Thursday, March 14, 2013

ለኢየሱስ ቀላል ነው


             ለኢየሱስ ቀላል ነው
ሁለቱ ማርያሞች በአንድነት ሆነው
የከበረ ሽቶ በዋጋቸው ገዝተው
የጌታን ሬሳ ሊቀቡት ፈልገው
የናርዶሱን ሽቶ በጉያቸው ይዘው
በአትክልቱ ውስጥ በመቃብሩ ሥፍራ
ሳይሽቀዳደሙ ሆነው በአንድ ተራ
መጡ ወደ መቃብሩ ከሰሎሜ ጋራ
ገና ከቤታቸው ሳሉ ከመንደራቸው
እንዲህ ተባባሉ እርስ በራሳቸው
በልባቸው ሆኖ ያብሰለሰላቸው
ሲገምቱት ደግሞ በጣም የከበደው
ረዳት ለማግኘት አወጡት ካፋቸው
እኛ ሶስታችንም ፍጹም የማንችለው
የመቃብሩ ድንጋይ ሐውልት የመሰለው
ሽቶውን እንዳንቀባው ተደንቅሮ ያለው
የመቃብሩን ደጃፍ መግቢያውን የያዘው
ወደውስጥ እንድንገባ ማነው ሚያንከባልለው?
ድንጋዩን  ለማንሳት ማነው የሚችለው ?
ይህንን ተናግረው ጉዞአቸውን ቀጥለው
ወዲያውኑ ሲደርሱ ከመቃብሩ ሥፍራ
በሃሳብ ሲገምቱት የሆነው ተራራ
ድንጋዩ ተንከባሎ
ደጃፉንም ጥሎ
ከሥፍራው ላይ ጠፍቶ
ተገኘ ትከፍቶ
ነገራችሁ ሁሉ የሆነ የሚያስፈራ
ችግርና ሀዘን እንዲሁም መከራ
ያልቻላችሁት ነገር ልትሰጡት አደራ
እንደሚከብድ ድንጋይ የተጫነባችሁ
ፊት ለፊት ለግጥሚያ የተጋረጠባችሁ
ገለል በል ብትሉት አልርቅም ያላችሁ
ጌታን ተማጸኑት ድል ታገኛላችሁ
ችግሩ ሲጠፋ በውን ታያላችሁ
ለመክፈት ለመዝጋት ስልጣን በእጁ ያለው
ሸክምን ለማራገፍ ለኢየሱስ ቀላል ነው።
                    በቸር ይግጠመን!!
                    ኃይሉ ነኝ!

እኔም አልፈርድብሽም!!

                              እኔም አልፈርድብሽም
      “እኔም አልፈርድብሽም  በሚለው ዓረፍተ ነገር ውስጥ አንድ ባለቤትና አንድ ማሰሪያ አንቀጽ ወይም ግስ አለው ። በሌላ አባባል ደግሞ ሁለት አካላት እንዳሉ የአማርኛችን የሰዋሰው አወቃቀር ይገልጸዋል። እኔም የሚለው ባለቤት ፈራጅና ምሕረት ሰጪና በሌላ ጎኑ የሚፈረድባት ወይም ምሕረት የተሰጣት በዚህ ዓረፍተ ነገር ውስጥ እናገኛለን ። ይህንን ርዕስ ያመጣሁት ቀጥታ ከዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 8 ሲሆን ፤ጌታ ኢየሱስ በማለዳ በጠዋት ሕዝቡ በዙሪያው ተሰብስበው ወንጌል እያስተማራቸው ነበር። ከሳሾች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን አንድ ስታመነዝር የተያዘችን ሴት ይዘው ፤ጌታ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር በመተባበር እንዲፈርድባት ወደእርሱ አመጡአት ። የሙሴ ሕግ አዋቂዎች “አባታችን ሙሴ በሰጠን ሕግ ላይ ማንም ሰው ሲያመነዝር የተያዘ በሞት ይቀጣ   ብሎ አዞአል። እኛ ደግሞ የሕጉ ባለአደራዎች ስለሆንን ኃጢያት ሲሰራ ዝም ብለን ማየት ስለማንችል በሕጋችን መሰረት መገደል አለባት ።ሙሴ ያዘዘው ትህዛዝ ይህችን ሴት ለብቻዋ ጉዳዩ ይመልከታት አይመልከታት ሳይገናዝቡ ነበር ይዘዋት የመጡት፤ምክንያቱም ሕጉ በተለያየ ሁኔታ ስለሚገልጸው አንተስ ስለዚህች አመንዝራ ሴት ምን ትላለህ? ብለው ጌታ ኢየሱስን ጠየቁት። ጌታ ኢየሱስን ሊፈትኑት በሌላ ጎኑ ተባባሪ ሊያደርጉት እንዳሰቡ ተገንዝቦ ። የሰውን ልጅ ከሕግና ከኃጢያት ነፃ ለማውጣት ወደዚህ ምድር የመጣው ጌታ ኢየሱስ ጎንበስ ብሎ መፃፍ ጀመረ ። በቃ እሱም እንደኛ ጥቅሱን ጠቅሶ ሊፈርድባት ነው ብለው እርስ በእርሳቸው ሲጠቃቀሱ ፤ ጽሁፉን ጽፎ ጨርሶ ሲነሳ “ከእናንተ መካከል ኃጢያት የሌለበት በመጀመሪያ አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት  አላቸው ። የተጻፈውን ጽሑፍ ሲያነቡ ሐፍረታቸውን ተከናንበው አንድ በአንድ ቦታውን ለቀው መሄድ ጀመሩ። ጻድቅ ነን ብለው የሚኮፈሱት የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ድንጋዩን በመጀመሪያ ከማንሳት የተቆጠቡት ኃጢያት መስራታቸውን የራሳቸው ሕሊና ስለፈረደባቸው ነው።እኛስ በአንድ ቤተስብ ኑሮ ፤ትዳር  ፤አገልግሎት ላይ የመጀመሪያውን ድንጋይ አንስቶ ለመወረውር ቅዱስ ነን?     
      ባለፈው ዓመት ከሥራ ወደቤት ለመመለስ ዳውን ታውን (Down Town) ባቡር ስጠብቅ ፤ አንድ በቅርብ ሩቅ የማውቀው ባቡር ጣቢያ ተገናኝተን ሰላምታ ከተሰጣጣን በኋላ ፤ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን አላይህም ምነው አገልግሎትም ቀረ እንዴ? ብዬ ጠየቅሁት ። ጌታ ሲፈቅድ እጀምራለሁ አለኝ ። ምነው ብዬ አጥብቄ ብጠይቀው ሁኔታውን ገልጾ ነገረኝ ። ሁኔታውን ካዳመጥኩት በኋላ “ የእኔ ወንድም አንተ እንደነገርከኝ በተመሳሳይ ሁኔታ እኔም ችግር ደርሶብኝ ነበር ። ቅስሜ ተሰብሮ ሞራሌ ደቆ ሞት እስከሚያስመኘኝ ድረስ ተስፋ ቆርጪ ነበር ። የፈራጆችን ፍርድ ቁብ ሳልሰጣቸው ። በቤተ ክርስቲያን ተሳትፎና አገልግሎት ቀጠልኩኝ የጠላቴ ሽረባ እንዲወገድልኝ በጾምና በፀሎት ተጋሁኝ ያ እንደጉም ጨፍግጎ የያዘኝ ችግር ብንን አለ ይህው እንደምታየኝ ዛሬም በጌታ ቤት አለው ። ወንድሜ ሆይ! ጠላትን ማሸነፍ የምትችለው በእንደዚህ መንገድ ነው አልኩት ። በጉዳዩ ተስማምተን ሁለታችንም በየፊናችን ሄድን።  
      የእግዚኣብሔር ቃል “ ይቅር በሉ እናንተም ይቅርታን ታገኛላችሁ” ይላል ። ሁልጊዜም አንድ ሰው አጠፋ፤ ኃጢያተኛ ነው ፤ ወንጀለኛ ነው ፤ የውሸት ክርስቲያን ነው እያልን ለመፍረድ ይዳዳናል ያ ደግሞ ሚስጢር ነው ለማንም አትናገር በሚል የውሸት ካባ እንደ ሙሴ የሕግ ሰዎችና እንደፈሪሳውያን የምንፈርድባቸው ብዙዎች ነን እንደዚህ ከሆነ የክርስቶስ ተከታይነታችን በምን ይገለጻል ። እንዲያውም ያንን ሰው በጌታ ፍቅር መክሮና ወደንስሐ እንዲመጣ ማበረታታት እንጂ ጭራሹኑ ከጌታ ቤት እንዲወጣ መገፋፋት ተገቢ ነው?!! ያ ሰው ለእኔና ለአንተ ጌታ ኢየሱስ እንደሞተልን ለርሱም ሞቶለታል ። ጴጥሮስ ወደ ጌታ ኢየሱስ ቀርቦ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው ሰባት ጊዜ ነውን ብሎ ጴጥሮስ ለማረጋገጥ  ሲጠይቀው አይደለም አለ ጌታ ኢየሱስ ሰባት ጊዜ ሰባ ነው አለው እዚህ ላይ እንደምንመለከተው እንዲያውም የተበደልን ብንሆን እንኳን ሰባ ጊዜ ሰባ ይቅር በሉት ነው የሚለው ስለዚህ የጌታ ኢየሱስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን ጥፋት አጥፍተዋል የምንላቸውን ሰዎች ይቅርታ በማድረግ ልባቸውን ወደጌታ እንዲመለሱ ብናደርግ መዝገባችን በሰማይ ይጻፍልናል ። ጌታ ኢየሱስ እንዲሰቀል የሚፈልጉት የካህናት አለቆች ነበሩ ። ሌላው በቄሳራዊው ጴላጦስ አደባባይ ቆመው ስቀለው!! ስቀለው!! ብለው የሚጮሁት ግማሹ ከአምስት ሺ ተመጋቢዎች ውስጥ ነው፤ ሌላው ፈውስን ከጌታ ኢየሱስ የተቀበለ ነው ፤ ቢያንስ ቢያንስ ታአምራት ሲደረግ አይቶአል። የእነዚህን ስዎች ሁኔታ ስንመለከት በደፈናው የሚያደርጉትን የማያውቁ ብቻ ስቀለው ስቀለው የሚሉ ናቸው ። መሐል ሰፋሪ የሆኑት አንዳንዶቹ የመንደር ሰዎች ገፋፍተዋቸው የመጡ ናቸው ። አንዳንዱም እንደይሁዳ የመጮያ ገንዘብ ተከፍሎት ነው ። የውስጥ ሚስጥሩን አያውቁም ብቻ ስቀለው ስቀለው ይሉ ነበር። ኃጢያት የሰራውን ያንን ሰው ስቀለው ስቀለው እያልን ከጌታ ቤት ከምናስወጣው በፍቅር ተቀብለነው በኃጢያቱ ተናዞ በቤቱ እንዲኖር ብናደርገው የእግዚኣብሔር ቃል እንደሚናገረው ገንዘብ አደረግከው ስለሚል የእግዚኣብሔርን መንግስት ያሰፋን ይመስለኛል። ነገር ግን ምንም ምክንያት ሳይኖረን ስቀለው ስቀለው የምንል ከሆነ ለእኛም አስቸጋሪ ዘመን ሊመጣብን ይችላል ። ለማንኛውም በሰው ፊት እንደምንታየው ጻዴቅ መምሰል ሳይሆን ሕይወታችን፤ ኑሮአችን ፤ ስልካችንና አነጋገራችን የተቀደሰ ሊሆን ይገባል ። እንዳይፈረድባችሁ በማንም ላይ አትፍረዱ ብሎ ጌታ ኢየሱስ እንዳስተማረን ። በሁሉም ነገር ላይ ፈራጅ ሆነን ሳለ ድንገት ጌታ ኢየሱስ ቢመጣ የተመካንበት ጽድቃችን ከንቱ እንዳይሆን እንጠንቀቅ!!!
                                                                         በቸር ይግጠመን!!
                                                                             ኃይሉ ነኝ     
   

Wednesday, March 13, 2013

ፍቅራችሁ ያለግብዝነት ይሁን!!


              ፍቅራችሁ ያለግብዝነት ይሁን!!
     ይህ ዓረፍተ ነገር የተገለጸው በሮሜ መጽሐፍ ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በጻፈው መልእክት ውስጥ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ሊያስረዳቸው የፈለገው ፍቅራችሁ እርስ በርሳችሁ፤አንዱ ለአንደኛው የሚወድበት ፍቅር እውነተኛ ፍቅር ይሁን ለማለት ነው። ያ ፍቅር ያለግብዝነት ይሁን ይላል ። ግብዝነት ምንድን ነው? ሳባ የአማርኛ መዝገበ ቃላት እንዲህ ይላል “ለራሱ የሚያደላ ፤ ይሉኝታ ቢስ ፤ ሰነፍ ሲለው ፤የከሳቴ ብርሃን ተሰማ መዝገበ ቃላት ደግሞ ቁም ነገር የሌለው ይላል። ጌታ ኢየሱስ ደግሞ እኔ እንደወደድኳችሁ እርስ በራሳችሁ ተዋደዱ ብሎ ሕግ ደንግጎ አስቀምጦልናል። ጌታ ኢየሱስ በምን ዓይነት ፍቅር ወደደን? በግሪክ ቋንቋ ፍቅርን በሶስት ዓይነት መድበውታል ወይም ለሶስት ዓይነት የተለያየ ፍቅር ሶስት የተለያየ ስም ሰጥተውታል። ኤሮስ ፤ ፊሊያ ፤ አጋፔ ግሪካውያን ሁለቱን ለተለያየ የፍቅር ዓይነት ሲጠቀሙበት ፤ አጋፔን ግን ለእውነተኛ ፍቅር እግዚኣብሔር የሰውን ልጆች የወደደበትን ፍቅር ለመግለጽ ይጠቀሙበታል። “ዓለምን እጅግ ስለወደደ፤ አንዲያ ልጁን ሰጠ በዮሐንስ 3፡16 እንደተገለጸው እጅግ ስለወደደ ይላል ። እጅግ ለምትለው ቅጽል ቃል የከሰቴ ብርሃን መዝገበ ቃላት “እጅግ የበዛ፤ ውስጠ ብዙ ልክ የሌለው ። አደገ፥ በዛ ክልክ ዐለፈ ብሎ ያፍታታዋል።እግዚኣብሔር ከልክ ባለፈ ልክ በሌለው ፍቅር ነው የወደደን ማለት ነው ። እግዚኣብሔር አንዲያ ልጁን ጌታ ኢየሱስን በመስቀል እስኪሞት ድረስ ያሳየን ፍቅር ነው ግሪኮች አጋፔ የሚሉት፤ ጌታ ኢየሱስም እኔ እንደወደድኳችሁ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ ሲል ከልክ ባለፈ ፍቅር እርስ በእርሳችን እንድንዋደድ ነው ምሳሌ አድርጎ ራሱን ያቀረበው። ጌታ ኢየሱስ እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ ብሎ አላቆመም። ወንድማችሁን እንደምትወዱ ጠላታችሁንም ውደዱ ብሎአል። ፍቅር እውነተኛ ሆኖ የሚገለጸው ወንድምን እንደራስ ሲወዱ ነው ። አደባባይ ላይ ፍቅርን በተከሸነ ቃላት መግለጽ ይቻላል ፤ ወንድሜ! ወንድሜ! እያሉም ጉንጭና ትክሻን በመሳም ለታይታ ልናደርገው እንችላለን ። ግን ያ አይደለም ዋናው ነጥብ ወንድሜንና እህቴን በእውነተኛው ፍቅር፤እንደራሴ ወድጃአለሁ ነው።በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 10 ላይ ስለደጉ ሳምራዊ ጌታ ኢየሱስ ያስተማረው ምሳሌ አንዳንዶቻችን ከልጅነታችን ጀምሮ ተምረነዋል እናውቀዋለን። አንድ ሰው ወንበዴ አግኝቶ እንደበደበውና ፤ካህኑ በእግዚኣብሔር ቤት የሚያገለግለው ቅዱስ ነን ፤እኛ የእግዚኣብሔር ምርጦች ነን ፤ አንዳችም ኃጢያት የለብንም ከሚሉት አንዱ በዚያ በኩል ሲያልፍ  አይቶ እንዳላየ አለፈ ፤የሲቃ ጩኽቱ ወደልቡ ሊደርስ አልቻለም ። እንባው አልተሰማውም አለፈ መንገዱን ቀጠለ። ቀጥሎ በእግዚኣብሔር ቤተ መቅደስ ዕጣን የሚያጥነው ሌዋዊ እርሱም በዚያ ሲያልፍ የድረሱልኝ ድምፅ ወደ ጆሮው ገባች፤ ዓይኑን አሻቅቦ ቢያይ በደም የተበከለና መሐል መንገድ ላይ የተጋደመ ሰው መሆኑን ተረዳ ዓይኑን ጨፍኖ መንገዱን ነጎደ። አንድ ሳምራዊ ግን አነስተኛ ምናምንቴ የሆነው በዚያ በኩል ሲያልፍ ሞትኩኝ ድረሱልኝ የሚል ለቅሶ ሰማ ይህ ሰው መሆን አለበት ማየት አለብኝ ብሎ ተጠጋው ሲያየው ወንበዴዎች እንዳይሞት እንዳይሽር አድርገው የደበደቡት ምስኪን መሆኑን ተረዳ፤ ገንዘቡ፤ የሚጓጓዝበት አህያ ተወስዶበታል። የለበሰው ልብስ እንኳን ሳይቀር የለም ወንበዴዎቹ ወስደውታል። መጀመሪያ ሳይጸየፈው ደሙን ጠርጎ በዘይትና በወይን ጠጅ ቁስሎቹን ጠግኖለት በፋሻ አሰረለት። የራሱን አህያ ሰጥቶት ። ወደእንግዶች ማደሪያ ቤት ወሰደው ፤ እዚያም የሚገባውን ከፍሎ በሆቴል ቤት ውስጥ እንዲያርፍ አደረገ ፤በስተመጨረሻም ሁለት ዲናር ከፍሎለት እስኪያገግም በእንግዶች ማረፊያ እንዲቆይ አደረገ ያ ብቻ አይደለም ተጨማሪ ወጪ ቢኖርበት እንደሚከፍል አረጋግጦ ። ወደ ሚሄድበት ሄደ። ጌታ ኢየሱስ ለሰውዬ እንደጠየቀው እኛም ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባናል ለወንድሜ ምን ያህል ፍቅር አለኝ? የተራበውን ወንድሜን ወደቤቴ ግባ እሳትም ሙቅ ብለው ምን ይጠቅመዋል አይደል ያለው የእግዚኣብሔር ቃል። በእርግጥ ወንድሜን እንደራሴ እወደዋለሁ? ዋናው ጥያቄ ይህ ሲሆን መልስ ልንመልሰው የሚገባ ነው ። ወንድሜን እንደራሴ ካልወደድኩት ራሱ ግብዝነት ነው ግብዝነት ደግሞ እንደጌታ ኢየሱስ ትህዛዝ ወንድሜን አልወደድኩትም ማለት ነው ። ጌታ ሲመጣ እናንተ ያባቴ ብሩካን ልንባል እንፈልጋለን!! ወንድሜንና እህቴን በእውነተኛ ፍቅር ልንወዳቸው ይገባል!!።
                                                  ቸር ይግጠመን!!
                                                  ኃይሉ ነኝ!!         

Sunday, March 10, 2013

ይሻለኛል!


                ይሻለኛል!
ጌታ በማይፈቅደው መንገዱ ከሰፋው ፤
ሕይወት ከማይገኝበት ሞት ብቻ ከሆነው።
ሰላም ከሌለበት ፤ ከሌለበት ዕረፍት
ይሻለኛል እኔ የክርስትና ሕይወት
ከፍልስጤም ጎራ ጠላት ከበዛበት
ፀጉርን ከሚያስላጭ ከደሊላ ምቾት
ዓይንን ከሚያስወጣ ከፍልስጤም አገር
ይሻለኛል በክብር ከኢየሱስ ጋር መኖር።
ከጶጥፋራ ቤት ጮማ ከሞላበት
ሽንኩርትና በጥሁ የአትክልት ዓይነት
እነዚህን በሙሉ ለሰውነት ምቾት
ተትረፍርፎ ቢገኝ ኃጢያትን ለመስራት
ጌታን በማሳዘን ከመኖር በኃጢያት
ይሻለኛል እኔ ከጌታ ጋር ሕይወት
አልጋ ወራሽ ሆኜ በግብፅ ቤተ መንግሥት
ከፈርዖን ዙፋን ጌታ ባልነገሰበት
የፈርዖን ልጁ ወራሽ ነው ከምባል
ከጌታ ጋር ሆኖ መሰደድ ይሻላል
ኃጢያትና ርኩሰት ከሚደረግበት
ከጥፋት ከተማ ሞት ካንዣበበት
ከሶዶም ጎመራ ወርቅ አልማዝ ካለበት
ይሻለኛል ጌታ ትርፍ ባይኖርበት
ዓለም ከምትሰጠው ምቾትና ድሎት
ብዙ መቀማጠል ግን ባዶ ከሆነበት
ሁሉም ነገር ኖሮኝ ከጌታ ከምርቅ
ይሻለኛል ኢየሱስ በተስፋ መጠበቅ
ለሥጋ ከሚመች ካለበት ብዙ ሀብት
ራሴን ለውርደት ሕይወቴን ከመስጠት
በኃጢያት አረንቋ ራስን ከመክተት
ይሻላል ኢየሱስ ከዘለዓለም ሞት
  
            በቸር ይግጠመን!!
             ኃይሉ ነኝ   

Friday, March 8, 2013

እኔ ግን ሞቻለሁ


እኔ ግን ሞቻለሁ
ጌታ ደግነቱን ማዳን ታምራቱን
ፍቅሩን ርህራሄውን ለጋስ ቸርነቱን
አባቶች ነግረውኝ ለእኔ አስተምረውኝ
በመስቀል መሞቱን ይህን ገልጸውልኝ
አረጋግጠው መክረው ስላስጠነቀቁኝ
መንገዱን መርጪ ጌታን ተከተክልኩኝ
በእርግጥ እንደሞተልኝ እኔም ስለተረዳው
መሞትን ፈልጌ ከዓለም ተለየው
ወደመስቀሉ ስር በእምነት ሲያደርስኝ
ድሬቶ ቡትቶ ቀድሞ የነበረኝ
ከላዬ ተገፎ ገደል ውስጥ ገባልኝ
መሞት እንደሚገባኝ በመሞት ወሰንኩኝ
ምንም ስለሌለኝ ከዓለም የማተርፈው
ከጌታዬ ጋራ እኔ ግን ሞቻለሁ
          በቸር ይግጠመን!!
          ኃይሉ ነኝ

አዲስ ነገር ይሆናል!!


አዲስ ነገር ይሆናል     

በሰላሳኛው ዓመት በአራተኛው ወር  
 የአይሁድ ምርኮኞች እያሉ በኬባር  
 የተነገረው ቃል በተግባር እንዲውል 
ብዬ የምናገር እግዚር እንዲህ ይላል   
እኔ የቡዚ ልጅ የሆንኩት ሕዝቅኤል 
ንጉሥ  ኢኮንያን በተማረከበት
በአምስተኛው ዓመት በአምስተኛው ዕለት
 በኬባር  ሸለቆ  ባለሁበት  ሰዓት    
 የእግዚኣብሔርን መንፈስ ከሰማየ ሰማያት
 በክብሩ  እንዳለ  እግዜርን  አየሁት 
 የእግዚኣብሔር መንፈስ  በእቅፉ እንደያዘኝ    
 እጅግ የደረቁ ብዙ አጥንት አሳየኝ   
  በተከማቹበት  ሸለቆ  አኖረኝ       
 እንደዚህ በማለት ጥያቄ ጠየቀኝ 
 እነዚህ አጥንቶች ሞተው የደረቁት
 በዚህ ሸለቆ ውስጥ ተከማችተው ያሉት
ዳግመኛ የሚያገኙ ይመስልሃል ሕይወት ?    
ይህንን ጥያቄ  እግዜር ሲጠይቀኝ       
  እንደዚህ ነበረ  መልሴን  የሰጠሁኝ    
አንተ ታውቀዋለህ  እኔ ምን አውቃለው   
 ገሎ የሚያድን ካንተ ሌላ ማነው?        
እግዚኣብሔር አምላክም ቃል እየነገረኝ                     
ለእነዚህ አጥንቶች እንደዚህ በል አለኝ                      
እኔም በታዘዝኩት ትንቢት ተናገርኩኝ 
መናገር ስጀምር ኮሽኮታ ሰማሁኝ
አጥንት ከአጥንት ጋር ሲያያዝ አየሁኝ
እጥንት በጅማት በሥጋ ሲሸፈን
 በቆዳ  ሲለበጥ ሙሉ አካል  ሲሆን
ይህ ተፈጸመ  እግዚኣብሔር ሲወስን
ቀጥሎም እንዲህ አለኝ
እግዚር ተናገረኝ
አካል ሙሉ እንዲሆን ያሻዋል እስትንፋስ
በአራቱም ማዕዘናት ተናገር ለንፋስ
ደግሞም በታዘዝኩት ትህዛዝ  መሰረት
ንፋስ  ግባ  ብዬ  ስናገረው  ትንቢት
ሕይወት የሌላችው ተጋድመው የነበሩት
እስትንፋስ አግኝተው  ሆኑ እንደሰራዊት
 ዘመን  አልፎልን   ሲመጣ   ዘመን
ድንቅን አይተናል  በደግ  አምላካችን
 ሳምንት በሳምንት በወር  በዓመታት
ጌታ ሰጥቶናል  ብዙ   በረከት
 በያዝነው ዓመት በምንጠብቀው 
የእግዚኣብሔር ሥራ እኛ የምንሰራው
መሥራት ያለብን እኛ ያልሰራነው
 ሥራውን ሊሰራ ሊያስተካክለው
የጌታችን ፈቃድ ዓላማው ያ ነው
በአዲሱ  ዓመት  አዲስ  ነገርን
ያደርጋል  ጌታ ውድ አምላካችን
            በቸር ይግጠመን!!!
          ኃይሉ ነኝ! Jan2009

ቀጠሮ እናክብር


ቀጠሮ እናክብር
ቀጠሮ ተቃጥሮ ነገር ለመቋጠር
ተስማምተን ስንሄድ በስልክ ስንናገር
ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ቀጠሮ እንዳይሻር
እንደአምላካችን ቃል ጊዜውን ለማክበር
ከወንድሜ ጋራ ተነጋግረን ነበር
ቃሉ እንደታመነ እንድንሆን ታማኝ
ልክ በሰዓቱ በሥፍራው እንድንገኝ
ለጊዜው ለሰዓቱ በአንድነት ተስማምተን
እንዳትቀር እንዳትቀር ብለን የተናገርን
በጌታ ፊት ነበር ሃሳቡን ያጸደቅን
አባቶች እንዳሉት ቀድሞ እንደተናገሩት
የተናገሩት ከሚጠፋ ይጥፋ የወለዱት
ቃል የእግዚኣብሔር ነው ብዬ
የያዝኩትን ፕሮግራም ሁሉ ጥዬ
የዕለቱን አጀንዳ በዚህ ላይ ጠቅልዬ
ወንድሜ በሰዓቱ እንዳይገኝ ቀድሞኝ
ቀድሞም በመድረሱ እርሱ እንዳያዝንብኝ
ልክ በሰዓቱ በሥፍራው ላይ ብገኝ
ብጠብቅ ብጠብቅ ምንም አላየሁኝ
ዓይኖቼን በሩቁ አሻግሪ ብቃኝ
ስልክም አልደወለ ስጠብቅ እንደሞኝ
በዓላችን ምንድነው? ዥንጉርጉር የሆነው
ትርጉም የማይሰጥ ግራ የሚያጋባው
ክርስቲያን ነን ብለን የክርስቶስ አገልጋይ
ቀጠሮ አለማክበር የምንሆን ወላዋይ
                    በቸር ይግጠመን!!!
                      ኃይሉ ነኝ! Jul 2008