Sunday, March 17, 2013

የጠፋው በግ


                 የጠፋው በግ
  እስከ ስምንተኛ ዓመት ባለው ዕድሜዬ ፊደል የቆጠርኩት በየኔታ  ቤት  ነበር  ።   ትምህርት  ቤቱ   የሚገኘው  በቤተ ክርስቲያን ወይም  በደብር ሥር ሰለነበረ  ሳምንቱን  በሙሉ ውሎዬ በቤተክርስቲያን ዙሪያ ነበር ።  ታዲያ ከቀኖች ሁሉ ለእኔ ደስ የሚለኝ እሁድ ነበር ። ምክንያቱም በዚያን ዕለት ከየት   እንደሚመጡ   የማላውቃቸው  ሁለት  ሰዎች  ስለ ሕጻናት ትምህርት ካስተማሩ በኋላ ትናንሽ ፎተግራፍ ሥዕል ይሰጡናል እነዚያን ፎተግራፎች ከመውደዴ የተነሳ ሳምንት እሁድ ቶሎ እንዲመጣ እናፍቅ ነበር ። በየሳምንቱ  የተለያዩ ፎተግራፎች ብወስድም አንድ ፎተግራፍ ግን እስከዛሬ ልቤ ተቅርቅሮ ያለ ነው ፤ (የጠፋው በግ) በዚህ ርዕስ የተሳለ ስዕል ሲሆን ሥዕሉ እንደዚህ ነው አንድ እረኛ በግ እንደ ነበረችውና ይህች በግ ጠፍታ በማታውቀው መንገድ ሄዳ፤ ገደል ወድቃ  እየተሰቃየች ነው ፤ የበጊቱ እረኛ ደግሞ በጊቱን ከዚያ አዘቅት ለማውጣት ሐረግና ቆንጥር ይዞ እየታገለ ያሳያል በሌላ በኩል ጭልፊት ፣ ጥንብ አንሳ በግዋን ከእረኛው ቀድሞ ለመውሰድ ከገደሉ ስር ያንዣብባል ። ሰዓሊው በጥሩ  ሁኔታ ገልጾ ሥሎታል ፣ ድንቅ ስዕልና ሰዓሊ ፣ ሁልጊዜም ይህንን ስዕል ስመለከት ፈጥኖ የሚታሰበኝ ፣ምን ዓይነት ተንኮለኛ በግ ነች ? ለምን እዚህ ገደል ውስጥ ገብታ  እረኛውን ታስቸግራለች እያልኩ ነበር ። ዛሬ ግን ለእኔ ብዙ ለውጥ አለው ስለጠፋው በግ  በተለያየ  መልኩ   በብዙ    ቦታ   ተፅፎ ይገኛል በኦሪትና በአዲስ ኪዳን ፣ ለዚህ  ለተነሳውበት ሃሳብ ግን   የማቴዎስ   ወንጌል  18 ፡ 12   ዋና    መንደርደሪያዬ አደርገዋለሁ ። ይህንን ምሳሌ ጌታ ኢየሱስ ያነሳበት ምክንያት በሉቃስ ወንጌል እንደተገለጸው ቀራጮችና ኃጢያተኞች የሚናገረውን ቃል በጽሞና ያዳምጡት ስለነበረ ፣ ፈሪሳውያንና ጻፎች ደግሞ ከኃጢያተኞችና ከቀራጮች ጋር ይበላል በማለት ስላጉረመረሙ ነው ። ጌታ ኢየሱስ ለፈሪሳውያን እንዲህ አላቸው አንድ ሰው መቶ በጎች ቢኖሩትና ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋበት ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋውን ለመፈለግ አይሄድምን? ብሎ ጥያቄ ይጠይቃቸዋል ። Tyndale  Bible ሲያብራራው እንደዚህ ይላል  (ዘጠና ዘጠኙን ትቶ አንድ በግ ሊፈልግ የሚሄድ እረኛ ሞኝ ይመስላል ፣ ነገር ግን ዘጠና ዘጠኙ በሜዳ ላይ ሲተዋቸው ምንም ችግር እንደሌለባቸውና ማንም እንደማይነካቸው ያውቃል የጠፋችው በግ ግን አደጋ ላይ ነች  ምክንያቱም እያንዳንዱ በግ ከፍተኛ ግምት አላቸው) ትርጉም የእኔ ነው፤ ነገሩን ስንመለከት አንዲቷ በግ ጠፍታለች ፣ቆንጥር ይዟት ይሆናል ወድቃ ተሰብራ ሊሆን ይችላል አስቸጋሪ ገደል ውስጥ ገብታ መውጫ አጥታ እየተሰቃየች ነው ። መልካም እረኛ የጠፋችውን አንዲቱን በግ ፈልጎ ማግኘት አለበት ፣ ሞት እያንዣበባት አደጋ ላይ ያለችውን ፣ አውሬ ሳይበላት በፊት ማግኘት አለበት ፤ ጥንብ አንሳ ፣ ጭልፊት  በበረሃ የተጎዳውን ለማንሳት ስለሚያንዣብቡ ያለምንም ጥርጥር ብቻዋን ሆና ሲያገኙት ሊቀራመቷት ስለሚችሉ ፣ አደጋው ከመድረሱ በፊት በየጫካውና በየወንዙ ባለፈባቸውና ባገደመባቸው ሥፍራ ሁሉ ሊፈልግበት ወደ ሚገባው አስቸጋሪ ቦታ  መሄድ አለበት ፣  ስለዚህ እስኪያገኛት ድረስ ይፈልጋታል ።  ስለ ጠፋው በግ ምሳሌ ስንመለከት ፣ እግዚኣብሔር ለእያንዳንዱ የሰው ልጅ ፍቅር እንዳለው ያሳየናል ፣ በትንቢተ ኤርሚያስ 50 ፡ 6 ላይ  (ሕዝቤ እንደጠፉ በጎች ሆነዋል)ይላል ። እግዚኣብሔር ከማዘኑ የተነሳ፣መንከራተታችንን ተመልክቶ ነው  ሕዝቤ ብሎ በማቆላመጥ  እንደጠፉ በጎች ናቸው በማለት በቃሉ የተናገረው ፤ የጠፋ በግ ምን ያህል እንደሚንከራተት በሃሳብ ተመልከቱ ፤ እግዚኣብሔር አዳምንና ሔዋንን ፈጥሮ በመልካም ሥፍራ በገነት ውስጥ እንዲኖሩ አደረጋቸው ፣ በገነት ውስጥ ያለውን ማንኛውንም ነገር መብላት እንደሚችሉ ፣ ነገር ግን መልካሙንና ክፉውን የምታስታውቀውን ዛፍ እንዳይበሉ አዘዛቸው ፣ ኣዳምና ሄዋን ግን የኃጢያት ምንጭ የሆነውን ፍሬ በመብላት ከእግዚኣብሔር ተለዩ ከገነት ተባረሩ የመንፈስ ሞት ሞቱ ከዚያ በኋላ መንከራተት ጀመሩ በቃየል የተጀመረው ውሸት ዓለምን ሁሉ ሞላ ስለዚህ ምድር በእግዚኣብሔር ፊት በክፉ ሥራ ረከሰች በአመጻም ተሞላች በዚህ ምክንያት በዓለም ሁሉ ተበታተነና  መንከራተት ጀመረ ። በሕዝቅኤል የትንቢት መጽሐፍ እንደተጻፈው በጎቼ በየተራራው ሁሉና በየኮረብታው ላይ  ተንከራተቱ  በማለት ምን ያህል እንዳዘነልን ይገልጸዋል ፣ በጎች ምንጊዜም እረኛቸውን ተከትለው ነው የሚሄዱት ፣ እረኛውን ካልተከተሉ መንገዳቸውን ስተዋል፣ አቅጣጫቸውን ቀይረዋል  ፣ በጉድባ ውስጥ ወድቀዋል ፤ እነዚህ መንገዳቸውን  የሳቱትን ወደ መንጋው ለመመለስ ለበጎቹ ግድ የሚለው መልካም እረኛ ያስፈልጋል መልካም እረኛ ለእያንዳንዱ በግ  ግድ ይለዋል ፤ እግዚኣብሔር በማቆላመጥ በጎቼ ያለውን ሕዝብ ከዚያ ከመርገምና ከኃጢያት ለማውጣት የግድ አንድ ነገር ያስፈልግ ነበር ። ፈላጊ ፤ እረኛና ፤ ጠባቂ ። በእረኛነት ጉዳዩን ሊያስፈጽሙ ብዙዎች ተላኩ ፣ ለተንከራተተው በግ መፍትሔ ሊሆኑ አልቻሉም ፤ መፍትሔው ደግሞ አንድ ነበር እረኛው እግዚኣብሔር የጠፋውን በግ ከጠፋበትና ከኮበለለበት ወደ መንጋው መመለስ ለዚህ ደግሞ ራሱ እግዚኣብሔር ልጁን ጌታ ኢየሱስን ወደ ምድር ልኮ የጠፋውን በግ መመለስ ፣ ነጻ ማውጣት ፣ በሕይወት እንዲኖር ማድረግ ነበር ዓላማው ፤ ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ለዓለም ተሰጠ ጌታ ኢየሱስ ደግሞ ተልዕኮው ከሌሎቹ የተለየ መሆኑን ለማሳየት መልካም እረኛ እኔ ነኝ ፣ መልካም እረኛ ነፍሱን ስለበጎቹ ይሰጣል በማለት ደሙን አፍስሶ የሰውን ልጅ ሞት ሞቶ  ድሉን ከጠላት ላይ ከወሰደ በኋላ የአዳምን ዘር ከሞትና ከኃጢያት ነጻ አውጥቶ በመንፈስ ከመንጋው ጋር ቀላቀለው፤ ከዚህ በኋላ እያንዳንዱ የራሱ ምርጫ አለው ከመንጋው ተለይቶ ወደ ገደልና ቆንጥራማ መሄድ ወይም ከመንጋውና ከእረኛው ጋር መኖር ምንጊዜም ጌታ ኢየሱስ ለሚንከራተቱት ያዝናል፤ በቃሉ   (ሕዝቡም እረኛ እንደሌለው በግ ተጨንቀውና ተመልካች የለሽ ሆነው ባየ ጊዜ አዘነላቸው) ይላል አዎ!! ጌታ ኢየሱስ የሌላቸው  በዲያብሎስ እጅ ሆነው ወደ ሞት እየመራቸው ያሉ ስንቶች ናቸው? ከዚህስ በኋላ ወደ ሕይወት እንዲመለሱ የማድረግ ሐላፊነቱ የማነው? እረኛ እንደሌላቸው በጎች ለሚንከራተቱት ማን ፈጥኖ ይድረስላቸው ? ጌታ ኢየሱስ አንድ ትህዛዝ ሰጥቶአል ወደዓለም ሁሉ ሄዱ ለፍጥረት ወንጌልን ተናገሩ፤ የጠፉትን ነፍሳት ከሞት፣ ከሸለቆ፣ ከጠላት ወጥመድ ነፃ ሊያወጣ የሚችል የተላከ ብቻ ነው፣ ተልከሀል? አዎ ተልከናል እኛ የክርስቶስ አምባሳደሮች ነን አምባሳደር ደግሞ ለአገሪቱ ተወካይ ነው እኛም የሰማይ አገር ተወካይ ስለሆንን ስለተውከልንበት ሰማያዊ አገር ወንጌልን ልንናገር፣ ልናስረዳ፣ ልንመልስ የሚገባውን የአምባሳደርነት ሥራ ልንሰራ ሐላፊነት አለብን፣ የአምባሰደርነታችንን ሐላፊነት ባንፈጽም ተጠያቂ ነን፤ በጌታ ኢየሱስ በደሙ የተዋጀ ክርስቲያን የአምባሳደርነት ሥራውን መፈጸም አለበት፣ እረኛ እንደሌላቸው ሲባዝኑ ለሚታዩ ሕዝቦች ወንጌልን ልናደርስላቸው ግዴታችን ነው። ሹመቱን ብቻ ሳይሆን ሥራውንም መስራት አለብን ጳውሎስ እንደተናገረው ወንጌልን ባልናገር ወዮልኝ እንዳለውና እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ቃሉን በአደባባይ እንደመሰከረው እኛም ለጠፉት ነፍሳት ግድ ብሎን ወደ ሕይወት እንዲመለሱ ወንጌሉን እንናገር!!                                            
                                                              በቸር ይግጠመን!!!
                                                              ኃይሉ ነኝ!!! 2008

Saturday, March 16, 2013

እንደዚህ ነበረ!!


እንደዚህ ነበር!!
ከአገሬ ወጥቼ ከሰው አገር ብገኝ
ከዓመታት በኋላ አገሬ ናፈቀኝ
ከቤተሰቦቼ መልእክት ቢደርሰኝ
አገሬን ለማየት ናፍቆቱ አደረብኝ
ናፍቆቴ ቢታጨቅ በብዙ ነገሮች
ቆርጪ ተነሳሁ ላያቸው ወገኖች
ከዚህ በተረፈ በሚተርፈኝ ጊዜያት
ወዲቱ ኢትዮጵያን አገሬን ለመጎብኘት
ወንዝ ተራራዎችን የታሪክ ገዳማት
የጀግኖች ወገኖቼን የሰማዕታት ዐውልት
ለማየት ጓጓሁኝ የአገሬን አራዊት
በሃሳብ ሆኜ ይህንን ስመለከት
ወስኜ ተነሳሁ ለመሄድ አገር ቤት
ትኬቴን ቆርጪ የምሳፈርበት
ቀጠሮዬን ይዤ ልክ በዚያው ዕለት
ወደኢትዮጵያ ምድር እኔ የምጓዝበት
ለቤተሰቦቼም ስልክ ደውዬላቸው
የምደርስበት ሰዓት በውል ነገርኳቸው
ስጦታዬን ይዤ ሻንጣዬን ቀርቅቤ
ብርድም እንዳይመታኝ ልብሴን ደራርቤ
እንደተዘጋጀው ለመሄድ ለመብረር
ስልክ ተደወለልኝ በአጋጣሚ ነገር
ዚስ ኢዝ ኃይሉ ስፒክ
ለደወለልኝ መልሴ ለወዲያኛው መድረክ
ዩር ፕሮግራም ትራንስፈር
ዋት? ዉ ኢዝ ስፒከር
መልስ ሳይሰጠኝ ድርግም አደረገው
ከእንቅልፌ ባንኜ ጉዳዩን ሳስበው
በውኔ ሳይሆን ለካስ በሕልሜ ነው
የዚያን ዕለት እንደዚህ ነበር
ለወሬ የማይመች ደግሞም ለመናገር
በአየር ተሳፍሬ ልገባ አገሬ
ካርቱምን አልፌ ስደርስ ወደምድሬ
የአየር ጎረቤቴ አጠገቤ ያለው
የያዝከው ፓስፖርት የካናዳ ሕዝብ ነው
እንደአነጋገርህ የት ነው የምትኖረው
ከአገርህ ውጪ የቆየህ ትመስላለህ
ኢትዮጵያ ስትገባ ተቀባይ ሰው አለህ?
ወይስ ከተማውን በደንብ ታውቀዋለህ
የማታውቀው ከሆነ እኔ አውቀዋለሁ
መኪናም ስላለኝ እኔ አደርስሃለሁ
በጉዳዩ ተስማምተን ዕቃ ተቀብለን
ከመኪናው ሥፍራ እየገፋን ደርሰን
ከመኪናው ጀርባ ዕቃችንን ጭነን
ተሽቀዳድሞ ሮጦ ጋቢና ገባና
ሞተሩን አሙቆ ማርሹን አስገባና
መንገዱን ቀጠለ እኔን ተወኝና
እጆቼን ዘርግቼ እየሮጥኩ በፍጥነት
አምቧርቅ ጀመረ ሌባ ያዙ በማለት
የጩኸቴ ሲቃ ሕዝቡን አስደንግጦት
እንደዕብደት ያረገኝ ያመመኝ መስሎት
እጆቹን አንስቶ ያዝ ሲያደርገኝ
ከሄድኩበት ዓለም ወዲያው ሲመልሰኝ
እዚያው አይሮፕላን ውስጥ ከጓደኛዬ ጋር ነኝ
የዚያን ዕለት እንደዚህ ነበር
ለወሬ የማይመች ደግሞም ለመናገር
                   በቸር ይግጠመን!!
                   ኃይሉ ነኝ!!2008

ተስፋዬ እግዚኣብሔር ነው!


ተስፋዬ እግዚኣብሔር ነው።
ያኔ በለጋነት ያኔ በልጅነት
ሕይወቴን ሲነካት ነፍሴን ሲያስጨንቃት
አምላኬን አወቅሁት ጌታን ተረዳሁት
ልቤን ከፈትኩለት በልቤ አስገባሁት
እኔ ልገዛለት ራሴን ሰጠሁት
በፊቱ ተንበርክኬ በፀሎት ጠየቅሁት
መድኔን ላልክደው ቃሌን ገባሁለት
ዓለም አሳይታኝ ሳቅና ፈገግታ
ያላት መስሎኝ ደስታ የምትሰጥ እርካታ
ወዲያ ወዲህ ስትል ነገር ስታስመስል
ያላት መስሎኝ ፍቅር እኔኑን ስትሰልል
ዓለምን ተጠጋኋት እርሷን ተከተልኳት
ለካስ እሳት አላት የምትፋጅ ናት
የምታቃጥል ናት የምታደርስ ከሞት
እንዲህ አደረገችኝ ወደእርሷ ሳበችኝ
ፈገግታ አሳይታኝ በእጅዋ አስገባችኝ
በውስጥዋ አስገብታ የምትሰጥ መስላ ደስታ
እንደኳስ ለግታ በሥጋዬ ተጫውታ
ሞራሌንም መትታእኔን አንገላታ
ምልክቷን ትታ ስጦታዋን ሰጥታ
ለፍርድ በአደባባይዋ ቁም ስቅሌን አሳይታ
አንተ የእኔ አይደለህም ለእኔ አትጠቅምም
 ጤና አትሰጠኝም  ፍፁም አትሆነኝም
በአዋጅ በነጋሪት ይህንን ስትገልጽልኝ
ጌታን በመንበርከክ ንስሐ ጠይቅሁኝ
ለዘለዓለሜ ማገልገል ጀመርኩኝ
ጌታ እንደዚህ አለኝ ዳግም ተናገረኝ
አንተ የእኔ ነህ እኔም የአንተው ነኝ
በቅዱሱ ደሜ አንተን የገዛሁኝ
በዘመንህ ሁሉ አንተን እጠብቃለሁ
በምትሄድበት መንገድ እኔ በዚያ አለው
መልካምነቴንም በፊትህ አሳያለሁ
ጊዜ ዘመን አልፎ ዘመንን ተክቶ
የሕይወት ውጣ ውረድ ኑሮዬን አዛብቶ
ብረር ብረር አለኝ ካናዳ ሊያኖረኝ
የኑሮ ሐዲዱ መሪው አሻገረኝ
በቤት በአደባባይ ሰው እያደረገኝ
እስከዛሬ ድረስ እኔም ከእርሱ ጋር ነኝ
ሌላውን የተስፋ ቃል እጠብቃለሁኝ
ዓመት ሁለት ዓመት ከነፉ ዓመታት
አምላኬ ለእኔ ቃሉን የሰጠበት
በአምላኬም ፈቃድ ጉዞ የጀመርኩበት
እምባዬን አብሼ ቅኔ የተቀኘሁበት
ሙሉ ነጻነቴን የተቀዳጀሁበት
ወደ ዓለም አልሄድም ወይ እርሷ አትመጣም
ቃለ መሐላዬን ከእንግዲህ አታጠፋም
ዓለምን ፈልጋ ወደምድርዋ አልጓዝም
እርሷም  አትመጣም እኔም አልሻትም
ጌታ የሰጠኝን በእርሷ ፊት አልጥልም
ቃል የገባልኝን ፍፁም አልዘነጋም
እንደሚፈጽምልኝ ምንጊዜም አልረሳም
ለእኔ የተናገረው ወደፊት ሊያደርገው
ታማኙ ጌታዬ ሁልጊዜም ታማኝ ነው
ሸለቆ ባይሞላ ሐሩር ቢያደርቀው
ከብቶች ባይኖሩኝ በእምነት የማግደው
በእጆቼ የያዝኩት ወርቅ አልማዝ ምቆጥረው
ቤቶች ባልገነባ ጎጆዬ ነው የምለው
ሁሉን እስኪያደርግልኝ እሱ እስኪፈጽመው
በመጠበቂያዬ በአምባዬ እቆማለሁ
አንድ ነገር ብቻ እኔ እረዳለሁ
ሁሉን የሚያደርገው ተስፋዬ እግዚኣብሔር ነው
                           በቸር ይግጠመን!!!
                          ኃይሉ ነኝ!! 5/12/2006

Friday, March 15, 2013

ምክንያቴ ብዙ ነው!!


ምክንያቴ ብዙ ነው!!!
ዘርዝሬ ልገልጸው በአፌ ልናገረው
ምሥጋና አቅርቤ እኔ የማልጨርሰው
ያደረገልኝ በቁጥር የማልገልጸው
እግዚኣብሔር አምላኬን የማመሰግነው
የውለታው ብዛት ቁጥር ሥፍር የለው
 ለጌታ ለአምላኬ ክብር የምሰጥበት
በገናዬን ይዤ ቅኔ የምቀኝበት
በእጆቼ አጨብጭቤ ስለት የማገባበት
ፅናጽሉን ለእርሱ ሿሿ የማሰኝበት
ምክንያቴ ብዙ ነው ጌታን የማከብርበት
ጠላቴ ሊጥለኝ እንደአመድ ሊረግጠኝ
አለቀለት በቃ ልገድለው ነው ሲለኝ
ዕድሜውን ልቀጨው ወደሞት ልወስደው
ይህንን ቃል ዝቶ ወጥመድ አዘጋጅቶ
ሕይወቴን ሊያጠፋ ጠላት ተዘጋጅቶ
መሣሪያ አበላሽቶ ብሎኖቹን ፈትቶ
ሳላስበው ድንገት እኔን አዘናግቶ
ሊገድለኝ ሲያደባ
ሊከተኝ ከጉድባ
የመሞቴን አዋጅ በጉራ ሲያውጅ
ጌታ ኢየሱሴ አወጣኝ ከሞት ደጅ
ከመሞት አድኖኝ በክብር ላቆመኝ
ይህንን ስላደረገ ክብር እሰጣለሁኝ
ድምጼን ከፍ አድርጌ ላዜም ለጌታዬ
ልደርድረው እኔ ይናገር በገናዬ
እርሱ እንዲቀበለው ላቅርብ ምሥጋናዬ
ሌላ ምንም የለኝ ይህ ነው ችሎታዬ
ጠላቴ ዔላማው ሁለት እጆቼን ጎምዶ
በሚሆነው ነገር እኔኑን አናዶ
እጆቼ እንዳይጽፉ
ቃሉን እንዳያስፋፉ
የደካከሙት ተስፋ የቆረጡት
በሚያወጣው ቃላት እንዳይጽናኑበት
ነበረ ዕቅዱ የሰው ልጆች ጠላት
ጌታ አድኖኛል ከሞት አትርፎኛል 
ምን ብዬ ላመስግን ቃላቶች ያጥሩኛል
መስንቆዬን ልቀኝ እስቲ ዜማ ያውጣ
ከበሮው ይከበር ክብርን እንዲያመጣ
ላሸብሽብ ልጨፍር ለአምላኬ ለጌታ
እሱን ካስደሰተው ለሰራው ውለታ
የጠላቴ ሃሳብ የእርሱ ፍላጎት
በእኔ ሊፈጽመው የነበረ ምኞት
መጻፍ መናገሬን ይህንን ተመልክቶ
የእጆቼን ውጤት በክፉ ዓይኑ አይቶ
ሰዎች በመባረክ ስላገኙ ትምህርት
ጠላቴ እንዲህ አለ እጁን ብቆርጥለት
የአመልካች የአውራ ጣት ከሥራ ባስወጣት
ቁርጥ አድርጌለት እንዳትጽፍ ባደርጋት
እጁ እንዳይሰራ ችግር ብፈጥርበት
በምላሱ አይጽፍ ፋይሉን ብዘጋለት
ነበረ ምኞቱ አልሆነም ድርጊቱ
ጠላቴ ደከመ ለፋ እንዲያው በከንቱ
ጌታዬ እንዳለው እንደተናገረው
ለእኔ እንደጋብልኝ ዘላለማዊ ተስፋው
ጠላቴ በእኔ ላይ ደግሞም በሰውነቴ
አንዳችም አልቻለም ሊያደርግ በሕይወቴ
ዛሬ ለጌታዬ እጆቼ ይጽፋሉ
ያጨበጭባሉ ክብርን ይሰጣሉ
አፌን እከፍታለሁ ቅኔን እቀኛለሁ
ማዕሌተ ቅኔ ለጌታ አቀርባለሁ
እግዚኣብሔር ይመስገን ብዬ እዘምራለሁ
ሌላ ምንም የለኝ ለጌታ እማቀርበው
ጌታ ያደረገውን ቆጥሬ አልችለው
የማመሰግንበት ምክንያቴ ብዙ ነው
                   በቸር ይግጠመን!!
                  ኃይሉ ነኝ!! 2006