ላመስግን ቃላቶች ያጥሩኛል
መስንቆዬን ልቀኝ እስቲ ዜማ ያውጣ
ከበሮው ይከበር ክብርን እንዲያመጣ
ላሸብሽብ ልጨፍር ለአምላኬ ለጌታ
እሱን ካስደሰተው ለሰራው ውለታ
የጠላቴ ሃሳብ የእርሱ ፍላጎት
በእኔ ሊፈጽመው የነበረ ምኞት
መጻፍ መናገሬን ይህንን ተመልክቶ
የእጆቼን ውጤት በክፉ ዓይኑ አይቶ
ሰዎች በመባረክ ስላገኙ ትምህርት
ጠላቴ እንዲህ አለ እጁን ብቆርጥለት
የአመልካች የአውራ ጣት ከሥራ ባስወጣት
ቁርጥ አድርጌለት እንዳትጽፍ ባደርጋት
እጁ እንዳይሰራ ችግር ብፈጥርበት
በምላሱ አይጽፍ ፋይሉን ብዘጋለት
ነበረ ምኞቱ አልሆነም ድርጊቱ
ጠላቴ ደከመ ለፋ እንዲያው በከንቱ
ጌታዬ እንዳለው እንደተናገረው
ለእኔ እንደጋብልኝ ዘላለማዊ ተስፋው
ጠላቴ በእኔ ላይ ደግሞም በሰውነቴ
አንዳችም አልቻለም ሊያደርግ በሕይወቴ
ዛሬ ለጌታዬ እጆቼ ይጽፋሉ
ያጨበጭባሉ ክብርን ይሰጣሉ
አፌን እከፍታለሁ ቅኔን እቀኛለሁ
ማዕሌተ ቅኔ ለጌታ አቀርባለሁ
እግዚኣብሔር ይመስገን ብዬ እዘምራለሁ
ሌላ ምንም የለኝ ለጌታ እማቀርበው
ጌታ ያደረገውን ቆጥሬ አልችለው
የማመሰግንበት ምክንያቴ ብዙ ነው
በቸር ይግጠመን!!
ኃይሉ ነኝ!! 2006
No comments:
Post a Comment