Sunday, March 16, 2014

እኔም አልፈርድብሽም

                                          እኔም አልፈርድብሽም
      “እኔም አልፈርድብሽም” በሚለው ዓረፍተ ነገር ውስጥ አንድ ባለቤትና አንድ ማሰሪያ አንቀጽ ወይም ግስ አለው ። በሌላ አባባል ደግሞ ሁለት አካላት እንዳሉ የአማርኛችን የሰዋሰው አወቃቀር ይገልጸዋል። እኔም የሚለው ባለቤት ፈራጅና ምሕረት ሰጪና በሌላ ጎኑ የሚፈረድባት ወይም ምሕረት የተሰጣት በዚህ ዓረፍተ ነገር ውስጥ እናገኛለን ። ይህንን ርዕስ ያመጣሁት ቀጥታ ከዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 8 ሲሆን ፤ጌታ ኢየሱስ በማለዳ በጠዋት ሕዝቡ በዙሪያው ተሰብስበው ወንጌል እያስተማራቸው ነበር። ከሳሾች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን አንድ ስታመነዝር የተያዘችን ሴት ይዘው ፤ጌታ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር በመተባበር እንዲፈርድባት ወደእርሱ አመጡአት ። የሙሴ ሕግ አዋቂዎች “አባታችን ሙሴ በሰጠን ሕግ ላይ ማንም ሰው ሲያመነዝር የተያዘ በሞት ይቀጣ ” ብሎ አዞአል። እኛ ደግሞ የሕጉ ባለአደራዎች ስለሆንን ኃጢያት ሲሰራ ዝም ብለን ማየት ስለማንችል በሕጋችን መሰረት መገደል አለባት ።ሙሴ ያዘዘው ትህዛዝ ይህችን ሴት ለብቻዋ ጉዳዩ ይመልከታት አይመልከታት ሳይገናዝቡ ነበር ይዘዋት የመጡት፤ምክንያቱም ሕጉ በተለያየ ሁኔታ ስለሚገልጸው አንተስ ስለዚህች አመንዝራ ሴት ምን ትላለህ? ብለው ጌታ ኢየሱስን ጠየቁት። ጌታ ኢየሱስን ሊፈትኑት በሌላ ጎኑ ተባባሪ ሊያደርጉት እንዳሰቡ ተገንዝቦ ። የሰውን ልጅ ከሕግና ከኃጢያት ነፃ ለማውጣት ወደዚህ ምድር የመጣው ጌታ ኢየሱስ ጎንበስ ብሎ መፃፍ ጀመረ ። በቃ እሱም እንደኛ ጥቅሱን ጠቅሶ ሊፈርድባት ነው ብለው እርስ በእርሳቸው ሲጠቃቀሱ ፤ ጽሁፉን ጽፎ ጨርሶ ሲነሳ “ከእናንተ መካከል ኃጢያት የሌለበት በመጀመሪያ አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት” አላቸው ። የተጻፈውን ጽሑፍ ሲያነቡ ሐፍረታቸውን ተከናንበው አንድ በአንድ ቦታውን ለቀው መሄድ ጀመሩ። ጻድቅ ነን ብለው የሚኮፈሱት የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ድንጋዩን በመጀመሪያ ከማንሳት የተቆጠቡት ኃጢያት መስራታቸውን የራሳቸው ሕሊና ስለፈረደባቸው ነው።እኛስ በአንድ ቤተስብ ኑሮ ፤ትዳር  ፤አገልግሎት ላይ የመጀመሪያውን ድንጋይ አንስቶ ለመወረውር ቅዱስ ነን?     
      ባለፈው ዓመት ከሥራ ወደቤት ለመመለስ ዳውን ታውን (Down Town) ባቡር ስጠብቅ ፤ አንድ በቅርብ ሩቅ የማውቀው ባቡር ጣቢያ ተገናኝተን ሰላምታ ከተሰጣጣን በኋላ ፤ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን አላይህም ምነው አገልግሎትም ቀረ እንዴ? ብዬ ጠየቅሁት ። ጌታ ሲፈቅድ እጀምራለሁ አለኝ ። ምነው ብዬ አጥብቄ ብጠይቀው ሁኔታውን ገልጾ ነገረኝ ። ሁኔታውን ካዳመጥኩት በኋላ “ የእኔ ወንድም አንተ እንደነገርከኝ በተመሳሳይ ሁኔታ እኔም ችግር ደርሶብኝ ነበር ። ቅስሜ ተሰብሮ ሞራሌ ደቆ ሞት እስከሚያስመኘኝ ድረስ ተስፋ ቆርጪ ነበር ። የፈራጆችን ፍርድ ቁብ ሳልሰጣቸው ። በቤተ ክርስቲያን ተሳትፎና አገልግሎት ቀጠልኩኝ የጠላቴ ሽረባ እንዲወገድልኝ በጾምና በፀሎት ተጋሁኝ ያ እንደጉም ጨፍግጎ የያዘኝ ችግር ብንን አለ ይህው እንደምታየኝ ዛሬም በጌታ ቤት አለው ። ወንድሜ ሆይ! ጠላትን ማሸነፍ የምትችለው በእንደዚህ መንገድ ነው አልኩት ። በጉዳዩ ተስማምተን ሁለታችንም በየፊናችን ሄድን።  
      የእግዚኣብሔር ቃል “ ይቅር በሉ እናንተም ይቅርታን ታገኛላችሁ” ይላል ። ሁልጊዜም አንድ ሰው አጠፋ፤ ኃጢያተኛ ነው ፤ ወንጀለኛ ነው ፤ የውሸት ክርስቲያን ነው እያልን ለመፍረድ ይዳዳናል ያ ደግሞ ሚስጢር ነው ለማንም አትናገር በሚል የውሸት ካባ እንደ ሙሴ የሕግ ሰዎችና እንደፈሪሳውያን የምንፈርድባቸው ብዙዎች ነን እንደዚህ ከሆነ የክርስቶስ ተከታይነታችን በምን ይገለጻል ። እንዲያውም ያንን ሰው በጌታ ፍቅር መክሮና ወደንስሐ እንዲመጣ ማበረታታት እንጂ ጭራሹኑ ከጌታ ቤት እንዲወጣ መገፋፋት ተገቢ ነው?!! ያ ሰው ለእኔና ለአንተ ጌታ ኢየሱስ እንደሞተልን ለርሱም ሞቶለታል ። ጴጥሮስ ወደ ጌታ ኢየሱስ ቀርቦ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው ሰባት ጊዜ ነውን ብሎ ጴጥሮስ ለማረጋገጥ  ሲጠይቀው አይደለም አለ ጌታ ኢየሱስ ሰባት ጊዜ ሰባ ነው አለው እዚህ ላይ እንደምንመለከተው እንዲያውም የተበደልን ብንሆን እንኳን ሰባ ጊዜ ሰባ ይቅር በሉት ነው የሚለው ስለዚህ የጌታ ኢየሱስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን ጥፋት አጥፍተዋል የምንላቸውን ሰዎች ይቅርታ በማድረግ ልባቸውን ወደጌታ እንዲመለሱ ብናደርግ መዝገባችን በሰማይ ይጻፍልናል ። ጌታ ኢየሱስ እንዲሰቀል የሚፈልጉት የካህናት አለቆች ነበሩ ። ሌላው በቄሳራዊው ጴላጦስ አደባባይ ቆመው ስቀለው!! ስቀለው!! ብለው የሚጮሁት ግማሹ ከአምስት ሺ ተመጋቢዎች ውስጥ ነው፤ ሌላው ፈውስን ከጌታ ኢየሱስ የተቀበለ ነው ፤ ቢያንስ ቢያንስ ታአምራት ሲደረግ አይቶአል። የእነዚህን ስዎች ሁኔታ ስንመለከት በደፈናው የሚያደርጉትን የማያውቁ ብቻ ስቀለው ስቀለው የሚሉ ናቸው ። መሐል ሰፋሪ የሆኑት አንዳንዶቹ የመንደር ሰዎች ገፋፍተዋቸው የመጡ ናቸው ። አንዳንዱም እንደይሁዳ የመጮያ ገንዘብ ተከፍሎት ነው ። የውስጥ ሚስጥሩን አያውቁም ብቻ ስቀለው ስቀለው ይሉ ነበር። ኃጢያት የሰራውን ያንን ሰው ስቀለው ስቀለው እያልን ከጌታ ቤት ከምናስወጣው በፍቅር ተቀብለነው በኃጢያቱ ተናዞ በቤቱ እንዲኖር ብናደርገው የእግዚኣብሔር ቃል እንደሚናገረው ገንዘብ አደረግከው ስለሚል የእግዚኣብሔርን መንግስት ያሰፋን ይመስለኛል። ነገር ግን ምንም ምክንያት ሳይኖረን ስቀለው ስቀለው የምንል ከሆነ ለእኛም አስቸጋሪ ዘመን ሊመጣብን ይችላል ። ለማንኛውም በሰው ፊት እንደምንታየው ጻዴቅ መምሰል ሳይሆን ሕይወታችን፤ ኑሮአችን ፤ ስልካችንና አነጋገራችን የተቀደሰ ሊሆን ይገባል ። እንዳይፈረድባችሁ በማንም ላይ አትፍረዱ ብሎ ጌታ ኢየሱስ እንዳስተማረን ። በሁሉም ነገር ላይ ፈራጅ ሆነን ሳለ ድንገት ጌታ ኢየሱስ ቢመጣ የተመካንበት ጽድቃችን ከንቱ እንዳይሆን እንጠንቀቅ!!!
                                                                                           በቸር ይግጠመን!!
                                                                                               ኃይሉ ነኝ     

   

እግዜር ያዘጋጃል

እግዜር ያዘጋጃል
ገና በጠዋቱ አብርሃም ሲጸልይ
ዓይኖቹ ተከፍተው ሲያይ ወደ ሰማይ
የሰራዊት ጌታ ሆኖ በክብሩ ላይ
እግዚኣብሔር ለአብርሃም እንደዚህ ጠየቀው
ምንም ሳያቅማማ መልስ እንዲሰጠው
እግዚሔር የፈተነው እንደዚህ የሚል ነው
እኔ የሰጠውህን በእርጅና ዘመን
አንዱ የምትወደውን ልጅህ ይስሐቅን
እኔ በማሳይህ በሞሪያ ተራራ
መስዋዕት አድርገህ ስጠኝ ሳትራራ
የእግዚኣብሔርን ጥያቄ ነገሩን አድንቆ
ማንም እንዳይጎዳ መንፈሱን ጠብቆ
የሚያደርገውን ሁሉ በኃይል ተጠንቅቆ
እንጨቱ እንዲነድ በደንብ ሰነጣጥቆ
መለኮሻ የሚሆን እንደያዘ እሳቱን
በሌላኛው እጁ ስላታም ቢላውን
በንጋት በጠዋት አዘጋጅቶ ሁሉን
አህያውን ጭኖ ጀመረ ጉዞውን
ከተጓዘ በኋላ ሶስት ቀንና ሌሊት
ልጁን ይስሐቅን ለእግዜር የሚሰዋበት
በሩቁ ተራራውን ሞሪያን ሲያዩት
አህያ ከነጓዙ በዚያ ስፍራ ትቶ
አብርሃም ሁለቱን ሎሌዎችን ጠርቶ
ጉዳዩን ነገራቸው ሚስጥሩን አስረድቶ
እናንተ እዚህ ቆዩ ጠብቁ አህዮችን
መስዋቱን ለማቅረብ እኛ እንሄዳለን
ለአምላክ የሚገባውን እንሰግድለታለን
መሰዋቱን አቅርበን ክብርን እንሰጣለን
እዚህ እንድትጠብቁን እኛ እንመጣለን
ወደሞሪያ ተራራ በመውጣት ላይ ሳሉ
ይስሕቅና አብርሃም እንዲህ ተባባሉ
እሳቱና እንጨቱ ይህው በእጄ ነው
ቢላው እንደሆነ በጣም የተሳለው
ካንተ ጋር ነው ያለው
ከዚህ በተረፈ እጃችን ባዶ ነው
የመስዋዕቱ በግ ለእግዜር የሚሰዋው
ወዴት ነው የሚገኘው?
ይህንን ጥያቄ ይስሐቅ ሲጠይቀው
በፍጥነት ነበረ አብርሃም የመለሰው
እኛ አዘጋጅተናል ቢላዋና እሳት
ለመንደድ እንዲያመች የተሻለ እንጨት
 ለአምላካችን የሚሆን መስዋዕት
ድርሻው የእግዚኣብሔር ነው በግ ለማዘጋጀት
                በቸር ይግጠመን!!
                ኃይሉ ነኝ!






በተጠራህበት ዘብ ቁም!!

                                               በተጠራህበት ዘብ ቁም!!
የኢአዲግ ሰራዊት አዲስ አበባ ሲቆጣጠር የዚያን ጊዜ ከፍተኛ ባለስልጣኑም ፤መካከለኛውም ፤ዝቅተኛውም ሹማምንት ፤ማለትም የደርግ አባላት ፤ሚኒስትሮች ፤የፀጥታ አባላት ፤የገበሬና የቀበሌ አባላት በጅምላ በአንድነት  እዚያው ዓለም በቃኝ እስር ቤት በአንድነት ታስረው ነበር።
  ሰንፎ የተቀመጠው እስረኛ አእምሮው እንዳይላሽቅ ትምህርት መማርና ማስተማር እንዳለበት ተረድቶ ከእስር ቤቱ አጠገብ ዛኒጋባ ቤት ተሰራና ትምህርት ተጀመረ። መጀመሪያ ለገበሬዎቹ ቅድሚያ ተሰጠና ትምህርቱ በየደረጃው እንደፍላጎቱ ቀጠለ፤ ዘብ ካለ ይማራል ዘብ ከሌለ ዘብ እስኪመጣ ይጠብቃል ። በኋላ በኋላ መግባባት ሲጀመር መማር መብቱ መሆኑን አምነው ሲቀበሉ በእስር ቤቱ ኮሚቴ አማካኝነት መማር ተጀመረ። እንደሚታወቀው በዘመኑ ኮምፒውተር ለብዙዎቻችን አዲስ ስለነበረ ፤አንድ የታወቁ እንጂነር (theory) ንድፈ ሀሳቡን አስተምረውን በኋላ ላይ አንድ ቤተሰብ ኮምፒውተሩን ገዝቶ ለእስር ቤቱ ስለሰጠ ሰጪው ዜግነቱ አሜሪካው ስለሆነ ኮምፒውተሩ በስንት መከራ ወደእስር ቤቱ ገባ ። እኛ ደግሞ ችግር ያደርሳሉ ተብሎ ስለተፈራ ለዚያ ኮምፒውተር አንድ ዘብ ተመድቦለት ነበር። ያንን ኮምፒውተር በደንብ ከፋፍተን ለማየትና ለመረዳት አትንኩ! አታድርጉ! የሚል ትህዛዝ ስለበዛብን ያንን ትምህርት የጀመረው በሙሉ መበስጫጨት ጀመረ። እኔ ደግሞ ከዚያ ዘብ ጋር በብዙ ነገር እንግባባ ስለነበረ ኮምፒውተር ያለ ስልክና ኢንተርኔት ምንም ባዶ ማለት ነው ለምን አንተ ዘብ ትቆማለህ? ተዉ!! አታድርጉ!! አትንኩ!!ትለናለህ ለምንድነው ብዬ ጠየቅኩት ። ከበላይ አለቃዬ ስለዚህ ኮምፒውተር ብዙ ተነግሮኛል ደግሞም የእናንተ አደገኛነት ከበረሃ ጀምሮ ስለምናውቀው እንደገናም  እናንተ በእንደዚህ ነገር በጣም የሰለጠናችሁ ስለሆነ አንድ ነገር አድርጋችሁ ከውጪው ዓለም ብትገናኙ  በንዝህላልነቴ የሚደርስብኝ እኔ አውቃለሁ ። ስለዚህ በተሰጠኝ የስራ ድርሻ ተጠንቅቄ መጠበቅ አለብኝ የእኔ ሥራ ኮምፒውተሩን መጠበቅ ስለሆነ እጠብቃለሁ አለኝ። ስለዚያ ወታደር ሳስብ በጣም ይገርመኝ ነበር በተሰጠውና በታዘዘው ነገር ሙሉ እምነት የነበረውና ለዓላማው ታማኝ ነበር ።   
   የእግዚኣብሔር ቃል በ2ጢሞ 2፡3 እንዲህ ይላል እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ በጎ ወታደር ከእኛ ጋር መከራን ተቀበል በውትድርና የሚያገለግል ሰው አዛዡን ለማስደሰት ይጥራል እንጂ በሌላ ሥራ ራሱን አያጠላልፍም ።እንደ በጎ ወታደር ፤ በጎ የሚለው ቃል ከሳቴ ብርሃን ተሰማ መዝገበ ቃላት (ጠባየ መልካም፤ በጎ ሰው ፤ የተወደደ ፤ ያማረ ቅን የቀና ይለዋል ። በጎ ወታደር ምን ዓይነት ነው? በጎ ወታደር መከራን የሚቀበል ነው ፤ በጎ ወታደር አዛዡን ለማስደሰት የሚጥር ነው ፣ በጎ ወታደር ራሱን በሌላ ሥራ አያጠላልፍም ።እንደ መዝገበ ቃላቱ ደግሞ በጎ ወታደር በጎ ሰው ነው ፤ በጎ ወታደር ቅን ነው ። ወታደር የተሰጠውን የሥራ ድርሻ የሚሰራና የታዘዘውን የሚፈጽም ነው ። በውትድርና ውስጥ የተለያየ እርከን አለ ከተራ ወታደር እስከ ጄኔራል፤ ከተራ ወታደር ጀምሮ ሁሉም አለቃ አለው ። እኛ ግን በጎ ወታደርነታችን ለጌታችን ኢየሱስ ነው ። ጌታ ኢየሱስ ጠቅላይ አዛዣችንና ጠቅላይ መመሪያችን ነው ። ወታደር ከተሰጠው ሥራ ውጪ አይሰራም እያንዳንዳችን የክርስቶስ በጎ ወታደር ነን በክርስቶስ ኢየሱስ የተመረጥን ፣ ወታደር ደግሞ በተመደበበት ሥራ የሚሰራ ነው ከተሰጠው ሥራ ውጪ አይሰራም ምደባው ዘብ ከሆነ የዘብ ስራውን በትጋት ይሰራል ። በ1ቆሮንቶስ 12፡5-6 አገልግሎትም ልዩ ልዩ ሲሆን ፤ ጌታ ግን አንድ ነው ፤ አሰራርም ልዩ ልዩ ሲሆን ፤ ሁሉን በሁሉ የሚሰራው ግን ያው አንዱ እግዚኣብሔር ነው። ለውትድርና የተጠራንበት አገልግሎት በየትኛው ጎን ነው? ። አገልግሎት ልዩ ልዩ ነው በቤተ ክርስቲያን ወይም በጌታ ሥራ ውስጥ አገልግሎት የተለያየ ነው ። በወታደራዊ አገልግሎት ጌታ የመደበህ በየትኛው ክፍል ነው ?።ጸሎት ነው ፤ ማስተማር ነው ፤ መምከር ነው…….ወይስ ቤቱን ማጽዳት ካላውቅከው በጸሎት ጌታን ጠይቅህ አገልግሎትን መጀመር ያስፈልጋል ። በወታደራዊ አገልግሎት እንደምታየው ጠበብ ያለ ይመስላል ። ቤቱንም ማጽዳት ከፍተኛ አገልግሎት ነው ።ትርፍ ሳታተርፍ ብትገኝ ተጠያቂ ነህ !!ሳላገለግል ጌታ ቢመጣብኝ ተጠያቂ ነኝ!! ወታደሮች አለቃቸውን ለማስደስት ሥራቸውን እንደሚገባው እንደሚሰሩ፤አለቃቸው የማዕረግ እድገትና ሽልማት እንደሚሰጣቸው ያላግባቡ ሲፈጽሙ የተገኙ ደግሞ እንደሚጠየቁ ታውቃለህ? በማቴዎስ ወንጌል በምዕራፍ 25፡14-30 ና በሉቃስ ወንጌል በምዕራፍ 19፡11-27 ጌታ ኢየሱስ የሰጠው ምሳሌ ማስታወስ ይገባል አንድ መስፍን ንጉሥ ሆኖ ለመምጣት ወደ ሩቅ አገር ለመሄድ ሲዘጋጅ አገልጋዮቹን ጠርቶ ለእያንዳንዱ አስር ምናን ሰጣቸው ። ንግሥናውን ተቀብሎ ሲመለስ ፤ የመጀመሪያው ቀርቦ አስር ምናን ሰጠህኝ አስር ምናን አትርፎአል ይህው ገንዘብህ ብሎ ሰጠው ንጉሱም በአስር ከተማ ላይ ባለስልጣን አድርጎ ሾመው ። አምስት ያተረፈውም በአምስት ከተሞች ላይ ሾመው ። በመጨረሻ ጌታ ሆይ!!አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፤ ካልበተንህበትም የምትሰብስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ ስለዚህ መሬት ቆፍሬ ቀበርኩት  ይህው ገንዘብህ ብሎ ለንጉሱ ሰጠው ። ንጉሡም አንተ ክፉ ፤ ሰነፍ አገልጋይ ያላስቀመጥኩትን የምወስድ ፤ ያልዘራሁትን የማጭድ ፤ ጨካኝ ሰው መሆኔን ካውቅህ ፤ መጥቼ ገንዘቤን ከነትርፉ እንድወስድ ለምን ለሚሰሩበት ሰዎች አልሰጠህም ? ጌታ ኢየሱስ ልንሰራበት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ሰጥቶናል ያ ስጦታ ሰርተን ፍሬ ልናፈራበት ነው ።ስለዚህ እኛ በጎ ወታደሮች አዛዣችን ኢየሱስን በሁሉም ሁኔታ በተሰጠን ስጦታ ልናስደስተው ይገባል እንጂ እንደ ሰነፍ አገልጋይ የተሰጠን ብር ልንቀብረው አይገባም ስለዚህ በተጠራንበት አቅጣጫ ስብከት ቢሆን ምስክርነት መዝሙር ቢሆን ጸሎት ጌታ በሰጠን ስጦታ እናገልግል።ለዚህ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ምሬቱን ይስጠን!! አሜን!!!
                                          ቸር ይግጠመን!!!

                                            ኃይሉ ነኝ!                

አዋጅ ለባለጆሮዋ ቤተ ክርስቲያን

                                        አዋጅ ለባለጆሮዋ ቤተ ክርስቲያን
         በቅርብ ለዘመን መለወጫ አንድ ቀን ሲቀረው ከፌስ ቡክ ጓደኞቼ በአሜሪካ ሲልቨር ስፕሪንግ ማሪላንድ ከምትኖር እህቴ አዋጅ ለባለጆሮዋ ቤተክርስቲያን በሚል ርዕስ ኤሜል ደረሰኝ በቀጥታ ለእኔ የተፃፈ ስለነበረ አነበብኩት፤ ደግሜ አነበብኩት ለሶስተኛ ጊዜ ካነበብኩት በኋላ ይህንን አዋጅ ሌላውም ሊያነበው ይገባል ብዬ አንዳንድ ሃሳቦችን ጨምሬ ጻፍኩት። ሙሉ ለሙሉ ሃሳቡ የእህቴ ነው።
      ( ንቂ ንቂ ዲቦራ ንቂ ንቂ  ቅኔም ተቀኜ ) መሳፍንት 5፡12
 ንቂ ፥ንቃ ፥ ንቁ ፥ መንቃት የሚለውን ግስ ስንመለከት የከሰቴ ብርሃን ተሰማ መዝገበ ቃላት እንዲህ ይላል ዕውቀትን ለመሰብሰብ አህምሮውን የሰነገለ ፣ የወለወለ ሲለው ። የነቃ ፥ በዕውቀት የተባ ፥ ጥበብን ለመስማት የልቡናውን ጆሮ ቀቅሮ የሚያዳምጥ ይለዋል።
ሳባ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ ነቃ ተቀሰቀሰ፣ ተጠነቀቀ፣ ተጋ ይላል።
   ዲቦራና ባራቅ በዘመሩት መዝሙር ላይ የእግዚኣብሔር ሕዝብ ከከተሞቻቸው ተሰልፈው ወረዱ ይላል። ወርደው አልቆሙም ከላይ “ ዲቦራ ሆይ! ንቂ! ተነሺ! መዝሙር እየዘመርሽ ወደፊት ቀድመሽ ምሪ” ብለው ዘመሩ በነገራችን ላይ ዲቦራ የዕብሩ ትርጉም ንብ ማለት ነው ታዲያ የሕዝቡን መዝሙር ሰማች መጽሐፉን ስናነበው ምን ያህል የእግዚኣብሔርን ስራ እንደሰራች ታሪኳን ስናነብው ይገልጸዋል ። በዚህ ላይ የተጠቀሰው ጥቅስ ለእሷ የእግዚኣብሔርን ስራ ለመስራት ዋና መስረት ነው የሆናት ።  መንቃት በቀጥታ ከመጠቀም ጋር የተያያዘ ነው ። መጠቀም የሚቻለው ከሙሉ መንቃት ጋር ነው ።እንደ ዲቦራ።
     ግማሽ መንቃት ለተጠቃሚነት አያበቃም የከሰቴ ብርሃን መዝገበ ቃላት ዕውቀትን ለመሰብሰብ አህምሮውን የሰነገለ፥ ጥበብን ለመስማት የልቡናውን ጆሮ ቀቅሮ የሚያዳምጥ ይለዋል የተኛና በግማሽ መንቃት ለተጠቃሚነት አያበቃም የመኃልየን ቆንጅዬ ሴት “እኔ ተኝቻለሁ ልቤ ግን ነቅቶአል” አይደለም ያለችው። የመኃልዬ ቆንጆ ሙሉ ለሙሉ አለመንቃቷ ፍቅረኛዋን ልታገኝ ያለመቻሏን ትናገራለች። እግዚኣብሔር ለቤተ ክርስቲያን በሰጣት ትሩፋት ተጠቃሚ ለመሆን አንድ ነገር ግድ ይላታል ። መንቃት!! ለመንቃት ደግሞ ምን ያስፈልጋታል? ቤተ ክርስቲያን ለመንቃት ስነ-ጽሑፍ ያስፈልጋታል ምክንያቱም አንዱ የመንቂያ መንገድ ስነ-ጽሑፍ ነው። ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ለስነ-ጽሑፍ ግድ የለሽ ናት ። ስነ-ጽሑፍ ምኗም አይደለም ። ስነ-ጽሑፍ ለቤተ ክርስቲያን ቢኖርም ባይኖርም የማይጠቅምም የማይጎዳም ነው ። እንደ ምንም ነገር ነው። ስነ-ጽሑፍ ለእግዚኣብሔርም ለሰይጣንም ጠቃሚያቸው ነው ።
       እግዚኣብሔር ለሰው ልጅ ሶስት ታላላቅ ስጦታዎችን ሰጥቶአል። በምንም የማይተኩ ከምንም የማይወዳደሩ ልጁን፤ መንፈሱንና ቃሉ ናቸው ። ከእነዚህ ሶስቱ ደግሞ አንደኛው (ቃሉ) በመጽሐፍ ደረጃ በእያንዳንዱ ክርስቲያን እጅ ይገኛል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ያነባል ፤ ይማራል፤ያስተምረዋል፤ ያስነብበዋል፤ ያነበዋል፤ ያጠናዋል፤ ያስጠናዋል፤ ይሰብከዋል……..ይህ እጅግ ታላቅና ውድ ስጦታ ለሰው ልጆች ይደርስ ዘንድ እግዚኣብሔር የስነ-ጽሑፍ ችሎታውን በውስጣቸው ያሳደረባቸውን ሰዎች ተጠቅሞአል። ይህ ማለት ደግሞ እግዚኣብሔር ታላቅ ስጦታ የሆነውን ወደ ሕዝቡ ለማድረስ ስነ-ጽሑፍን ዋነኛ መሣሪያው አድርጎ ተጠቅሞአል ማለት ነው ። በድንቅ ድንቅ ስነ-ጽሑፍ የእግዚኣብሔር ታላቅ ሥራ የተገለጸው በስነ-ጽሑፍ ባለሙያዎች ነው ።
      በሌላ ጎኑ ደግሞ ሰይጣንም ታላላቅ የክህደት አስተምህሮችንም ያሰራጨው በስነ-ጽሑፍ አማካይነት ነው ።የስነ-ጽሑፍ ችሎታ ያላቸውን አድኖና አሳድዶ ተጠቅሞባቸዋል። በሃይማኖት ሽፋን ኢየሱስን “ሰው ብቻ” አድርገው በማስቀመጥ ቁጥር ስፍር የሌላቸውን ሰዎች ወደጥፋት የነዱ የስነ-ጽሑፍ ሰዎች ናቸው ። በቅርባችን ደግሞ ገድላትና ድርሳናትን በየስርቻውና በየቤታቸው በማዘጋጀት መጽሐፍ ቅዱስን ይዘው እንኳን ወደ ተረት እንዲሳቡ ለማድረግ የበቁት ሰይጣን የስነ-ጽሑፍ ሰዎችን በመጠቀም ነው ።
      ቤተ ክርስቲያንስ እንዴት ታድርግ? እግዚኣብሔር የስነ-ጽሑፍ ሰዎችን በስስት የሚያያቸው ለመሆናቸው ቅንጣት ያህል የምትጠራጠር አይመስልም !!ስለዚህ የስነ-ጽሑፍ አቅም ያላቸውን ልታበረታታቸው፤ አገልግሎቱን ልትደግፍና የእግዚኣብሔርን ሥራ እንዲሰራ ከጎን ልትቆም ይገባል ።

     ዲቦራዋ ቤተ ክርስቲያን ሆይ ንቂ!! እንቁዎችሽን አክብሪ ብዙ መስራትና መጥቀም ሲችሉ እንደ መኃልዬ ቆንጆ ባለመንቃት በችለተኛነት እንቁዎቻቸውን እንደታቀፉ አይጥፉብሽ አይሙቱብሽ። ቤተ ክርስቲያን ማለት ደግሞ እኔም ፤ አንቺም ፤ አንተም ፤ እሱም ፤ እሷም ፤ እነርሱም ፤ ሁላችንም ስለሆንን የእግዚኣብሔርን ሥራ ልንሰራ እንነሳ ቤተ ክርስቲያን ያለ ስነ-ጽሑፍ ግማሽ መንቃት ስለሆነ ነቅተን ለማንቃት እንድንችል አገልግሎቱን እንደግፍ    

ምድራዊውን ትታችሁ!!

ምድራዊውን ትታችሁ!!
የእግዚኣብሔርን ሕዝብ በመድረክ ላይ
ምህመኑ ባለበት ሥፍራ በአደባባይ
ጭፋሪዬ  ዝማሬዬ ማሸብሸቡ
አንድም ሳይዛነፍ ማወረቡ
እኔን ላየ የሚመስለው
በሰማያት ሰማያት ያለነው
ፀሎቱን አሳምሪ ሳንበለብለው
እንባዬን ፊቴ ላይ ስሞላው
በለሆሳሴ ሳነባው
ሰዓቱን በለቅሶ ሳስረዝመው
ሁሁታዬን በዕልልታ ሳንበለብለው
ለሚመለከተኝ ድንቅ ነው
ስሰብክ ወንጌልን ስናገር
የቃል ሚስጢርን ሳሳምር
ፊደል ቋንቋ ሳነባብር
ወዲያ ወዲህ ስሽከረከር
ያየኝ የሰማኝ በሙሉ
ጻድቅ በማለት ይገረማሉ
ፈራሽ ስራዬን ያደንቃሉ
በዙፋኑ ላይ እኔን ይሾማሉ
እኔ ግን ድሃ ከንቱ ፍጥረት
የራሴን ጽድቅ የምመሰርት
በኢየሱስ ስም እኔን የማነግሥ
እሱ የሰራውን እኔ የማፈርስ
ለሚያደንቁኝ አደንቃለሁ
ብድራቱንም እመልሳለሁ
ከእኔ በልጦ አድጎ ሳየው
ተቀባይነት በሕዝብ ሲኖረው
ምክንያት ነገር እፈጥርና
መሰላሉን እሰብርና
በአንካሴ አስኪድና
ለእሱ አምሳያውን እፈጥርና
በአስቸኳይ አስወግደዋለሁ
ቦቱ እንደሆን የእኔ ነው
እኔ ማነኝ ከንቱ ፍጥረት
የማላግጥ በእግዚኣብሔር ቤት
የወንጌል አብሮ አደጌን
የጌታ ልጅ ጓደኛዬን
የወንጌል ፍሬ መከታዬን
አንዲት ነጥብ ሲያርመኝ
ሥርዓቱ ይህ ነው ብሎ ሲለኝ
የአፌን ጅራፍ አስጨኸለሁ
ቦታ እንዳይኖረው አደርጋለሁ
እኔ ማነኝ ከንቱ ፍጥረት
የማፈርስ የእግዚኣብሔር ቤት
ለምድራዊ ኑሮዬ ሳካብት
ነገሬን በምድር ስመሰርት
ጥፋትን ብቻ በመመልከት
አምልጦኝ ነበር ሰማያዊውን ሕይወት
አሁን ግን ገባኝ ተረዳሁኝ
የከንቱ ከንቱ አንደሆንኩኝ
ንስሐ እንደሚያስፈልገኝ
ጌታ እንደገና እንዲጎበኘኝ
ውጣ ውረዱን አልፋችሁ
በእግዚኣብሔር ቤት ሆናችሁ
ዛሬም በእኔ ሃሳብ ያላችሁ
ሳታውቁም ሆነ አውቃችሁ
የራሳችሁን ጥቅም ፈልጋችሁ
የእግዚኣብሔርን ቤት ያፈረሳችሁ
ተመለሱ ተለወጡ እባካችሁ
የምድር የሆነውን ትታችሁ።
በቸር ይግጠመን!!
ኃይሉ ነኝ!!Jan 2014


በትርህን አንሳው!!

 በትርህን አንሳው!!!
ሙሴ!! በግብጻውያን ብትናደድ
ከፈርዖን ቤተ መንግሥት ስትሰደድ
ከግብጽ ተነስተህ በረሃ ብትወርድ
በዚያ በበረሃ ምድር
በጎችን ስታግድ የአማትህን የዮቶር
ትይዘው የነበረው ያች ድንቅ በትር
ጣላት ስትባል ጌታን በማክበር
ስትጥላት እባብ ስታነሳት በትር
በእግዚኣብሔር ትህዛዝ በጣም በመደሰት
ይዘሃት የሄድከው ወደፈርዖን ቤት
የተሰራባትን ድንቅ ታአምራት
ሕዝቡ እግዚኣብሔርን በክብር ለመቀደስ
ከግብጽ ነጻ ሆኖ ባሕሩ ዳሩ ሲደርስ
ሕዝቡን ሊያጠፋ ፈርዖን ሲገሰግስ
ወገኖቼ አትፍሩ እግዜርን አክብሩ
ፈርዖን በሚያደርገው አትደናበሩ
እግዚኣብሔር ስለእኛ ጠላትን ይዋጋል
ጸሐይዋ ሳትጠልቅ ድል ለእኛ ይሆናል
ብለህ በትርህን ወደላይ ስታነሳ
ፈርዖን ሰምጦነው የሆነው ሬሳ
በትርህን አንስተህ እጅህን ስትዘረጋው
የአማሌቅ ሰራዊት በጦር የሚሸነፈው
በትርህ የታለ? ለማንስ ሰጠህው?
ሙሴ እንድትነግረኝ ወዴት አደረግከው ?
ለእኔ ባለአደራ ለኢያሱ ሰጠውት
ይመልስላችኋል ለእሱም ብትጠይቁት
ኢያሱም  ቢሆን ሳለ በሕይወቱ
በኖረበት ዘመን ሲኖር በምድሪቱ
እግዜርን አክብሮ ተስፋን አስከብሮ
ከሽማግሌዎች ጋር በመግባባት ኖሮ
በትሩን ሰጥቶአል ለወር ባለተራው
ሊጠየቅ ሚገባው ባለተራው ሰው ነው
አደራውን ከኢያሱ የተቀበልከው
ለበትሩ ባለአደራ የሆንከው
በጊዜው በዘመኑ በሕይወት የምትኖረው
ሲወርድ ሲዋረድ አንተ የተረከብከው
በትርህ ወዴት ነው ያለው?
በበርሃ ስትኖር በጎቹን ያገድክበት
ወንዝ ስትሻገር ጀልባ የቀዘፍክበት
ጠላት ሲታገልህ ድል የመታህበት
ለነፍሳት መዳኛ ወንጌል የገልጽክበት
የጠላት ጭንቅላት የፈጠፈጥክበት
ከተማ ስትገባ ወደየት አደርስከው
አንተ ባለአደራ ተስፋህን አትርሳው
ብዙ ድል ስላለህ አንተ የምትሰራው
ዛሬም እንደገና በትርህን አንሳው።
               ቸር ይግጠመን!!
                 ኃይሉ ነኝ!





በእርግጥ ይጎበኛል!!!

በእርግጥ ይጎበኛል
ሕዝቦቼ እያለ ጌታ የሚጠራቸው
በአብርሃም ምክንያት ተስፋ የገባላቸው
በኖሩበት ምድር ድርቅ ቢያጠቃቸው
የሚበላ ነገር ቢያጡ ከቤታቸው
እርሻቸው ጦም አድሮ ምግብ ቢያሳጣቸው
ወረዱ ወደግብፅ በተሃቸውን ይዘው
ወደግብፅ ቢጓዙ እህልን ፍለጋ
ዮሴፍ ሰጣቸው ምግብ ያለዋጋ
መኖሩ ሲታወቅ ዮሴፍ በሕይወት
ሁሉም ተሰብስበው ሄዱ ሊጎበኙት
እግዜር ጎበኛቸው ጌታ አሰባቸው
ከመታው ርሃብ ከሞት ታደጋቸው
ሀና በዘመንዋ ልጅ ስላልነበራት
ሁልጊዜም ፀሎትዋ ነበር እንዲሰጣት
ጠዋት ታነባለች ማታም ታለቅሳለች
ሁሌም ንዝነዛዋ ልጅ ስጠኝ እያለች
ምኞትዋ ነበረ ልጅ እንዲሰጣት
ካለባት ተጽዕኖ ነጻ እንዲያወጣት
እግዚኣብሔር እንባዋን ጩኽትዋን ተመልክቶ
ጌታችን ጎበኛት ሳሙኤልን ሰጥቶ
ዛሬም በዘመናችን በአንዳድ ሰው ሕይወት
ችግሩ በዝቶበት ተስፋው ያለቀበት
መቼ ነው እግዚኣብሔር እኔን ሚጎበኘኝ
ከተሸከምኩት ችግር ጌታ የሚያላቅቀኝ
ብሎ የሚያስብ ሰው
ምንም የሌለው ተስፋ የሚጠብቀው
በእርግጥ ይጎበኛል እግዚኣብሔር ታማኝ ነው።
               በቸር ይግጠመን!!!
                ኃይሉ ነኝ!