Sunday, March 16, 2014

የመስቀል ወፍ

የመስቀል ወፍ
በአገራችን በምድራችን
በወንዛችን ተራራችን
ያኔ ሳንመጣ ካናዳ
እንደዛሬ ሳንሆን ባዳ
ለነገሩ ሳንሆን እንግዳ
በአበሾቹ ቀዬ መንደር
የምናስታውሰው ያለ የነበር
ዘመን አልፎ ሲመጣ ዘመን
ሁልጊዜም የሚታሰበን
በሕልማችን በሃሳባችን
በምናባችን የሚታየን
አሮጌው ዘመን አልፎ
አዲስ ዘመን አሸንፎ
ከዘመን ዘመን አልፈን
አዲስ ዓመት እውን ሲሆን
ሐምሌ ነሐሴ ክረምቱ
ሲያልፍ ጭጋግ ወራቱ
ያኔ በአገራችን በቀያችን
በገጠር ከተማ መንደራችን  
በአንድነት ሆነው ሴቶቻችን
የኮባ ግልድም አገልድመው
ፀጉራቸውን ሳዱላ ተሰርተው
ቅቤ በአደስ ተቀብተው
ወርቀ ዘቦ ካባ ደርበው
ተመራርጠው በዕድሜያቸው
ጎራ ከፍለው እንደእኩያቸው
እርስ በእርሳቸው
ሴቱ በአንድነት ሆነው
ዘመን ሲለወጥ በዕለቱ
 ሰው ከሰው ሳይገናኝ  በጠዋቱ
እማማና አባባ ሳይነሱ ከመኝታ
እንደተሰማ የወፍ ጫጫታ
ሳምንት ወር የተሟሸውን
በእሳት በቅቤ የቀለጠውን
ሴትዋ እየደለቀች  ከበሮዋን
ለተቀባያዋ ስታቀነቅን ዜማዋን
ታቅፋው አደይ አበባዋን
ቄጠማ አክርማውን
እንኳን አደረሳችሁ ለማለት
ሲሽከረከሩ በየሰዉ ቤት
ያዜሙ ነበር እንደዚህ በማለት
አበባዮሽ ለምለም
በአባብዬ ቤት ለምለም
ቁሙ በተራ ለምለም
አበባ ለምለም ወሸባ ለምለም
እንደርስዎ ጌታ የለም
ከብረው ይቆዩ ከብረው
ለዓመት ወንድ ልጅ ወልደው
ሰላሳ ጥጃ አስረው
ከብረው ይቆዩ ከብረው
ይህንን ብለው አዜመው
የመልካም ምኞት ገልጸው
ምርቃት ለሕዝብ ሁሉ ሰጥተው
ወር ሳምንት ሳይሞላው
ክረምቱን መውጣቱን አስልታ
የአደይ አበባውን መፍካት አይታ
የደመራውን እሳት ተመልክታ
ውብ ዜማዋን እያዜመች
መምጣቷን እየተናገረች
ትመጣ ነበር የመስቀል ወፌ
እንድኖር ክረምት ወጣ ብዬ አርፌ
ዛሬ ዘመን ቢያልፍም
ክረምቱ ቢፈጸምም
ብሩህ ሰማይ ቢታይም
 ፀሐይዋ እንኳንብትወጣም
ከዘመን ዘመን ብንሻገርም
ወፌን አላየዋትም
ወፌን አላያችሁም ወይ እንዳልል
ሁሉም ይናፍቃታል
ለራሱ ይመኛታል
መምጣቷን ይጠብቃል
ቢያያት ያከብራታል
ለሚስጢር ይፈልጋታል
 በቤቱ ያስቀምጣታል
ወፌ የዘንባባ ዝንጣፌ አላት
ሰላምን የምታበስርበት
ፍቅርን የምትገልፅበት
ብትመጣ ጊዜዋን ጠብቃ
እንደዚህ እላታልሁ በቃ
እነሆ ክረምት አልፎአል
ዝናቡ ቆሞ በጋ መጥቶአል
በየመስኩ ኣዳይ አበባ አብቦአል
የአበባው ሽታ ምድርን ሞልቶአል
የአዝመራው ጊዜ ደርሶአል
የመስቀል ወፌ ከሄድሽበት
ርቀሽ ከኖርሽበት
ድምፅሽን ልስማው
ዜማሽን ላዳምጠው ስላት
ብትሰማኝ ብትመጣልኝ ልንገራት
ወፌ የመስቀል ወፍ

ኃይሉ ገቢ Jan 7/2007

ዜግነት

ዜግነት
ገና በሕጻንነት ሳለሁ በት/ቤቴ
ፊደል አስቆጣሪዬ የት/ቤት አባቴ
የሕብረተሰቡ አካል እንዲሆን መሰረቴ
ፊደል አስቆጠረኝ እንዳውቅ ስለዜግነቴ
አስተማሪው ሲያስተምረኝ
እንደዚህ  ብሎ አለኝ
ደሙን ያፈሰሰ ልቡ የነደደ
በአገር ፍቅር ስሜት ጠላት ያስወገደ
ጠላትህ መሀይምነት ነው
ሕዝቡ እንዳያውቅ ያደረገው
ባለጋራህ በሽታ ነው
ሕዝቡን በሞት የሚቀስፈው
አንተ ተምረህ ካስተማርከው
ዜግነት ማለት ያ ነው
ዜጋ ዜግነት የሚባለውን
የአገር መሰረት የሆነውን
እንደ ማህተሜ በጉያዬ
በደረቴ ላይ አንጠልጥዬ
 አስተማሪው ባስተማረኝ
ዜግነትን ስለተረዳሁኝ
በስርዓቱ ስለሄድኩኝ
ሕዝቡን  ስላስተማርኩኝ
አቅጣጫውን  ስለነገርኩኝ
በሽታውን ታምሜ ቁስሉን ስለጠገንኩኝ
የሚራበውን ተርቤ ሕዝቡን ስላስተማርኩኝ
አንዱ መጥቶ ሲያስረኝ
ሌላው ደግሞ ሲፈታኝ
ዘመኔን አሳለፍኩኝ
ዜጋ እሱ ብቻ መሰለኝ
ዜግነት እንደሌለኝ ቆጠርኩኝ
 ስለዚህ መናገር  ካልቻልኩኝ
ሕዝቡን ካላስተማርኩኝ
የቁም እስረኛ ከሆንኩኝ
ዜግነትን ከተገፈፍኩኝ
አገሬን የማገለግልበት ሰዓት
እስኪ መጣ የምፈለግበት ዕለት
ለአገሬ አንድ ቀን ብቆይላት
ይህንን ከልቤ ጋር አስቤበት
ሄድኩኝ ወደ ባዕድ መሬት
የደረስኩበት ምድር
አሁን የምኖርበት አገር
እትብቴ የልተቀበረበት
ዘር ምንጅላቴ የልኖረበት
የዘር ዐረጌ የሌለበት
ሰጠኝ የመኖር ነፃነት
ስናፍቀው የነበረው ዜግነት
ተምሬ እንዳስተምር
ሰርቼ እንድከብር
ከአንዱ ቦታ ወደ አንዱ ለመዘዋወር
በነጻነት በሁሉም ቦታ እንድኖር
አለኝ ነጻነት የተሟላ
ሥራ ቢሆን ከለላ
        ምን ያደርጋል !!!
ሁሉም ነገር ቢሟላልኝ
ተትረፍርፎ  ሁሉን ባገኝ
የሰላም አየር ብተነፍስ
ሁሉም ቢቀየር እንደአዲስ
አገሬ ትናፍቀኛለች እትብቴ የተቀበረበት
አያት ቅድመ አያቴ የሞቱላት
እናትና አባቴ የኖሩበት
አፈር ፈጭቼ ያደግኩበት
በየኔታ ቤት የተማርኩት
ፊደል የቆጠርኩበት
አገሬ ትዝ ትለኛለች
የታሪክ ቁንጮ የሆነች
ወሎ ላሊበላ ጎንደር
አክሱም እንደዚሁም ሐረር
ሉሲ የተፈጠረችበት
የታሪክ ምዕራፍ የተገለጸበት
አባይ አዋሽ ያለበት
የተከዜ ፏፏቴ የሚፈስበት
 ዘርዝሬ የማልገልጸው
አውርቼ የማልጠግበው
በየትም ቦታ የማላፍርባት
በአደባባይ የምናገርላት
ባንዲራዬን የማውለበልብላት
አሁንም እናፍቃታለሁ
ኢትዮጵያነት ለእኔ ዜግነት ነው

ኃይሉ ገቢ Oct 25/2007

ኢትዮጵያችን

ኢትዮጵያችን
አማራ ጉራጌ ሳንል
በዘር ትብታብ ውስጥ ሳንውል
ሁሉም በአንድነት በጋራ
ማንም ሳይቀር ከኤርትራ
ቦታ ሥፍራ ሳንለይ
ሳይኖርብን ከልካይ
በሂዋርዝ ጥላ ውስጥ ሆነን
ብርጅን እኩሌታ አጋምሰን
ዘመን ከዘመን ለመሸጋገር
 ሚሊንየምን ለማክበር
ከፍ አለች ባንዲራችን
ተውለበለበች ሰንደቃችን
እኔም የሥራ ልብሴን አውልቄ
የሰንበቱን ልብስ አጥልቄ
እንደ እንቁጣጣሽ ደምቄ
ይዤ አደይ አበባዬን
ዘመን መለወጡን ማብሰራዬን
እንቁጣጣሽ ዘመን ያምጣሽ ለማለት
ሕዝቡን በሩቁ አሻግሪ ስመለከት
ባንዲራዬን አየዋት ጠገብኳት
በልጅነቴ ሰንደቅ ዓላማችን ያልኳት
ትግርኛ ጉራጌኛው አማርኛ ጭፈራው
ዳንሱ እስክስታ ሽለላው
የማይጠገበው የአበባዮሽ ጨዋታ
ልባችንን ሞላው በደስታ
ያኔ የአገር ቤታችን ሕይወት
በሰው መንፈስ ውስጥ አየሁት
እኔም በምናቤ ተመለከትኳት
የእትብታችን መቃብር ቤታችን
ውብ አገር መመኪያችን
እኛን ያፈራችው አገራችን
ምድረ ገነት ኢትዮጵያችን

            ኃይሉ ገቢ መስከረም1/2000- Sep11/2007

ቃል ኪዳን

ቃል ኪዳን
በአንቺና በእኔ መካከል የነበረ
ቃል ኪዳኑ የተፈራ የከበረ
ትዝታውን ካልረሳሽው ካልካድሽው
ለደቂቃ ለሰኮንድ አስታውሼው
ከሥራ ቦታ እኔን ለማየት
አኔም አንቺን ለመሸኘት
እኔ ሥራ ላይ ከሌለው                                                                       ጭንቀት በፊትሽ ላይ የነበረው
ምን ሆኖ ይሆን የት ሄደ
እስኪሉሽ የወደደና  ያበደ
ቃል ኪዳን የእህትነት
በንፁህ ፍቅር ስሜት
ያን ሁሉ አውርተን ተጨዋውተሽ
ዛሬ እንዴት ጠፋ ከሕሊናሽ
ለፍላፊ ያልሽኝ ምን ብዬ
ምን አጥፍቼ ምን በድዬ
ወሽካታ ያልሽኝ ምን ዋሽቼ
ምን ተናገርኩኝ ኽረ! መቼ
አውርቼ ይሆን ዘላብጄ
የሰደብሽኝ ውድ ወዳጄ
እኔን ሰድበሽ አስቀይመሽ
እንደ አለንጋ አንቺ ገርፈሽ
አናደሽ ጭራ አስበቅለሽ
አሁን ደግሞ ትሸሼያለሽ
እባክሽን ቃል ኪዳኑን አስታውሰሽ
እንታረቅ እንስማማ ሁሉን ትተሽ

ኃይሉ ገቢ 15/6/1975

ትዝታ

ትዝታ
አንቺ ሶቭየት ኅብረት ለመሄድ
እኔም አንቺነትሽን በመውደድ
ሳይነጋ በሌሊት አንቺን ለመሸኘት
በሰላም ያግባሽ ለማለት
ሄድኩኝ ቦሌ መሸኛው  ድረስ
 ሸኝቼሽ ወደ ሥራ ለመመለስ
ብጠብቅ የሚመጣው ሌላ
መንፈሴ ተጨነቀ ሰውነቴ ተጉላላ
ውድ እህቴ ሄዳ ይሆን
ሳንተያይ ዓይን ለዓይን
ሰው አገኝ ነበር ሄዳ እንኳን ቢሆን
ብዬ በሃሳብ ስብከነከን
ድንገት ዓይኔን ወደኋላ ስመለከት
አንቺን አየው የእኔ እመቤት
በሩቅ ሆነሽ ጃኖ ለብሰሽ
ደብተር ብዕር በእጅሽ ይዘሽ
 አውለብልቤ ሰላም አልኩሽ
በዓይኔ ብቻ አንቺን ሸኘውሽ
አይሮፕላኑ ተሻገረ
አመረረ እየበረረ
ወደ ሰማይ ገብቶ ቀረ
ይህ ለእኔ ትዝታ ነው
ምንጊዜም የማልረሳው

ኃይሉ ገቢ1981

ሳቀች

ሳቀች
እንደሞናሊዛ አይደለም ፈገግታ የለበትም
ለማስመሰል ይመስላል እኔን አላረካኝም
ሳቀችብኝ ቅዳሜ ማታ
እኔን አይታ ተመልክታ
ሳቀች እኔን እያየች
ምን ይናገረኝ እያለች
ድሮ ጥንት ስንተዋወቅ
እኔን እንደዛሬ ሳትንቅ
ሩጫ መሮጥ ስትጀምር  
ተስፋ እንዳትቆርጥ ስንመካከር
መስኮብ እሄዳለሁ ስትለኝ
የሞራል ድጋፍ እያደረግኩኝ
ሞራሏ እንዳይሰበር እየመከርኩኝ
አልጄሪያ ኬንያ ሞምባሳ ስትሄድ
አገር ውስጥም ለሥራ ስትገደድ
ናዝሬት ደብረ ዘይት ለሥራ
ሲቻለኝ እየሄድኩ ማንንም ሳልፈራ
አወይ የሰው ነገር
ምንም ሳልናገር
ሳቀች ተንተከተከች
የተበደለ  እየመሰለች
አይደል እንደሞናሊዛ ፈገግታ የለበትም
ተንተክትካ ሳቀችብኝ እኔ ግን አልበደልኳትም
በእኔስ ብትስቂ አይገርመኝም
ወንድምሽ ነኝ ምንም አላጠፋሁም

                         ኃይሉ ገቢ 1973

የምሥራች

ማስታወሻ                                                        
 ከዚህ በታች የሚገኙት ግጥሞች ከ1973 -1975 ባሉት ጊዜያት ከጻፍኳቸው ሲሆኑ ከማስታወሽዬ ውስጥ ያገኘዋቸው ናቸው።
የምሥራች
ደስታዬን ተካፈሉ እልል በሉ
ዘመድና ወዳጆቼ በሙሉ
አኩርፋኝ የነበረች ጓደኛዬ
መንምኖ የነበረው ተስፋዬ
አንድ ቀን በምሽት
ዘመድ ወዳጆቼ ባሉበት
ላንቀያየም በአንዳች ነገር
ማንም ላያጠፋ ካለን በምድር
ያለፈውን ይቅር ብለን
ለሚቀጥለው በሰላም ለመሆን
ታረቅን ዘመዶቼ
እልል በሉ ወዳጆቼ
የእኔን መጥፎ የማትወደውን
የእሷን ጉድለት የማልሻውን
ጓደኛዬን ወድ እህቴን
አይቻት የማልጠግባትን
ታረቅን እንደ በፊቱ ልንሆን

       ኃይሉ ገቢ 1973