ወንድማዊ ፍቅር(Philadelphia)
ጌታ በቃሉ ሲነግረን ሲያስተምረን
እንደራስህ አድርገህ ውደድ ጠላትህን
ከራስህም በላይ አፍቅር ወንድምህን
የሚያቃናልህን የሕይወት ጎዳናህን
እምነት ተስፋ ፍቅር ፀንተው ይኖራሉ
ለዘላለም ነዋሪ ፍቅር ነው ከሁሉ
እኔ እንደወደድኳችሁ እንዳፈቀርኳችሁ
እንድትዋደዱ እርስ በራሳችሁ
በቃሉ ተጽፎ ተገልጾ እንደምናየው
የተቀመጠልን መዝገቡ ሰፊ ነው
በሰው አቅም እንኳን የማንመረምረው
ከሰፊው መዛግብት ጥቂቱ ይህ ነው
ጴጥሮስ ወደጌታ ኢየሱስ ቀርቦ
በነገሩ ላይ በጣሙን አስቦ
በዳዩን ወንድሜን ስንቴ ይቅር ልበለው
ኸረ! ለመሆኑ መጠኑ ስንት ነው?
የቁጥሩ መጠን ሰባት ጊዜ ነው?
ወይስ ከዚህ በላይ መተመኛ አለው?
ይህንን ጥያቄ ቢጠይቀው ጴጥሮስ
እንደዚህ እያለ ሲመልስ ኢየሱስ
ዝርዝር አድርጎ ሲገልጽለት እውነት
በመገረም ነበር ሰዎች ያዳመጡት
እኔ የምላችሁ ሰባት ጊዜ አይደለም
ፍቅርንም ለመግለጽ ይህ አይመጥንም
ሰባት ጊዜ ሰባ መጠኑ ይህ ነው
የይቅር ባይነት ሂሣብ መተመኛው
ከአራት መቶ በላይ ቁጥሩን ስናየው
የፍቅር ታጋሽነት መቻሉን ጭምር ነው
ፍቅርና ትዕግሥት ሚስጥሩ የገባው
ጴጥሮስ እንዲህ አለ በዘመን መጨርሻው
ለጌታዬ ፍቅር ምርጫዬ ይህ ነው
ወደታች ቁልቁል ነው እኔ ምሰቀለው
ጳውሎስ ለሃይማኖቱ ቀናተኛ ነበር
ክርስቲያኑን ሁሉ አሳዶ የሚያስር
ጌታን ሳያስበው ድንገት አገኘውና
አገልጋይ አረገው በራሱ ጎዳና
ሩጫዬን ሩጪ ሥራዬን ፈጸምኩኝ
ወንጌልን ለአሕዛብ ፍቅርን አስተማርኩኝ
ሩጫዬን ፈጽሜ ስላገባደድኩኝ
ወደጌታዬ ስሄድ የድል አክሊል አለኝ
እስጢፋኖስ ሲላስ እንዲሁም ማቴዎስ
ማርቆስ ጢሞቲዎስ ሌላውም ዮሐንስ
ቁጥር የሌላቸው የሃይማኖት አርበኞች
የፍቅር ምልክት ልዩ ምስክሮች
ደማቸው እስኪፈስ የተደበደቡት
ለሥጋ ሳይሳሱ በዘይት የፈሉት
የእምነት አባቶች ምሳሌ የሆኑት
ተተኪውን ትውልድ ፍቅርን ያስተማሩት
የጌታ ፍቅር ስፋቱ ምን ያህል ነው
ወርድና ርዝመቱን በሜትር ስንለካው
የፍቅርን መጠን በምን እንለካለን?
ምን ያህል እንደሆን እንዴት እናሰላለን?
አዎ! ሜትር ተሰብስበው መለኪያ ቢሆኑ
ሂሣብ አዋቂዎች ፍቅርን ቢተምኑ
መስፈሪያ የለውም የሚመዘንበት
የጌታ ኢየሱስ ፍቅር ሰው የሚያሰላበት
የተቀመጠልን መዝገቡን መርምረን
አንጓ የሆነውን ሁሉንም ፈትሸን
ዋናውን መሰረት ፍቅርን ጨብጠን
ሁለት ዓመት አልፈን ሶስትን አስቆጥረን
ዛሬም ስምንት ላይ ከጌታ ጋር አለን
ጠላት እንዳሰበው ሳንሆን ተፈቃቅረን
የሰይጣን ወረራን በፍቅር ሰባብረን
ዛሬም ከጌታ ጋር ወንጌል እንሰብካለን
ወንድማዊ ፍቅር ሰጥቶናል
እጅ ለእጅ በአንድነት አያይዞናል
ጌታ በፍቅር አንድ አድርጎናል
ቃል ኪዳኑን ይዘን ወደፊት ብለናል
ሰንደቅ ዓላማችን አድርገን የያዝነው
ቃል ኪዳናችን ነው የምንተገብረው
ሌላ ዓላማ የለንም እግዚኣብሔር ፍቅር ነው
ለእኛ ጌታ ነግሮናል ፊላደልፊያ ብሎናል
በወንድማማች ፍቅር እንድንኖር መክሮናል
የተከፈተ በር ኢየሱስ ሰጥቶናል
ማንም የማይዘጋው እርሱ ከፍቶልናል
ወንጌልን በፍቅር እንድንሰብክ ነግሮናል
የጠፉትን ነፍሳት እንሰበስባለን
በፍቅር አገልግለን ለፍቅር እናልፋለን
ጌታችን ሲመጣ የድል አክሊላችን
እንቀበላለን ከእርሱ ከአምላካችን
በቸር ይግጠመን!!
ኃይሉ ነኝ
No comments:
Post a Comment