Sunday, March 3, 2013

አልከዳህም!!! ትከዳለህ!!


                    አልከዳህም!!! ትከዳለህ
ኢየሱስም፤ “ በእውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ በዚህች ሌሊት ዶሮ
ሁለት ጊዜ ከመጮኹ በፊት አንተ ሦስት ጊዜ ትከዳኛለህ”
አለው።                       ማርቆስ 14 ፡ 30

አይሁድ ተሰብስበው ጌታችን ሊሰቅሉት
በመጨረሻው ዕለት በቀረችው ሰዓት
እግራቸውን አጥቦ ሲያበላቸው እራት
ቁጭ ብለው ሳለ በሰው ቤት ሰገነት
ከመውጣታቸው በፊት ወደ ደብረ ዘይት
ለተከታዮቹ ለደቀመዛሙርት
ጌታ እንዲህ አላቸው
እረኛው ሲመታ ይበተናል መንጋው
ችግሩ ሲመጣ ሁሉም ይከዳኛል
ከእናንተ እያንዳንዱ እኔን ይረሳኛል
ጴጥሮስ እንዲህ አለ እኔ አልለይህም
እስከ ሞትም ድረስ ፍጹም አልከዳህም
ሁሉም ቢከዳህም እኔ አልተውህም
ጴጥሮስ አትሳሳት አትናገር ውሸት
ሶስቴ ትከዳለህ ዶሮ ሳይጮኽ ሌሊት
ጌታችን ሲገርፉት በመቃ ሲመቱት
በጃኖ ሸፍነው ማን መታ እያሉት
እንደ ሰው ቆጥረውት ሲያላግጡበት
ፍዳውን ሲያበሉት ይህንን በመመልከት
ይከተለው ጀመር ሆኖ ከእርሱ በርቀት
ጴጥሮስ ርቆ ሄደ ሰዎችን በመፍራት
ካህናት ግቢ ውስጥ በትችኛው በኩል
እሳት በሚሞቁ በስዎች መካከል
በየፊናው ሥራውን ሲተገብር
ጴጥሮስ በበኩሉ በፍርሓት ላይ ነበር
ከገረዲቱ አንዱ ወደ እርሱ ተጠግታ
በእርግጥ ስላወቀችው በጣም ተመልክታ
አንተ ከናዝሬቱ ጻድቅ ከምትለው
ከኢየሱስ ጋር ነበርክ ብላ ስትለው
አንቺ የምትይው አላውቅም ያንን ሰው
ሆኖ በመደንገጥ ሀፍረት እየገባው
ለመጀመሪያ ጊዜ ድንገት ሳያስበው
ጌታውን በመክዳት ሄደ ወደ መግቢያው
በዚያ ሰዓት ነበር ዶሮ ሊጮኽው የቻለው
ከሰዓት በኋላ በዚያ ስፍራ ላሉት
በበሩ አቅጣጫ ቆመው ለሚገኙት
ይህ ሰው ከነርሱ ጋር ነበረ በማለት
ስለተናገረች በዚያ ለነበሩት
ይህ የምትይው የምትናገሪው አላስታውሰውም
እኔ ከእርሱ ወገን ፍጹም አይደለሁም
ለሁለተኛ ጊዜ ሆኖ በሰዎች ፊት
መዋሸት ጀመረ ጌታውን በመክዳት
ለሶስተኛ ጊዜ በዚያ የተሰበሰቡት
ክብ ዙሪያ ቆመው እሳት ለሚሞቁት
አንተ የገሊላ ሰው እንደመሆንህ መጠን
አንጠራጠርም ከእርሱ ጋር እንደምትሆን
እኔ አላውቀውም እያለ ሲገዘት
ወዲያው ዶሮ ጮኽ ለሁለተኛ ጊዜያት
ጴጥሮስ ሲያስታውሰው ጌታ የተናገረው
በውድቅት ሌሊት ትከዳለህ ያለው
ዶሮ ሲጮህና ኢየሱስን ሲያየው
በእርግጥ መክዳቱን ያኔ ነው ያወቀው።
                  በቸር ይግጠመን!!!
                  ኃይሉ ነኝ!! Mar, 2009


           

ይመጣል ጌታችን!!!


   ይመጣል ጌታችን!!
“እናንተ የገሊላ ሰዎች ስለምን ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ቆማችኋል?
ይህ ወደሰማይ ሲያርግ ያያችሁት ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲያርግ ባያችሁት
ዓይነት ተመልሶ ይመጣል” አሉአቸው።         
                                                 የሐዋርያት ሥራ 1 ፡ 11
እኛኑን ሊያድነን ከሰማይ ቢመጣ
ከአዳም ዘር ከማርያም ብቻ ስለወጣ
አለቃ ነው ሲባል ደግሞም ጌትነቱን
ስላልተቀበሉት የአምላክ ልጅነቱን
አሰወግደው ብለው ፈረዱበት ሞትን
እንደወንጀለኛ በመስቀል ሰቀሉት
የሚይዘው መስሎአቸው ማህተም አተሙት
መቃብር እንደማይችለው ፍጹም አልተረዱት
በሶስተኛው ዕለት ሳያስቡት ድንገት
ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ በጠዋት
ከሞት ከተነሳ አርባ ቀን ቆይቶ
ለደቀመዛሙርቱ ሁሉን አስረድቶ
የጠፉትን ሁሉ ወደ እውነት መልሶ
ጊዜው ሰዓቱ ሲደርስ ሄደ ተመልሶ
ይመጣል ጌታችን በወሰነው ሰዓት
ቤትን አዘጋጅቶ ለዘለዓለም ሕይወት
ለጻድቃን ትንሳኤ ለኃጢያተኞች ሞትን
ይመጣል ጌታችን ለመወሰን ይህንን
በጌታዬ መምጣት እኔ ተስማምቼ
የዓለም ቅራቅንቦ ወደኋላ ትቼ
ራሴን በመናቅ ንስሐ ገብቼ
እየጠበቅሁ ነው እህት ወንድሞቼ
ምንስ አሰባችሁ ምንስ ተሰማችሁ
ጌታችን ሲመጣ ምንድነው ፍርዳችሁ
በግራ ነው በቀኝ እርሱ የሚያቆማችሁ
ይመጣል ጌታችን እኛኑን ሊወስደን
ለምንጠብቀው በኢየሱስ ተማምነን
           በቸር ይግጠመን!!
           ኃይሉ ነኝ!


Saturday, March 2, 2013

ጌታ ሆይ ቶሎ ና!!


    ጌታ ሆይ ቶሎ ና!!

ደቀመዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ እርሱ ቀርበው

“ይህ ሁሉ ነገር የሚሆነው መቼ ነው ?የመምጫህና

የዘመኑ መጨረሻ ምልክትስ ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት

                             ማቴዎስ 24፡3

 

የትንቢት አዋጆች ሁሉም ተፈጽሞአል

የመጨረሻው ዘመን በፊታችን ሆኖአል

የጎርፍ ሙላቱ የምድር ሙቀቱ

በነዚህ ምክንያት የሰው ልጅ ቅስፈቱ

የዓለም መናወጡ በየስፍራው ጥፋት

አንደኛው በአንዱ ላይ በጦር መነሳሳት

እዚያም እዚህም ወንጌል ይሰበካል

የዳነው ድኖአል ያልዳነው አምጾአል

አመጸኛው ደግሞ ወንጌሉን አጣሞአል

ለራሱ አምላኩ እኔ ነኝ ብሎአል

መጭው ክርስቶስን በራሱ መስሎአል

አምላክ ተብሎ ይሰገድለታል ይመለክለታል

በዓለም በምድራችን ደግሞም በአህጉራችን

የሀሰት ክርስቶሶች ሲፈሉ እንደአሸን

ሰማን በጆሮአችን አየን በዓይኛችን

በየአደባባዩ በተቀደሰ ሥፍራ

ስለአምላክ ነገር አንድም ሳይፈራ

ርኩሰት በዝቶአል ድሪያ አመንዝራ

ዘመኑ ከፍቶአል ለእህምሮ ይከብዳል

የእግዚኣብሔርን ትህዛዝ ሕጉን አቃለዋል

አምላክን በመናቅ ይጋባል ያጋባል

ሁኔታውን ሁሉ ስንመረመር ሚስጢሩን

የክርስቶስ ኢየሱስ መምጫው መቃረቡን

በዚህ ይታወቃል በጫፍ ላይ እንዳለን

ዘመኑ የሰላም ነው እየተባለ ሲባል

ድርቅና ቸነፈር ምድርን አስቸግሮአል

የአውሎ ንፋሱ ዓለምን ሲያስጨንቀው

በደጅ እንደቀረብክ ምልክቱ ይህ ነው

ያለመተማመን ደግሞም መከዳዳት

የበሉትን በልተው እርስ በእርስ መጠፋፋት

ጌታ ሆይ!! ይመስላል የምትመጣበት ሰዓት

ወንጌል ተነግሮአል ትንቢቱም ተፈጽሞአል

በቃልህ እንዳዘዝከን ዓለምን ዞረናል

ትህዛዛትህንም ሁሉ ፈጽመናል

የመምጣትህ ነገር በጣሙን ናፍቀናል

ማራናታ እያልን በፊትህ እንጮሃለን

ጌታ ሆይ! ቶሎ ና እኛም እናርፋለን።

                በቸር ይግጠመን!!

                 ኃይሉ ነኝ! Feb,2013

 

Friday, March 1, 2013

ማነው ባለተራ?


ማነው ባለተራ?
በእምቢልታ በገና በውዳሴ መዝሙር
ምስጋና ለማቅረብ ለእግዚኣብሔር ክብር
ብሎ የተነሳው ትንቢተ ኢሳያስ
በቤተመቅደስ ውስጥ ጸሎቱን ሲያደርስ
እግዚኣብሔር በክብሩ ተቀምጦ ሳለ
ኢሳያስ በፍርሃት እንደዚህ ብሎ አለ
በበደሌ ምክንያት ደግሞም በኃጢያቴ
በበዳይ ሕዝብ መካከል እኔ መገኘቴ
እግዚኣብሔርን ደግሞ በዓይኔ በማየቴ
አለቀልኝ በቃ አልኖርም በሕይወቴ
እንደዚህ በማለት ኢሳያስ ሲቃትት
የሠራዊት ጌታ ይህንን በመመልከት
መላእክቱን ላከ ከሱራፌል አንዱን
የኢሳያስ ከንፈር የተቀደሰ እንዲሆን
ሱራፌልም ደግሞ ይዞ የፍም እሳት
በጉጠት አድርጎ አፉን በማስነካት
ኢሳያስ ነፃ ሆነ ከበደል ከኃጢያት
እኔኑን በድለው በጥፋት ውስጥ ላሉት
ኃጢያትን በመስራት በሞት ለሚጠፉት
ማንን እልካለሁ ማንስ ይሄድልናል
ይህንን የሚፈጽም ሰው ያስፈልገናል
ይህንን ጥያቄ እግዚኣብሔር ሲናገር
ኢሳያስ የመለሰው ያኔውኑ ነበር
በአገሬ በምድሬ ነጋሪ በማጣት
ወደሞት እየሄደ  እየጠፋ በኃጢያት
ወንድሜና እህቴ አባቴና እናቴ
በቅርቡም በሩቁ የእኔ ጎረቤቴ
ተመለስ የሚለው ከሞትና ከኃጢያት
ሰው ስላላገኘ ወንጌል የሚሰብክለት
የመንግሥቱን ወንጌል ነጋሪው በመርሳት
ወይ እኔ ከተረፍኩ ይበቃል በማለት
ስንቱ በሞት ሄደ ሳናስበው ድንገት
ወንጌል ተሸክሞ ከምዕራብ ተነስቶ
እስያ አፍሪካ አውሮፓን አካቶ
የምሥራቹን ቃል ተናግሮ አስረድቶ
እስከዛሬ አለ ሕይወት ያህል ሰጥቶ
ዛሬም አላቆመ ስራውን ይሰራል
ለደከመው ጀግና ማንስ ይተካዋል
ለነፍሳት ግድ ብሎት የሚጨነቅ ማነው?
ጌታ ሲናገረው ግልጹን ሲያስረዳው
ማንን እልካለው ማን ይሄድልኛል?
ብሎ ሲጠይቀው በተግባር የሚያውል
ዳገት ቁልቁለቱን ሞትን ሳይፈራ
መስቀል ተሸክሞ የሚወጣ ተራራ
ለጌታ የሚላክ ማነው ባለተራ?
ወንጌልን ለማድረስ የትውልድ ባላደራ
እኔ ወይስ አንተ ማነው ባለተራ?
እኔ ነኝ ባለተራ የሕዝብ ባላደራ
ለመስራት የቆረጥኩ የጌታዬን ሥራ
ይዤ መመሪያዬን የመዳን ወንጌልን
የጠፋው ወገኔን የማድንበትን
ለንስሐ ተዘጋጅ ብዬ የምልበትን
እኔ ነኝ ባላደራ ተረካቢ ትውልድ
ለሕዝቡ ለመድረስ ታሪክ የሚለኝ ግድ
ተራው የእኔ ነው ተራው የአንተ ነው
ተራው የሁላችን የአበሻ ሕዝብ ነው
         በቸር ይግጠመን!!!
        ኃይሉ ነኝ!  Nov 2009

Tuesday, February 26, 2013

ጽጌረዳ



ጽጌረዳ
ጽጌረዳ የአበባ ውብ
ከሩቅ ወደእሷ የምትስብ
ሮዝ ቀይ ጃኖ ለብሳ
በአጋም መካከል ተኮፍሳ
ወደ እርሷ ልጠጋ ወድጄ
ልዳስሳት ልነካት በእጄ
መስሎኝ ሳያት ፤ እሾህ ያላት
ብዙ ራቅኳት ፤ ተለየኋት
ጽጌረዳ ጣፋጭ ስዊት
 የአበቦች ዓለም ንግሥት  
ውብ መዓዛ ያላት ለዛ
ዘመን የሚያመጣውን አይቼ
ከዘመን ጋር የሚሄደውን ሸኝቼ
የጀርባዬን እኔነቴን ተመልክቼ
ቁጭ ብዬ ባለሁበት ሰዓት ተዝናንቼ
በአበባ መካከል ቁጭ ብላ
ከፊት ከኋላ ኖሯት ከለላ
ፅጌረዳን አየኋት አገኘኋት
እንዳልርቃት ከአደይ አበባዬ ጋር ናት
እንዳልተዋት እንዳልረሳት ታስጎመጃለች
ፍሬ አላት አበባ ነች
ራስዋን ቀና አድርጋ
ፅጌ ረዳ ሆና የበጋ
ፈገግታዋን እያሳየች
እንዲህ አለች
ትወስደኛለህ !!?? አለች
አትወስደኝም ዳግም ተናገረች
እንደ ውዳሴ ማርያም እየደገመች
የማልሸኛት እርሷ መስሎአት
እኔም አልኳት ልቤም አላት
የውስጤን የልቤን ነገርኳት
አንቺን ያልወሰድኩሽ
የልቤ የውስጤ ያላደርግኩሽ
ፅጌረዳዬ ብዬሽ
ከአበቦቼ መካከል አስቀምጪሽ
ጠዋት ማታ ታቅፌሽ
በአደባባዬ ተክዬሽ
ለፍሬ ለአበባነት አድርሼሽ
ለቤቴ ውበት ሰጥተሽ
የእኔ የራሴ አድርጌሽ
እኖራለሁ ከአንቺጋር
ውበትሽ ሳይከስም በክብር
ይህንን ገልጪ ብነግራት
እኔ ቋንቋ አላውቅም በማለት
እየጣረች ነው እንዳልወስዳት
በምን ቋንቋ ላስረዳት
የመውሰድ ትርጉሙን ትጠይቃለች
እያስረዳች ፤ ግን ትሰነጣጥቀዋለች
እንጨት ይመስል ትፈልጣለች
ፊደል ቋንቋውን ትናገራለች
ከፋ ይሁን ሔረርጎታ
ምናልባትም አሳይታ
የበቀለችበት ቦታ
ቤተልሔም ይሁን ናዝሬት
ፊደል ሐዋርያ የቆጠረችበት
እኔ ከቋንቋ ምን አለኝ
ከቀዬ ምን ሊተርፈኝ
እኔ የምፈልገው ፅጌረዳነት
ከምትሰጠው መሀዛ ውበት
ፅጌረዳዬን በአበባዬ መካከል አድርጌአት
በዓይኔ ሸኘዋት አደረስኳት
እንዳለችው አልወሰድኳት
በእቅፌ አላደረግኳት
ልቤ ግን ተከተላት
 ከአበቦች መንደር አደረሳት
ብቻ ብቻ ልቤ ተረዳት
ውሰደኝ ካለች ልውሰዳት
በቸር ይግጠመን!!!
ኃይሉ ነኝ August 12/2006

የኃይሉ ማስታወሻዎች HEG: ጩኽቴን ማን ይስማው?

የኃይሉ ማስታወሻዎች HEG: ጩኽቴን ማን ይስማው?: ጩኸቴን ማን ይስማው ? ከአምላኬ በታች አባት አለኝ የምለው የወለደኝ አባት ወይ እረኛዬ ነው ችግር ቢበዛብኝ ግራ ግራ ብሆን ሊለግሰኝ ብዬ እንዲነግረኝ ምክሩን ስልክ ደውዬለት ቀጥሮ ብጠይቀው ቃል እንዲያካፍለኝ ነገሬን ብ...

ጩኽቴን ማን ይስማው?


ጩኸቴን ማን ይስማው ?
ከአምላኬ በታች አባት አለኝ የምለው
የወለደኝ አባት ወይ እረኛዬ ነው
ችግር ቢበዛብኝ ግራ ግራ ብሆን
ሊለግሰኝ ብዬ እንዲነግረኝ ምክሩን
ስልክ ደውዬለት ቀጥሮ ብጠይቀው
ቃል እንዲያካፍለኝ ነገሬን ብነግረው
ዛሬ አይመቸኝም ነገ ነገ ሲለኝ
ነገ ነገ ወልዶ ነገ ቢበዛብኝ
የነገ ሲገርመኝ ሳምንት አሳለፍኩኝ
ሳምንት አሳልፌ ወርን  አጋመስኩኝ
የተጨነቅኩበት አውጥቼ ከአንደበቴ
የተቸገርኩትን የውስጤን ከአንጀቴ
ለጩኸቴ ምላሽ ካልሰጠኝ አባቴ
የሚያስፈልገውን ምክሩን ካልለገሰኝ
አባት ለአባትነት የሥጋ አባት አለኝ
ጩኸቴን ካልሰማው ጉዳቴን ካላየው
ከተቀደሰው ቃል ለልቤ የሚያሻው
ተናግሮ አስተምሮ ልቤን ካልመለሰው
አባቴ ካልሰማኝ ጩኸቴን ማን ይስማው ?
                             በቸር ይግጠመን!!!
                       (2009) ኃይሉ ነኝ!!