Sunday, March 16, 2014

ያረጀ አንበሳ

ያረጀ አንበሳ
ጥንት ዓለም በእግዚኣብሔር ሲፈጠር
አዳም ከሄዋን ጋር በገነት እንዲኖር
እንስሳት አራዊት እንዲያስተዳድር
ሊገዛ ሊመራ የአምላክ ፈቃድ ነበር
አዳም አጠፋና ከገነት ሲባረር
ሁሉም እያረጀ ሁሉም ይሞት ጀመር
በሕይወት እየኖረ አርጅቶ እንዲሞት
አዳም በማጥፋቱ ጌታ ፈረደበት
አንበሳ አርጅቶ ማደን ሲያቅተው
ጉልበቱ ይደክምና ነገር ግራ ሲገባው
የዝንብ መጫወቻ የዓይን አር ማከማቻ
ተከታዩ ጠፍቶ መሆን ነው ለብቻ
ጸሐይ ወጥታ ስትከር ዕዳር ታሀሳስ ጥር
ክረምት ሳይገባ ሲመጣ ግንቦት ወር
ከተማው ሲገማ ቆሻሻ ሲከመር
ዝንብ ይፈለፈላል ለማጥፋት ለመብረር
ሲበር ሲያጠፋ ያገኛል አንበሳ
ጊዜ የጣለውን ኮሳሳ ሬሳ
አንበሳ ሲያገሳ ያላየችው ዝንብ
ዓይኑን ታወጣለች መስሎአት የዕለት ምግብ
ጀግና ነበር አንበሳ የአራዊቶች ንጉስ
ዛሬ ግን ተነሳች እሱን ለመደምሰስ
መላ አከላቱን ዓይኖቹን ለማፍረስ
ዝንብ የአንበሳን ጉልበት ዙፋኑን ለመውረስ

      ኃይሉ ገቢ 1985

ዓለም በቃኝ

 ዓለም በቃኝ
ዓለም በቃኝ ወህኒ ቤቱ፤ማሰሪያ ቤት
የምንሊክ ልጅ ዘውዲቱ ያስገነቡት
አምና ካቻምና ድሮ ጥንት
ስንቱ አለፈ ከዚህ እስር ቤት
በግርፋት ቁም ስቅሉን ተመልክቶ
ስንቱ ወጣ ከዚህ እስር ቤት ተሰቃይቶ
በትኋኑ በበሽታው በዝናቡ በወጨፎ
ስንቱ ሞተ ስንቱ ተርፎ
ዛሬ ዛሬ ይህ ሁሉ ነገር ቀርቶ
ት/ቤት ፕሮጀክቱ ተመስርቶ
ላብራቶሪ  ጤና ጣቢያ አቋቁመን
ዓለም በቃኝን ውብ አድርገን
መታጠቢያ፤ ሽንት ቤቱ ፤ የፅዳቱ
አቤት ስንቱ የእስር ቤቱ ማስደሰቱ
ቢንጎ ፤ካፍቴሪያ፤ ሕብረት ስቁን
ዳርት፤ቴኒስ መጫወቻ አሰባስበን
ሰው አስተምረን በተራችንም ተምረን
ለዓመታት ሰው አስታርቀን                                                                          የበደሉንን ይቅርብለን
ሕዝቡን ብለን ሕዝብን መርተን
ሻማ ሆነን ብርሃን ሆነን ተቀጣጥለን
እስረኛውን አሳሪውን አስደስተን
የሄደውን እየሸኘን የመጣውን እየተቀበልን
ዛሬም እኛ እዚያው አለን
በማማችን ላይ ሆነን
ተራችንን እንጠብቃለን

         ኃይሉ ገቢ 1990

አውለብልቡት ሰንደቃችሁን

አውለብልቡት ሰንደቃችሁን
ዘመን አስቆጥራችሁ
የፈረሰውን ገንብታችሁ
ሰው ሳታዩ የሚያያችሁ
አምላክ ይበልጣል ብላችሁ
ስድብና ግልምጫውን ችላችሁ
በጌታ ጎን የቆማችሁ                                                                                     
በልደት በዓል ሳጣችሁ
ትክዝ ብዬ አንብቼ
የምጠይቀውን ሰው አጥቼ
ብጠብቅ ዘመኑን አልፌ
በሳምንቱ ብመጣ ከንፌ
ማንን ልጠይቅ
የትኛው እንደሚለጥቅ
ትምህርት ቤት እንደተማርነው
ሰላሹ ኸረ! ማነው ?
ጊዜ ወር አለፈኝ
ምጤን እያማጥሁኝ
የሚነግረኝ ስላጣሁኝ
ግራ ቢገባኝ አዘንኩኝ
ከሁሉ ጌታ ይበልጣል አልክኝ
ዛሬ ስትጀምሩ አገልግሎቱን
ማምለክ ማስመለክ ስራችሁን
እንዴት ደስ አለኝ መሰላችሁ
በመድረኩ ላይ በመቆማችሁ
በርቱ እግዚኣብሔር ይርዳችሁ
አውለብልቡት ሰንደቃችሁ

 ኃይሉ ገቢ Jan27/2007  

እኔ አገኘሁት

እኔ አገኘሁት
አምላኬን በጠዋት ገና በማለዳ
ይሁን የሚለኝ እኔን የሚረዳ
ችሎ የሚያስችል እንደልቤ የሚሆን
ልቤ የሚያርፍበት ጌታን የሚታመን
ሁሌም በጸሎቱ እኔን የሚያታጋኝ
ምኞቴ ነበረ ጥሩ ባል እንዳገኝ
ናፍቆቴን በተግባር ሳቀርበው በጸሎት
ፍላጎቴን አይቶ ከሰማየ ሰማያት
ቅሬታ እንዳይገባኝ ልቤን በመመልከት
እርሱ የፈለገው እኔ አገኘሁት
ፍቅርን አግኝቻለሁ!!
መንገዴን ለይቼ መድረሻዬን ገምቼ
መዋለሉን ትቼ በጌታ ጸንቼ
ልቤን ለጌታዬ በፍጹም ሰጥቼ
ካደረኩኝ ወዲህ ጌታን አለንታዬ
ምኞቴን ገልጪ ነገርኩት ለጌታዬ
ጋራ እንዳይሆንብኝ የሚሰጠኝ ትዳር
ብቸኝነት ጠፍቶ በሰላም እንድኖር
በሚሰጠኝ ትዳር እርሱ ብቻ እንዲከብር
ቻይ የሆነች እናት ለእኔ የሚሰጠኝ ሚስት
ይህ ነበር ጸሎቴ ጌታን የጠየቅኩት
ሁሉን የሚችለው እንባዬን ተመልክቶ
የውስጤን የልቤን ጌታዬ ተረድቶ
ንግሥት የምትሆነኝ ሰላም የምትሰጠኝ
ለድካሜ ብርታት ከጎኔ የምትሆነኝ
ላቀረብኩት ጸሎት መልሱን አገኘሁኝ
ችሎታ አይደለም የአምላክ ስጦታ ነው
ሁሉን ሚጠቀልል ፍቅርን አግኝቻለሁ
        የአይችሉምናየፍቅር የጋብቻ መታሰቢያ

             ኃይሉ ገቢ

የጀርባው ነገር

   የጀርባው ነገር
አውቀዋለሁኝ እሱም ያውቀኛል
አስተዳደጌን ማን ይነግረዋል
ከተራ ሥፍራ ከታች ጀምሬ
አስተዳደጌን  ምን ዓይነት ፍሬ
በሥራ ውጤት በምድሬቱ ዛሬ
ነግሬዋለሁ በጥብቅ አብክሬ
በእርከን ቢበልጠኝ ያዘና ወንበር
ሆንኩበት ለእሱ ፋርጣ ባላገር
ቋንቋው ልዩ ነው ጉራማሌኛ
ይመስላል እሱ የሆነ ሕልመኛ
ያጣጣል  ዘይቤ ያነጋገሩ
ስላልተራዳው የውን የምሩ
ግራ መሆኑን ስለተረዳሁት
ቀኝ መሆኔን እኔም ነገርኩት
ቀኝ ሲነሳበት ተቃወሰበት
ቁርጡን በመንገር በማስፈራራት
በእኔ ጎዳና በእኔ አቅጣጫ
መሄድ አለብህ ቢሆን በሩጫ
ለዚህ ትህዛዙ መልሴን ሰጠሁት
ስለዓላማዬ በግልጽ ነገርኩት
በማረጋገጥ ማንነቴን ሲያውቅ
ይናገር ጀመር እኔን በመናቅ
ወዳጅ ዘመዱን በጎኑ ላሉት
ይናገር ጀመር እንዲህ በማለት
ቀኝ ቀኝ በማለት ስላስቸገረኝ
ፈራሁት ጓዴን ከየት እንደሚገኝ
የጀርባው ነገር አከራካሪ
ውስጠ ወይራ በጣም አስፈሪ
ይሻላል ለእኛ ጀርባውን ብናየው
ስልጣን ከያዘ በጣም ችግር ነው
ሰበሰበና ወዳጅ ዘመዱን
ይመክር ጀመር የተቻለውን
የጀርባው ነገር ይጠና ያለኝ
ጀርባዬን አይቶ ሊሳፈርብኝ
ታርጋ ለጣፊ ታክሲ አደረገኝ
የጀርባው ነገር ይጠና ያለኝ
የተገጠበች አህያ አደረገኝ
ወይስ ለሸክም እኔን ፈለገኝ
አጋሰስ መጫኛ በቅሎ አደረገኝ
ለሽምጥ የሚመች ወይ ሰጋር ፈረስ
ሲጋልቡበት የልብ የሚያደርስ
ወደ ጦር ሜዳ ሊፈናጠጥብኝ
በትክሻዬ ላይ እሱ ድል ሊያገኝ
ፍልጎ ይሆን ጀርባህን ያለኝ

    ኃይሉ ገቢ Feb 2008 

እኔ ግን ሞቻለሁ!!

እኔ ግን ሞቻለሁ
ጌታ ደግነቱን ማዳን ታምራቱን
ፍቅሩን ርህራሄውን ለጋስ ቸርነቱን
አባቶች ነግረውኝ ለእኔ አስተምረውኝ
በመስቀል መሞቱን ይህን ገልጸውልኝ
አረጋግጠው መክረው ስላስጠነቀቁኝ
መንገዱን መርጪ ጌታን ተከተክልኩኝ
በእርግጥ እንደሞተልኝ እኔም ስለተረዳው
መሞትን ፈልጌ ከዓለም ተለየው
ወደመስቀሉ ስር በእምነት ሲያደርስኝ
ድሬቶ ቡትቶ ቀድሞ የነበረኝ
ከላዬ ተገፎ ገደል ውስጥ ገባልኝ
መሞት እንደሚገባኝ በመሞት ወሰንኩኝ
ምንም ስለሌለኝ ከዓለም የማተርፈው
ከጌታዬ ጋራ እኔ ግን ሞቻለሁ
          በቸር ይግጠመን!!
          ኃይሉ ነኝ


እግዚኣብሔር ይጠብቃል

                                 እግዚኣብሔር ይጠብቃል
                                 “የእርሱ ታማኝነት እንደጋሻ ወይም እንደ ከተማ ቅጽር ይሆናል” መዝሙር 91፡4
ስለጋሻ የከሰቴ ብርሃን ተሰማ መዝገበ ቃላት እንዲህ ይላል “ ከጎሽ ቆዳ ወይም ከጉማሬ ቆዳ ተሽጉዶ አርበኛው በጦር እንዳይወጋ መመከቻ ይለዋል ።ጋሻ ከጥንካሬ የተነሳ ምንም ነገር አይበሳውም ጀግናው በጦር ሜዳ ላይ ከጠላት የተወረወረ ጦር መክቶ የሚመልሰው በጋሻው ነው። ጋሻ ብልት የሆኑ አካባቢዎችን ጦሩ እንዳይጎዳው ያደርጋል። የእግዚኣብሔር ታማኝነት እንደጋሻ ነው ። ይጠብቃል ፤ይከላከላል ፤ ነፃም ያወጣል  
ሥልጣኔ ከተስፋፋበት ዘመን ጀምሮ አንዳንድ አገሮች ከጠላት ወረራ አገራቸውን ወይም ከተማቸውን ለመከላከል በዘመኑ ጠንካራ በሆኑ ቁሳቁሶች ማለትም ድንጋይና ጡብ ዙሪያውን ወይም ከድንበር እስከ ድንበር ግንብ ይገነቡ ነበር። የመጣው የጠላት ኃይል የሰራዊቱን የመሳሪያ ብዛትና ኃይል የመጣበትን አቅጣጫ ለማወቅ በግንቡ ጫፍ ላይ ማማ( የመጠበቂያ ግንብ) ዙሪያውን እንደመስኮት ያደረጉለት ነበር። ያ ማማ ደግሞ ለሁለት ነገር ይጠቀም ነበር። ለመከላከልና ለመዋጋት ።ለእኛ መከላከያችን በምን የተመሰረተ ነው?እግዚኣብሔር እንደቃሉ ታማኝ ነው።እግዚኣብሔር ይከላከላል ፤ ይጠብቃል። ድሮ ድሮ በልጅነታችን ጊዜ ግሪን ፕራይመርና ሬድ ፕራይመር የሚባሉ የእንግሊዘኛ መማሪያ መጻሕፍት ነበሩ።እነዚያ መጻሕፍት አዲስ በሚገዛበት ጊዜ በውስጡ እንደምርቃት ትራክት (pamphlet) ይገኝ ነበር ።ከነዚያ ትራክቶች ምንጊዜም የማልረሳው (ዶሮና ጫጩቶችዋ) የሚባለው ነበር። ያ ታሪክ የተጻፈው በግጥም ይሁን በስድ ንባብ ትዝ አይለኝም ምክንያቱም ጊዜው በጣም ረዘም ያለ ስልሆነ ነው ። ታሪኩ ግን እንደዚህ ነው። በአንድ መንደር ውስጥ ዶሮ ከነጫጩቶችዋ ትኖር ነበር። በአንድ በጋ ወራት የተለያየ ነገሮችን እየለቃቀመች ሳታስበው ከመንደር ወጥታ ከመንደሩ አጠገብ ወደአለው ዱር ገባች ። ዶሮዋ ከነጫጩቶችዋ ስታንሳ ፤ስትጥል፤ስትለቃቅም  ወደ ጫካው መካከል ዘልቃ ገባች ።በቁጥቋጦው መካከል ሳለች ድንገተኛ የሰደድ እሳት ተነሳ፤ ሰደድ እሳቱ አውሎ ንፋስ ስለነበረው ፤ዶሮና ጫጩቶችዋ መንቀሳቀስ አልቻሉም ። ስለዚህ ከሰደድ እሳቱ እሷንና ልጆችዋን ለማዳን በክንፏ ስር አድርጋ ጭንቅላትዋን ቀበረች ። ሰደድ እሳቱ ሲያልፍ እርሷ በሰደዱ እሳት ምክንያት ስትሞት ልጆችዋ በሕይወት ተረፉ። በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 15፡13 (ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም) የእግዚኣብሔር ታማኝነት እንደዚህ ነው ። እኛ በኃጢያታችን ምክንያት እንዳንጠፋ ጌታ ኢየሱስ ራሱ ሞቶ እኛን ከሞት አዳነን የሰው ልጅ መሞት የለበትም አለ ስለዚህ ከጠላታችን ጋር ፍልሚያ ገጥሞ ወገኖቼ አይጠፉም ብሎ መከላከያ ጋሻ ሆነና በቅጽሩ ውስጥ ያሉትን ከምርኮ አዳናቸው። ሲድራቅ ፤ ሚሳቅና አብድናጎ ናቡከደነፆር ላሰራው ምስል ስገዱ ባትሰግዱ ግን ወደእሳት ተጥላላችሁ ትሞታላችሁ ብሎ ተነገራቸው ። እኛ አንተ ላቆምከው ምስል አንሰግድም። ከዚህ ከሚነደው እሳት እግዚኣብሔር ያድነናል ባያድነን እንኳን ለዚህ አምላኬ ነው ብለህ ላቆምከው ጣዖት አንሰግድም በማለት ውሳኔያቸውን ነገሩት። ሰባት ጊዜ ከነደደው እሳት ውስጥ ቢጣሉም ግንብ አጥር ሆኖአቸው ዶሮዋ ጫጩቶችዋን እንዳዳነቻቸው እግዚኣብሔር ከለላ ሆኖ አዳናቸው። በዘመናችንስ? እግዚኣብሔር ታማኝ ነው ምንጊዜም ታማኝ ነው። በእርሱ ለታመኑት ታማኝ ነው ። የፌስ ቡክ ገጼን ሳገለባብጥ አንድ ጓደኛዬ ሼር ያደረገውን ፎተግራፍ አየሁኝ ። ባለፎተግራፉ መካከለኛ ዕድሜ ያለ ሰው ነው ። ምን ዓይነት አደጋ እንደደረሰበት አይገልጽም ግን አንገቱ የመሰበር አደጋ ስለደረሰበት (cervical Collar) በሚባለው ፋሻ ተጠግኖአል ከፎተግራፍ ስር እግዚኣብሔር ከሞት ስላዳነኝ ሊመሰገን ይገባዋል ይላል ።ምናልባት ይህ ሰው ከመኪና አደጋ ብዙዎቹ ሞተው እርሱ በትንሽ አደጋ እግዚኣብሔር አድኖት ይሆናል እግዚኣብሔርን ሊያመሰግን የተነሳው ። ታሪክ ቢፈተሽ ቁጥር ስፍር የሌላቸው በተለያየ አደጋ ምክንያት ሆስፒታል ገብተው አይድንም አትድንም እየተባሉ በዶክተሮች ውሳኔ ተሰጥቶባቸው ነገር ግን ወደ እግዚኣብሔር በቀረበ የምዕመን ጸሎት ምክንያት እግዚኣብሔር የዶክተሮችን ውሳኔ ሽሮ ከሞት ነፃ ወጥተው፤አዲስ ፍጥረት ሆነው  እግዚኣብሔርን ሲያመሰግኑ፤ ለእርሱ ለአምላካችን ሲያሸበሽቡለት  ብዙዎችን አይተናል ። እግዚኣብሔር ታማኝ ነው ። እግዚኣብሔር ታማኝ የሚሆነው እኛ ስንታመን ብቻ ነው ።እኛ ስንታመን እግዚኣብሔር ይጠብቀናል። በተደረገልን ሁሉ ታምነናል?
                                                      በቸር ይግጠመን!!
                                                       ኃይሉ ነኝ!