በተጠራህበት ዘብ ቁም!!
የኢአዲግ
ሰራዊት አዲስ አበባ ሲቆጣጠር የዚያን ጊዜ ከፍተኛ ባለስልጣኑም ፤መካከለኛውም ፤ዝቅተኛውም ሹማምንት ፤ማለትም የደርግ አባላት ፤ሚኒስትሮች
፤የፀጥታ አባላት ፤የገበሬና የቀበሌ አባላት በጅምላ በአንድነት እዚያው
ዓለም በቃኝ እስር ቤት በአንድነት ታስረው ነበር።
ሰንፎ የተቀመጠው እስረኛ አእምሮው እንዳይላሽቅ ትምህርት መማርና ማስተማር
እንዳለበት ተረድቶ ከእስር ቤቱ አጠገብ ዛኒጋባ ቤት ተሰራና ትምህርት ተጀመረ። መጀመሪያ ለገበሬዎቹ ቅድሚያ ተሰጠና ትምህርቱ በየደረጃው
እንደፍላጎቱ ቀጠለ፤ ዘብ ካለ ይማራል ዘብ ከሌለ ዘብ እስኪመጣ ይጠብቃል ። በኋላ በኋላ መግባባት ሲጀመር መማር መብቱ መሆኑን
አምነው ሲቀበሉ በእስር ቤቱ ኮሚቴ አማካኝነት መማር ተጀመረ። እንደሚታወቀው በዘመኑ ኮምፒውተር ለብዙዎቻችን አዲስ ስለነበረ ፤አንድ
የታወቁ እንጂነር (theory) ንድፈ ሀሳቡን አስተምረውን በኋላ ላይ አንድ ቤተሰብ ኮምፒውተሩን ገዝቶ ለእስር ቤቱ ስለሰጠ ሰጪው
ዜግነቱ አሜሪካው ስለሆነ ኮምፒውተሩ በስንት መከራ ወደእስር ቤቱ ገባ ። እኛ ደግሞ ችግር ያደርሳሉ ተብሎ ስለተፈራ ለዚያ ኮምፒውተር
አንድ ዘብ ተመድቦለት ነበር። ያንን ኮምፒውተር በደንብ ከፋፍተን ለማየትና ለመረዳት አትንኩ! አታድርጉ! የሚል ትህዛዝ ስለበዛብን
ያንን ትምህርት የጀመረው በሙሉ መበስጫጨት ጀመረ። እኔ ደግሞ ከዚያ ዘብ ጋር በብዙ ነገር እንግባባ ስለነበረ ኮምፒውተር ያለ ስልክና
ኢንተርኔት ምንም ባዶ ማለት ነው ለምን አንተ ዘብ ትቆማለህ? ተዉ!! አታድርጉ!! አትንኩ!!ትለናለህ ለምንድነው ብዬ ጠየቅኩት
። ከበላይ አለቃዬ ስለዚህ ኮምፒውተር ብዙ ተነግሮኛል ደግሞም የእናንተ አደገኛነት ከበረሃ ጀምሮ ስለምናውቀው እንደገናም እናንተ በእንደዚህ ነገር በጣም የሰለጠናችሁ ስለሆነ አንድ ነገር አድርጋችሁ
ከውጪው ዓለም ብትገናኙ በንዝህላልነቴ የሚደርስብኝ እኔ አውቃለሁ
። ስለዚህ በተሰጠኝ የስራ ድርሻ ተጠንቅቄ መጠበቅ አለብኝ የእኔ ሥራ ኮምፒውተሩን መጠበቅ ስለሆነ እጠብቃለሁ አለኝ። ስለዚያ ወታደር
ሳስብ በጣም ይገርመኝ ነበር በተሰጠውና በታዘዘው ነገር ሙሉ እምነት የነበረውና ለዓላማው ታማኝ ነበር ።
የእግዚኣብሔር ቃል በ2ጢሞ 2፡3 እንዲህ ይላል እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ
በጎ ወታደር ከእኛ ጋር መከራን ተቀበል በውትድርና የሚያገለግል ሰው አዛዡን ለማስደሰት ይጥራል እንጂ በሌላ ሥራ ራሱን አያጠላልፍም
።እንደ በጎ ወታደር ፤ በጎ የሚለው ቃል ከሳቴ ብርሃን ተሰማ መዝገበ ቃላት (ጠባየ መልካም፤ በጎ ሰው ፤ የተወደደ ፤ ያማረ ቅን
የቀና ይለዋል ። በጎ ወታደር ምን ዓይነት ነው? በጎ ወታደር መከራን የሚቀበል ነው ፤ በጎ ወታደር አዛዡን ለማስደሰት የሚጥር
ነው ፣ በጎ ወታደር ራሱን በሌላ ሥራ አያጠላልፍም ።እንደ መዝገበ ቃላቱ ደግሞ በጎ ወታደር በጎ ሰው ነው ፤ በጎ ወታደር ቅን
ነው ። ወታደር የተሰጠውን የሥራ ድርሻ የሚሰራና የታዘዘውን የሚፈጽም ነው ። በውትድርና ውስጥ የተለያየ እርከን አለ ከተራ ወታደር
እስከ ጄኔራል፤ ከተራ ወታደር ጀምሮ ሁሉም አለቃ አለው ። እኛ ግን በጎ ወታደርነታችን ለጌታችን ኢየሱስ ነው ። ጌታ ኢየሱስ ጠቅላይ
አዛዣችንና ጠቅላይ መመሪያችን ነው ። ወታደር ከተሰጠው ሥራ ውጪ አይሰራም እያንዳንዳችን የክርስቶስ በጎ ወታደር ነን በክርስቶስ
ኢየሱስ የተመረጥን ፣ ወታደር ደግሞ በተመደበበት ሥራ የሚሰራ ነው ከተሰጠው ሥራ ውጪ አይሰራም ምደባው ዘብ ከሆነ የዘብ ስራውን
በትጋት ይሰራል ። በ1ቆሮንቶስ 12፡5-6 አገልግሎትም ልዩ ልዩ ሲሆን ፤ ጌታ ግን አንድ ነው ፤ አሰራርም ልዩ ልዩ ሲሆን ፤
ሁሉን በሁሉ የሚሰራው ግን ያው አንዱ እግዚኣብሔር ነው። ለውትድርና የተጠራንበት አገልግሎት በየትኛው ጎን ነው? ። አገልግሎት
ልዩ ልዩ ነው በቤተ ክርስቲያን ወይም በጌታ ሥራ ውስጥ አገልግሎት የተለያየ ነው ። በወታደራዊ አገልግሎት ጌታ የመደበህ በየትኛው
ክፍል ነው ?።ጸሎት ነው ፤ ማስተማር ነው ፤ መምከር ነው…….ወይስ ቤቱን ማጽዳት ካላውቅከው በጸሎት ጌታን ጠይቅህ አገልግሎትን
መጀመር ያስፈልጋል ። በወታደራዊ አገልግሎት እንደምታየው ጠበብ ያለ ይመስላል ። ቤቱንም ማጽዳት ከፍተኛ አገልግሎት ነው ።ትርፍ
ሳታተርፍ ብትገኝ ተጠያቂ ነህ !!ሳላገለግል ጌታ ቢመጣብኝ ተጠያቂ ነኝ!! ወታደሮች አለቃቸውን ለማስደስት ሥራቸውን እንደሚገባው
እንደሚሰሩ፤አለቃቸው የማዕረግ እድገትና ሽልማት እንደሚሰጣቸው ያላግባቡ ሲፈጽሙ የተገኙ ደግሞ እንደሚጠየቁ ታውቃለህ? በማቴዎስ
ወንጌል በምዕራፍ 25፡14-30 ና በሉቃስ ወንጌል በምዕራፍ 19፡11-27 ጌታ ኢየሱስ የሰጠው ምሳሌ ማስታወስ ይገባል አንድ መስፍን
ንጉሥ ሆኖ ለመምጣት ወደ ሩቅ አገር ለመሄድ ሲዘጋጅ አገልጋዮቹን ጠርቶ ለእያንዳንዱ አስር ምናን ሰጣቸው ። ንግሥናውን ተቀብሎ
ሲመለስ ፤ የመጀመሪያው ቀርቦ አስር ምናን ሰጠህኝ አስር ምናን አትርፎአል ይህው ገንዘብህ ብሎ ሰጠው ንጉሱም በአስር ከተማ ላይ
ባለስልጣን አድርጎ ሾመው ። አምስት ያተረፈውም በአምስት ከተሞች ላይ ሾመው ። በመጨረሻ ጌታ ሆይ!!አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፤
ካልበተንህበትም የምትሰብስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ ስለዚህ መሬት ቆፍሬ ቀበርኩት ይህው ገንዘብህ ብሎ ለንጉሱ ሰጠው ። ንጉሡም አንተ ክፉ ፤ ሰነፍ አገልጋይ
ያላስቀመጥኩትን የምወስድ ፤ ያልዘራሁትን የማጭድ ፤ ጨካኝ ሰው መሆኔን ካውቅህ ፤ መጥቼ ገንዘቤን ከነትርፉ እንድወስድ ለምን ለሚሰሩበት
ሰዎች አልሰጠህም ? ጌታ ኢየሱስ ልንሰራበት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ሰጥቶናል ያ ስጦታ ሰርተን ፍሬ ልናፈራበት ነው ።ስለዚህ እኛ
በጎ ወታደሮች አዛዣችን ኢየሱስን በሁሉም ሁኔታ በተሰጠን ስጦታ ልናስደስተው ይገባል እንጂ እንደ ሰነፍ አገልጋይ የተሰጠን ብር
ልንቀብረው አይገባም ስለዚህ በተጠራንበት አቅጣጫ ስብከት ቢሆን ምስክርነት መዝሙር ቢሆን ጸሎት ጌታ በሰጠን ስጦታ እናገልግል።ለዚህ
ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ምሬቱን ይስጠን!! አሜን!!!
ቸር ይግጠመን!!!
ኃይሉ
ነኝ!