Saturday, March 15, 2014

ማነው ባለተራ?


ማነው ባለተራ?

በእምቢልታ በገና በውዳሴ መዝሙር

ምስጋና ለማቅረብ ለእግዚኣብሔር ክብር

ብሎ የተነሳው ትንቢተ ኢሳያስ

በቤተመቅደስ ውስጥ ጸሎቱን ሲያደርስ

እግዚኣብሔር በክብሩ ተቀምጦ ሳለ

ኢሳያስ በፍርሃት እንደዚህ ብሎ አለ

በበደሌ ምክንያት ደግሞም በኃጢያቴ

በበዳይ ሕዝብ መካከል እኔ መገኘቴ

እግዚኣብሔርን ደግሞ በዓይኔ በማየቴ

አለቀልኝ በቃ አልኖርም በሕይወቴ

እንደዚህ በማለት ኢሳያስ ሲቃትት

የሠራዊት ጌታ ይህንን በመመልከት

መላእክቱን ላከ ከሱራፌል አንዱን

የኢሳያስ ከንፈር የተቀደሰ እንዲሆን

ሱራፌልም ደግሞ ይዞ የፍም እሳት

በጉጠት አድርጎ አፉን በማስነካት

ኢሳያስ ነፃ ሆነ ከበደል ከኃጢያት

እኔኑን በድለው በጥፋት ውስጥ ላሉት

ኃጢያትን በመስራት በሞት ለሚጠፉት

ማንን እልካለሁ ማንስ ይሄድልናል

ይህንን የሚፈጽም ሰው ያስፈልገናል

ይህንን ጥያቄ እግዚኣብሔር ሲናገር

ኢሳያስ የመለሰው ያኔውኑ ነበር

በአገሬ በምድሬ ነጋሪ በማጣት

ወደሞት እየሄደ  እየጠፋ በኃጢያት

ወንድሜና እህቴ አባቴና እናቴ

በቅርቡም በሩቁ የእኔ ጎረቤቴ

ተመለስ የሚለው ከሞትና ከኃጢያት

ሰው ስላላገኘ ወንጌል የሚሰብክለት

የመንግሥቱን ወንጌል ነጋሪው በመርሳት

ወይ እኔ ከተረፍኩ ይበቃል በማለት

ስንቱ በሞት ሄደ ሳናስበው ድንገት

ወንጌል ተሸክሞ ከምዕራብ ተነስቶ

እስያ አፍሪካ አውሮፓን አካቶ

የምሥራቹን ቃል ተናግሮ አስረድቶ

እስከዛሬ አለ ሕይወት ያህል ሰጥቶ

ዛሬም አላቆመ ስራውን ይሰራል

ለደከመው ጀግና ማንስ ይተካዋል

ለነፍሳት ግድ ብሎት የሚጨነቅ ማነው?

ጌታ ሲናገረው ግልጹን ሲያስረዳው

ማንን እልካለው ማን ይሄድልኛል?

ብሎ ሲጠይቀው በተግባር የሚያውል

ዳገት ቁልቁለቱን ሞትን ሳይፈራ

መስቀል ተሸክሞ የሚወጣ ተራራ

ለጌታ የሚላክ ማነው ባለተራ?

ወንጌልን ለማድረስ የትውልድ ባላደራ

እኔ ወይስ አንተ ማነው ባለተራ?

እኔ ነኝ ባለተራ የሕዝብ ባላደራ

ለመስራት የቆረጥኩ የጌታዬን ሥራ

ይዤ መመሪያዬን የመዳን ወንጌልን

የጠፋው ወገኔን የማድንበትን

ለንስሐ ተዘጋጅ ብዬ የምልበትን

እኔ ነኝ ባላደራ ተረካቢ ትውልድ

ለሕዝቡ ለመድረስ ታሪክ የሚለኝ ግድ

ተራው የእኔ ነው ተራው የአንተ ነው

ተራው የሁላችን የአበሻ ሕዝብ ነው

    ኃይሉ ገቢ  Nov 2009

No comments:

Post a Comment