Monday, February 25, 2013

ጉዞህን የሚያሰናክለው ምንድነው?


ጉዞህን የሚያሰናክለው ምንድነው ?
     

 ወጣት በነበርኩበት ጊዜ በእግር የመጓዝ ልምድ ነበረኝ ። አንዳንድ ጊዜ ጠዋት ካልተመቸኝ ደግሞ ፀሐይዋ ቆልቆል ስትል ወደ ማታ አካባቢ የእግር ጉዞ አደርግ ነበር ። በየእሁዱ በተለይም ከሽሮ ሜዳ ተነስቶ እንጦጦ ተራራውን መውጣት የዘወትር ፕሮግራሜ ነበር። እንደዛሬ ሳይሆን ብዙ መንገድ በእግር መሄድ እወድ ነበር ።አንድ ቀን ታናሽ ወንድሜ ዛሬ ተራራውን ከአንተጋር እወጣለሁ አለኝ ፤ ተው አትችልም አልኩት ፤ እችላለሁ አለኝ ፤ እባክህን ታስተጓጉለኛልህ ብለው ፤ እንዳያውም ቀድሜ እገባለሁ አለኝ ። በል እሺ አልኩትና የማታዋ ፀሐይ በረድ ስትል ጉዞ ጀመርን ። ከተረተሩ ሥር ጀምረን የመጀመሪያውን ጉብታ ወጥተን ከጨረስን በኋላ ቀጥታውን መንገድ ስንጀምር ደከመኝ አለኝ ፤ ልጅ ነው ብዬ ዛፍ ስር ቁጭ ብለን ብዙ ጊዜ አጠፋን ። ደልዳላውን መንገድ ጨርሰን ወደሚቀጥለው ከፍታ ሥፍራ ስንደርስ ደከመኝ የሚል ጥያቄ ሲያቀርብ ቢመጣ ይምጣ ብዬ መንገዴን ቀጠልኩን ፤ የአስር ደቂቃ ያህል እንደሄድኩኝ ዞር ብዬ ስመለከት ከዓይኔ ሊርቅ ሆነ ፤ ስለዚህ የግዴታ መጠበቅ ስላለብኝ ዓይኔን አሻግሪ እየተመለከትኩኝ እጠብቀው ጀመር ። እስኪመጣ ጠብቄ ጉዞአችንን ለመቀጠል ወሰንኩኝ ። ልክ እንደደረሰ እግሬ ላይ ተጠምጥሞ ፤ ከዚህ በላይ መሄድ አልችልም ግን ሁለት አማራጭ እሰጠሃለሁ አንድ እኔን ጥለህ ወደፊት መሄድ ፤ ሁለት አብረን አብረን መመለስ አለብን አለኝ ። ነገሩን ሳስበው አንድ ጭግር ቢደርስበት ዕዳው የኔ ነው ብዬ ወደኋላ ተመለስኩኝ ። እኔ ዓላማዬ ወደምፈልግበት ቦታ ደርሶ መምጣት ነው ። ግን በዚያን ዕለት ሊሆን አልቻለም ። የጽሑፉ ርዕስ ጉዞህን የሚያሰናክለው ምንድንነው ? የሚል ነው ። አዎ!! ሰማያዊ ጉዞአችንን የሚያሰናክለው ምንድነው ? እኔ እንደምረዳው ሁለት ሲሆኑ ። ውጫዊና ውስጣዊ ወይም ጠላትና ሥጋ ናቸው ። የመጀመሪያው ውጫዊ ወይም ጠላት በምንሰራው የጽድቅ ሥራ ወደጌታ በተጠጋን ቁጥር አገልግሎታችንን ጠበቅ አድርገን ስንይዝ ጠላት ወይም ውጫዊ ኃይል በተለያየ መንገድ በሚታወቅና በማይታወቅ መልካምና ጥሩ በሚመስል ሁኔታ ሊያጠፋን ወይም ከአገልግሎታችንን ሊያወጣን ይሞክራል ። እዚህ ላይ ተመልከቱ የምንዋጋው ከደምና ከሥጋ ጋር ሊመስለን ይችላል ፤ ግን አይደለም የእግዚኣብሔርን ሥራ በምንሰራበት ጊዜ የምንዋጋው ከጠላት ጋር ነው ። ጠላት ዲያቢሎስ ደግሞ በግንባር እያወቅነው ፊት ለፊት እንድንዋጋው አይመጣም የሚመጣው በተለያየ መንገድ ነው። ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች በ1 ተሰ2፥18 ሲጽፍላቸው (ወደ እናንተ ለመምጣት ፈልገን ነበር ። በተለይም እኔ ጳውሎስ ብዙ ጊዜ ሞክሬ ነበር ። ነገር ግን ሰይጣን አዘገየኝ ) ይላል ። እዚህ ላይ ስንመለከት ጳውሎስ ብዙ ጊዜ ወደ ተሰሎንቄ ለመሄድ መሞከሩን ግን እንዳይሄድ እንዳዘገየው ይናገራል ። ስንገምተው ሰይጣን በግንባር ተገኝቶ ከጳውሎስ ጋር ግብግብ ገጥሞ የቀረ ይመስለናል ? አይደለም ነገር ግን ወደ ተሰሎንቄ እንዳይሄድ የቆሮንቶስ ጉዳይ እያሳሰበው የቆሮንቶስ ጉዳይ መፍትሔ ሲያገኝ ፤ ወደ ተሰሎንቄ ለመሄድ ሲዘጋጅ በበሽታ ምክንያት ሃሳቡን ቀይሮ ሊሆን ይችላል ። ምናልባትም በመርከብ እጦት ምክንያት የጉዞ ፕሮግራሙን ለማስተካከል ሳይችል ቀርቶ ሊሆን ይችላል ። ጳውሎስ የቀረበትን ምክንያት አናውቅም ፤ ጳውሎስ ግን ሰይጣን አዘገየኝ ይላል የቀረበት ምክንያት በውጫዊ ችግር ነው ። ወደእኛ ስንመለስ ጠላት በምንሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት ምክንያቶችን ያስቀምጣል ለዚያ ምክንያት መፍትሔ ስናገኝለት ሌላ ችግር እየደራረበ ከዚያ አዘቅት ውስጥ እንዳንወጣ ይጥራል ፤ የእግዚኣብሔርንም ሥራ እንዳንሰራ ፕሮብሌሞችን ይደራርባል ። ነገሮች ከአቅማችን በላይ ሆነው አቅላችንን አሳጥቶ ከአገልግሎታችንም ሊያስወጣን ይሞክራል መፍትሔው ግን በያዝነው የተቀደሰ ጎዳና ከጌታ ጋር መቀጠል ነው ። ጠላት ሰነፍ ካገኘ ድል ሳይቀዳጅበት አይተወውም ፤ ብርቱ ወታደር ግን በጠላት ላይ ድል ሳይቀዳጅ ወደኋላ አይልም ። ለዚህኛው ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ዳንኤል ነው ። ትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 6 በሙሉ ስናነብ ፤ ዳንኤል ልዩ የጥበብ መንፈስ የሞላበት ሆኖ በመገኘቱ እንደ ዘመናችን አጠራር ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ታጨ ወይም ዳርዮስ በመንግሥቱ ላይ የመጨረሻውን ሥልጣን ሊሰተው አሰበ ። ከመሳፍንቱና ከመኳንንቱ አስበልጦ ስለመረጠው ይህንን ጉዳይ ለማሰናከል ሰይጣን በበላይ አስተዳዳሪዎችና መሳፍንቱ ላይ ገብቶ ዳንኤል የእግዚኣብሔር ሰው ስለሆነ ሊያጠፋው ተነሳ ። አስተዳዳሪዎችና መሳፍንቱ በአንድነት ወደ ንጉሡ ሄደው ዳንኤልን ለማጥፋት ወደ አምላኩ የሚያቀርበውን ፀሎት ለማሰናከል የዶለቱትን ለንጉሥ ዳርዮስ በአዋጅ መልክ እንዲያወጣው ነገሩት ፤ ንጉሥ ዳርዮስ ሆይ !! እስከ ሰላሳ ቀን ድረስ ወደአንተ ካልሆነ በስተቀር ማንም ሰው ወደሌላ ሰውም ሆነ ፤ ወደሌላ አምላክ መጸለይ እንደሌለበት ፤ ንጉሥ አዋጅ እንዲያወጣ ትህዛዙም እንዲፈጸም ይህንን ትህዛዝ የተላለፈ ወደአንበሶች ጉድጓድ እንዲጣል የሚል ነበር ። በንጉሥ ፊት መልካም የሚመስል ነገር ግን ዳንኤልን ለማጥፋት የተዶለተ ፤ መልካም የሚመስል ነገር ግን በመርዝ የተቀመመ ነበር ። ንጉሥ ዳርዮስ ሃሳቡን ሲሰማው ክብሩን የሚያጎላለት ነውና ደስ ብሎት ሕጉን አወጣ ። ዳንኤል ግን ወደ አምላካችሁ አትጸልዩ የሚለውን አዋጅ መውጣቱን ሲያውቅ ፤ አዋጁ አላስደነገጠውም ፤ በአንበሳም ጉድጓድ መጣልም አላስፈራውም ። ለአምላኩ ግን ታማኝ ወታደር ሆነ ። ዳንኤል በሌላ ጊዜ ያደርግ እንደነበረው መስኮቱን ከፍቶ በቀን ሶስት ጊዜ ፀሎቱን ይፀልይ ጀመር ። እውነተኛ አገልጋይ ከሆንን ጠላት እኛንና አገልግሎታችንን ሊያሰናክል ይነሳል በዚህ ጊዜ ልንጠነቀቅና ድል በጠላታችን ላይ ልንቀዳጅ መታገል አለብን እንጂ ከአገልግሎታችን ገሸሽ ልንል አይገባንም ፤ ምክንያቱም ጳውሎስ እንደሚለው የድል አክሊል ይጠብቀናልና ልናስበው የሚገባን ያንን ነው ።
       ሁለተኛው ደግሞ ከውስጣችን ወይም ከሥጋችን ነው ፤ የውስጥ ነገር በጣም አስቸጋሪና አደገኛም ነው ከውጪ የሚመጣው የሚታይ ጠላት ነውና ልንቋቋመው እንችላለን ከውስጣችን የሚነሳው ባለጋራችን ግን በፆምና በፀሎት ካልሆነ ልንቋቋመው አንችልም ፤ ብዙ ጊዜም አሉ የሚባሉ አገልጋዮችም የሚፈተኑትና የሚወድቁት በውስጣቸውና በሥጋቸው ነው ። በውስጣችን የሚፈጠረው እኔነት ራስን ማስቀደም ሳይሞት የቀረው ማንነት ከጌታ እንዳንጣበቅ የሚያደርገን ይህ ነው ። ሰይጣን እግዚኣብሔርን ለመሆን ፈለገ ስለዚህ ለመላእክቱ እኔ ፈጣሪያችሁ ነኝ አላቸው ። ሊሆን የማይችለውን ፈለገ በትዕቢት ተነፋ እውነት አምላክ የሆነ መሰለው እግዚኣብሔር ግን ሰይጣንን በትዕቢቱ ምክንያት ከነበረበት የክብር ሥፍራ ወደ ምድር  ተጣለ ። ጌታ ኢየሱስ እኛን አገልጋዮቹን ስለሚወደን እንድንጠፋበት አይፈልግም ፤ ግን እኛ ሕጉን ጥሰን ወደማይገባው አቅጣጫ ስንሄድ ኃላፊነቱ የራሳችን ነው ። ለዚህ ጥሩ ምሳሌያችን ሳምሶን ነው ። ከእግዚኣብሔር ቃል መሳፍንት ምዕራፍ 13 እንመለከታለን ። የእግዚኣብሔር መላእክት ማኑሄ ወደ ተባለ ከዳን ወገን የተወለደ አንድ ፆርኣ ሰው እንደነበረና ሚስቱ መካን እንደነበረችና የእግዚኣብሔር መላእክ እንደተገለጸላት ይገልፃል ። መለኩ ሲገለጽላት ትህዛዝ ነግሮአት ነበር ። ከትህዛዙ አንዱ የምትወልደው ልጅ ምላጭ በራሱ ላይ እንዳይደርስበት ከእናቱ ማህፀን ጀምሮ የተመረጠ ናዝራዊ በመሆን ለእግዚኣብሔር የተለየ ይሆናል የሚል ነበር በተጨማሪም እስራኤልን ከፍልስጤማውያን እጅ መታደግ እንደሚችል ተናግሮአታል። ይህ ሁሉ የተስፋ ቃል የተነገረለት ለሳምሶን ነበር ። ከተወለደ በኋላ እግዚኣብሔር እስራኤልን ነፃ በማውጣት ብዙ ተጠቅሞበታል ። እንዲያውም በእግዚኣብሔር ቃል መሳፍንት 15 ፥ 20 ሳምሶን በፍልስጤማውያን ዘመን በእስራኤል ላይ ለሃያ ዓመት ፈራጅ ሆነ ይላል ። በምዕራፍ አስራ ስድስት እንደምንመለከተው እግዚኣብሔር ወደማይፈልገው አቅጣጫ ሄደ የሥጋው ነገር አሸነፈው ፤ መናገር የሌለበትን ስለ ፀጉሩ ሚስጢር ተናገረ ፤ ጸጉሩ በተላጨ ጊዜ የእግዚኣብሔር ክብር ከላዩ ላይ ተገፈፈ ። በጠላቶቹ እጅ ወደቀ ። ጉልበታም መሆኑ ቀርቶ እንደማንኛውም ሰው ሆነ ። አወዳደቁ አልማረም ዓይኑ ጠፍቶ የጠላት መጫወቻ ሆነ ።  እያንዳንዳችን የጌታ ኢየሱስ ደቀመዛሙርቶች ልናስብ ልንዘጋጅ የሚገባን ነገር ከውጪያዊ ጠላታችን የበለጠ ልንጠነቀቅበት የሚገባው በውስጣችን ሳይሞት የቀረውን የሥጋችንን ነገር ነው ። በገላቲያ መጽሐፍ 5፥19 ና በማቴዎስ 15 ፥ 19 የተገለፀው እንደፍም እሳት ተዳፍነው ያሉና የተመቻቸ ሁኔታ ሲያገኙ የሚፈነዱ ስልሆነ ልንጠነቀቅበት ይገባል ። ከውስጣችን በሚነሳው ጠላታችን ከተሸነፈን አወዳደቃችን አደገኛ ነውና ፈተናው ከመምጣቱ በፊት መንገዳችንና አቅጣጫችንን ልንመረምርና ዘወትር ቃሉን እያጠናንና እየጸለይን ልንተጋ ይገባናል በአገልግሎቱ የተጋ ሁሉ የሕይወት አክሊል ይጠብቀዋልና።
                                                                                ጌታ ይባርካችሁ!!
                                                                                 በቸር ይግጠመን!!!
                                                                                 ኃይሉ ነኝ!



        
                 






No comments:

Post a Comment