Thursday, March 7, 2013

ጊዜውን አንስረቅ!!


ጊዜውን አንስረቅ
ለሁሉም ጊዜ አለው ሰለሞን በቃሉ
እንደተናገረው ፤ እርግጥ ነው በሙሉ
ሲወለድ፤ ለማደግ በጊዜው በሰዓት
 ለሁሉም ጊዜ አለው ለመኖር ለመሞት 
በጊዜው ለመውደድ ፍቅርንም ለመስጠት
ሁሉም ይፈጸማል በዓለም ሳለን በሕይወት
ለመብላት ለመጠጣት ወይም ለመዝናናት
 ለመጨፈር ይሁን ራስን ለማርካት
ለዕረፍት ጊዜ አለው ሰላምን ለማግኘት
ጊዜ ይገዛዋል ለዓለም ሁሉ ፍጥረት
ገበሬው ተነስቶ ጓዶቹን ሰብስቦ
የእርሻ መሬቱን በግልም ፤  በደቦ
መሬቱን ለማሳ ፤ ለተክል ለማዘጋጀት
ከለፋበት መሬት ፍሬውን ለማግኘት
በጠዋት ተነስቶ ጓሉን የሚጎለጉል
ሳምንት ሳይበቃው ስራው ላይ የሚውል
ወራቱን ጨርሶ ዓመት የሚያጋምስ
እርሻውን በማለስለስ ጊዜውን የሚጨርስ
አራሹ ገበሬ ለእርሱም ጊዜ አለው
ዓመቱን በሙሉ በጊዜ የሚሰራው
መሬት ለማለስለስ ፤ እርሻውን ለማረስ
ለሥራው ጊዜ አለው ጓሉን ለመከስከስ
ገበሬው ተኝቶ ዓመቱን ያለስራ
ክረምት ሲመጣ ፍሬውን ቢዘራ
በመጨረሻ ላይ ርሃብ ነው መከራ
ጊዜውን ጠብቆ ክረምት ከመምጣቱ
ፀሐይ ባለችበት ዝናብ ከመብዛቱ
በጊዜው በሰዓቱ ቢያረስ መሬቱን
ቀጥሎም በጊዜው ቢጎለግል ጓሉን
ሰኔ ሲመጣለት ምድሩን ቢገለብጥ
በጊዜው ቢጠቀም ያገኛል ጥሩ ለውጥ
ተማሪው እያለ ሆኖ በትምህርት ቤት
ትምህርቱን አቋርጦ አይችልም መጫወት
በመማሪያ ጊዜ አይሄድም ለዕረፍት
ተማሪም ጊዜ አለው ሳለ በት/ቤት
በዓለም የሚኖር ለሁሉም ጊዜ አለው
በመጀመሪያ ዕለት አምላክ የፈጠረው 
ለአንዳንድ ሰው ደግሞ ጊዜ ሲያልፍበት  
መንጋቱን  መምሸቱን በዚህ በመደሰት
ጊዜው እንደሚያልፍ ፍፁም ሳይመለከት
አምላክ የሰጠውን ጊዜውን በመስረቅ
ጊዜውን ይጨርሳል ሴኮንድን በመናቅ
ሙሽራ ነኝ እኔ ፤ ሙሽራ የምጠብቅ
እንደሚመጣልኝ ፤ ተስፋ የማደርግ ከሩቅ
ዘይቴን ሞልቼ ፤ መብራቴን አብርቼ
ቢቆይም ቢመጣ ጊዜዬን ለይቼ
እየጠበቅሁ ነኝ ፤ ጊዜዬን ገምቼ 
ለእኔ ጊዜዬ ፤ ወርቅ ና አልማዝ ነው
ሴኮንድ ና ሰዓት አምላክ የፈጠረው
ጊዜውን ለማወቅ ሰዓት የተሰራው 
ሥራዬን ለመስራት ጊዜ የተገደበው
ሰዓቱን ጠብቂ ልኖርም ጭምር ነው
በሰዓት በጊዜ ችግር የገባችሁ
የጊዜ አጠቃቀም ውሉ የጠፋባችሁ
ጠይቁት የሱስን መፍትሔ አለላችሁ
             በቸር ይግጠመን!!!
               ኃይሉ ነኝ! 2005


ምክንያቴ ብዙ ነው!!



ምክንያቴ ብዙ ነው

ዘርዝሬ ልገልጸው በአፌ ልናገረው
ምሥጋና አቅርቤ ፍጹም የማልችለው
እግዚኣብሔር አምላኬን የማመሰግነው
ምክንያቴ ብዙ ነው
ምክንያቴ ብዙ ነው ጌታን የማነግስበት
ለጌታ አምላኬ ክብር የምሰጥበት
በገናዬን ይዤ ቅኔ የምቀኝበት
በእጆቼ አጨብጭቤ ስለት የማገባበት
ምክንያቴ አይቆጠር ጌታን የማከብርበት
ጠላቴ ሊጥለኝ እንደአመድ ሊረግጠኝ
አለቀለት በቃ ልገድለው ነው ሲለኝ
ዕድሜውን ልቀጨው
ወደ ሞት ልወስደው
ይህንን ቃል ዝቶ ወጥመድ አዘጋጅቶ
ሕይወቴ ሊያጠፋ ጠላት ተዘጋጅቶ
ስላስበው ድንገት እኔን አዘናግቶ
መሣሪያ አበላሽቶ
ብሎኖቹን ፈትቶ
ሊገድለኝ ሲያደባ
ሊከተኝ ከጉድባ
የመሞቴን አዋጅ በጉራ ሲያውጅ
ጌታ ኢየሱሴ አወጣኝ ከሞት ደጅ
ከመሞት አድኖኝ በክብር ላቆመኝ
ለዚህ ድንቅ ጌታ ክብር እሰጣለሁኝ
ድምፄን ከፍ አድርጌ ላዚም ለጌታዬ
ልደርድረው እኔ ይናገር በገናዬ
ላደረገው ሁሉ ላቅርብ ምሥጋናዬ
ሌላ ምንም የለኝ ይህ ነው ችሎታዬ
ጠላቴ ዒላማው ሁለት እጆቼን ጎምዶ
በሚሆነው ነገር እኔኑን አናዶ
እጆቼ እንዳይጽፉ
ቃሉን እንዳያስፋፉ
የደካከሙት ተስፋ የቆረጡት
በሚጽፈው ቃላት እንዳይጽናኑበት
ነበረ ሃሳቡ የሰው ልጆች ጠላት
ጌታ አድኖኛል ከሞት አትርፎኛል
ምን ብዬ ልበለው ምሥጋና ያንሰኛል
መሰንቆዬን ልቀኝ እስቲ ዜማ ላውጣ
ከበሮው ይከበር ክብርን እንዲያመጣ
ላሸብሽብ ልጨፍር ላምላኬ ለጌታ
እሱን ካስደሰተው ለሰራው ውለታ
የጠላቴ ሃሳብ የእሱ ፍላጎቱ
በእኔ ሊፈጽመው ነበረው ምኞቱ
መጻፍ መናገሬን ይህንን ተመልክቶ
የእጆቼን ውጤት በክፉ ዓይኑ አይቶ
ሰዎች በመባረክ  ስላገኙ ትምህርት
ጠላቴ እንዲህ አለ እጁን ብቆርጥለት
የአመልካች ፤ የአውራ ጣት ሁሉን ብጎምድለት
ከሥራ አስወጥቼ እንዳትጽፍ ባደርጋት
ሞራሉ እንዲነካ ችግር ብፈጥርበት
ፋይሉ ይዘጋል
ነገሩ ይቆማል
ነበረ ምኞቱ
አልሆነም ድርጊቱ
ጠላቴ በእኔ ላይ ደግሞም በሰውነቴ
አንዳችም አልቻለም ሊያደርግ በሕይወቴ
ዛሬ ለጌታዬ እጆቼ ይጽፋሉ
በአደባባዩ ክብርን ይሰጣሉ
ያጨበጭባሉ ቅኔን ይቀኛሉ
ዛሬ የእኔ ጌታ ዕረፍትን ሰጥቶኛል
ምሥጋና ብሰጠው ለእርሱ ያንስበታል
አፌን እከፍታለሁ ቅኔን እቀኛለሁ
ማዕሌተ ቅኔን ለእርሱ አቀርባለሁ
እግዚኣብሔር ይመስገን ብዬ እናገራለሁ
ሌላ ምንም የለኝ ምሥጋናዬ ይኽው
ምክንያቴ ግን ብዙ ነው
        በቸር ይግጠመን!!
        ኃይሉ ነኝ! Mar 31/2006    

የሰው የሆነውን


የሰው የሆነውን


ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም የወደፊቱ አገራችን
ጌታችን ኢየሱስ ለእኛ የመረጠልን
ለዘላለም አምራ ደምቃ የምትኖረው
በሰንፔር ፤ ሰርዲኖን በከበረ ድንጋይ የተገነባችው
የከተማዋ መንገድ መስታወት በሚመስለው
በጠራ ንፁህ ወርቅ የተመሰረተችው
ሃያ አራት ሰዓት በሩ ክፍት የሆነው
የእግዚኣብሔር ክቡር በግ የሚያንጸባርቅላት
ፀሐይና ጨረቃ መቼም የማያሻት
አመንዝራ ርኩሰት ፍፁም የሌለባት
ውሸት የሚናገር የማይገባባት
ፀያፍ የሆነ ነገር የማይደርስባት
በአንድ ተሰብስበን የምንኖርባት
ጌታ ኢየሱስ የሁላችን አባት
ቅዱስ ቅዱስ ብለን የምንሰግድለት
ለዚች ውቢት አገር በጌታ ተመርጠን
የመሄጃውን ጊዜ መናፈቅ ሲገባን
በሰው አገርና በሰው ምድር እየኖርን
የሰው የሆነውን እንናፍቃለን
            በቸር ይግጠመን!!
            ኃይሉ ነኝ!! Mar 2013 

Monday, March 4, 2013

ድርሻው የእግዚኣብሔር ነው!!!

ድርሻው የእግዚኣብሔር ነው
ገና በጠዋቱ አብርሃም ሲጸልይ
ዓይኖቹ ተከፍተው ሲያይ ወደ ሰማይ
የሰራዊት ጌታ ሆኖ በክብሩ ላይ
እግዚኣብሔር ለአብርሃም እንደዚህ ጠየቀው
ምንም ሳያቅማማ መልስ እንዲሰጠው
እግዚሔር የፈተነው እንደዚህ የሚል ነው
እኔ የሰጠውህን በእርጅና ዘመን
አንዱ የምትወደውን ልጅህ ይስሐቅን
እኔ በማሳይህ በሞሪያ ተራራ
መስዋዕት አድርገህ ስጠኝ ሳትራራ
የእግዚኣብሔርን ጥያቄ ነገሩን አድንቆ
ማንም እንዳይጎዳ መንፈሱን ጠብቆ
የሚያደርገውን ሁሉ በኃይል ተጠንቅቆ
እንጨቱ እንዲነድ በደንብ ሰነጣጥቆ
መለኮሻ የሚሆን እንደያዘ እሳቱን
በሌላኛው እጁ ስላታም ቢላውን
በንጋት በጠዋት አዘጋጅቶ ሁሉን
አህያውን ጭኖ ጀመረ ጉዞውን
ከተጓዘ በኋላ ሶስት ቀንና ሌሊት
ልጁን ይስሐቅን ለእግዜር የሚሰዋበት
በሩቁ ተራራውን ሞሪያን ሲያዩት
አህያ ከነጓዙ በዚያ ስፍራ ትቶ
አብርሃም ሁለቱን ሎሌዎችን ጠርቶ
ጉዳዩን ነገራቸው ሚስጥሩን አስረድቶ
እናንተ እዚህ ቆዩ ጠብቁ አህዮችን
መስዋቱን ለማቅረብ እኛ እንሄዳለን
ለአምላክ የሚገባውን እንሰግድለታለን
መሰዋቱን አቅርበን ክብርን እንሰጣለን
እዚህ እንድትጠብቁን እኛ እንመጣለን
ወደሞሪያ ተራራ በመውጣት ላይ ሳሉ
ይስሕቅና አብርሃም እንዲህ ተባባሉ
እሳቱና እንጨቱ ይህው በእጄ ነው
ቢላው እንደሆነ በጣም የተሳለው
ካንተ ጋር ነው ያለው
ከዚህ በተረፈ እጃችን ባዶ ነው
የመስዋዕቱ በግ ለእግዜር የሚሰዋው
ወዴት ነው የሚገኘው?
ይህንን ጥያቄ ይስሐቅ ሲጠይቀው
በፍጥነት ነበረ አብርሃም የመለሰው
እኛ አዘጋጅተናል ቢላዋና እሳት
ለመንደድ እንዲያመች የተሻለ እንጨት
 ለአምላካችን የሚሆን መስዋዕት
ድርሻው የእግዚኣብሔር ነው በግ ለማዘጋጀት
                በቸር ይግጠመን!!
                ኃይሉ ነኝ!





ልዑል


     ልዑል
እግዘኣብሔር  ከጥንቱ  የተናገረለት፤
ኢሳያስ  ሚክያስ  የተነበዩለት፤
ዳዊት  በውዳሴ  ለእርሱ የገለፀለት ፤
ዮሐንስ ጎዳና ጠርጎ ያዘጋጀለት፤
የምሥራቹን ቃል  ሱራፌል መላእክት
ተወልዶአል ብለው የመሠከሩለት፡፡
ልዑል የእግዚኣብሔር ልጅ
መሲህ  የዓለም ወዳጅ
ተወልዶአል  አማላጅ፡፡
ገና  ጥንት  ከዘመናት   በፊት
እግዚኣብሔር  ለዳዊት ቃል እንደገባለት
ጦረኛ  ስለሆንክ  ስላለ በእጅህ  ደም
ቤቴን ልትሰራ አንተ አትችልም
ቤቴን የሚሰራው  ከአብራክህ  የሚወጣው
ያንተ ልጅ ብቻ  ነው
ከአብራክህ  የሚወጣው አንተ የምትወልደው
ልዑል የእግዚኣብሔር  ልጅ  ተብሎ ሚጠራው
ዙፋኑ ዘለዓለም  የማይናወጥ  ነው
የሰው ልጅ  አዳኝ ነው ከአንተ  የሚገኘው፡፡
ስለእርሱ የገለፀው ነቢዩ  ሚክያስም
አንቺ  ቤተልሄም  ታናሽ ብትሆኝም
 ከቁጥር ባትገቢም ሰው ባያስብሽም
የእስራኤል ገዥ ከአንቺ ይወለዳል
የእግዚኣብሔር ክብር በአንቺ ይገለፃል፡፡
ከብዙ  ዓመታት ከዘመናት በፊት
እንደተናገረው ኢሳያስ  በትንቢት
እነሆ ድንግል ልጅን ታረግዛለች
ወን ድ ልጅም ደግሞ እርሷ ትወልዳለች
ስሙን አማኑኤል ብላ  ትለዋለች
የእግዚኣብሔር ክብር በእርሱ ይገለፃል
ሰው ሁሉ በአንድነት ልዑሉን ያዩታል፡፡
አዳምና ሄዋን በገነት ውስጥ ሳሉ
የተከለከለውን በለስ ስለበሉ
ኃጢያትን በደልን በመፈፀማቸው
አትብሉ ተብለው ያን በመብላታቸው
ልዕል እግዚኣብሔርን በማሳዘናቸው
ሁለተኛ ጥፋት  እንዳይገኝባቸው
ከገነት አባሮ በሩን ዘጋባቸው
በአዳም ምክንያት ደግሞም በበደሉ
አዳምና ሄዋን ፍጥረታት በሙሉ
ከእርግማን በታች ሁሉም  በመዋሉ
እግዚኣብሔር አምላክም ይህንን በመመልከት
ሊያድነው ፈለገ  ከተፈረደበት 
ፍጥረት እንዲሻገር ከሞት ወደ ሕይወት
በዋኔስ  ሞከረ   አልተሳካለትም
ከሞት ወደ ሕይወት አልተሸጋገረም
ባደረገው  በጎ  ከመሞት  አልዳነም
በጥቦት  ባውራ በግ በፍፁም አልሆነም
በሁሉም ሙከራ ሰው ነጻ አልወጣም፡፡
ስለዚህ መፍትሔው የአዳም መዳኛው
ልጁን  ላለም ፍጥረት በመስጠት ብቻ ነው፡፡
ስዓትና  ጊዜ  ዕለታቱ  ሲደርስ
የአዳም ዘሪያ ከሞት ለመመለስ
ተወለደ  ልዑል አዳኝ የእግዚኣብሔር ልጅ
የፍጥረታት ጌታ የሰው ልጅ አማላጅ፣፣
ሰባ  ሰገሎች  የምድር ጠቢባን
የተነገረው ቃል ተግባራዊ እንዲሆን
ከምሥራቅ ተነስተው  በኮከቡ ምሪት
ቤተልሔም ድረስ እሱ እስካለበት
ዕጣንና  ከርቤ  ወርቅ አልማዝ  ስጦታ
ይዘው መጥተውለት  ለሕፃኑ ለጌታ
በእግሩ ሥር ሰገዱ ተገቢውን ሰላምታ፣፣
   ተወለደ ልዑል ተወለደልን
   ከኃጢያትና ከሞት እኛኑን ሊያድን
   በአነስተኛ ሥፍራ እርሱ የተወለደው
   ልዑሉ  ተዋርዶ  እኛን ሊያከብር ነው፣፣
   ታዲያ?
  የእግዚኣብሔር ልጅ በልብህ ተውልዶአል?
   ልዑሉን  በልብህ ሥፍራ ሰጥተህዋል?
   በእርግጥ በአዳኝነት ተቀብለህዋል?
  ወይስ በዘልማድ ጉዞ ጀምረሃል!!
ልዑል በሕይወትህ ሊወለድ  ይገባል።
                       በቸር ይግጠመን!!
                       ኃይሉ ነኝ Dec 24/2008.
                         

መክሊት


   መክሊት (ሉቃስ19፥12-27ማቴ 25፥14-30)
በአንድ ከተማ ውስጥ በጣም ትንሽ መንደር
ክቡር የተባለ አንድ መስፍን ነበር
ከዋናው ከተማ ርቆ ካለው ግዛት
ከንጉስ መኖሪያ መልእክት ቢመጣለት
ንግሥና ሊሰጠው ክብር ሊጨመርለት
ቶሎ እንድትመጣ ብለው ቢልኩበት
ወደዚያ ከተማ ከመሄዱ በፊት
ካሉት አገልጋዮች አስሩን ሰብስቦ
ሳይበዛም ሳያንስም መጠኑን አስቦ
ለአሰሩም አገልጋይ ታማኝ ነው ላላቸው
ታላንትና ምናን አካፍሎ ሰጣቸው
ሰርተው እንዲያተርፉ ምክርም ለገሳቸው
ከመስፍኑ አሽከሮች አንደኛው እኔ ነኝ
ከገንዘቡ ቆጥሮ በእጁ የተሰጠኝ
መነገድ አላውቅም ዛሬ አልማርም
የመስፍኑን ምክር እኔ አልዘነጋውም
ከመቸርቸሪ በፊት ነጋዴ ከመሆኔ
በቤቴ መድረክ ላይ ቁጭ ብዬ እኔ
ንግድን ስለማላውቅ ስራው እንዳይከብደኝ
እመራመር ጀመር ሃሳብ ውስጥ ገባሁኝ
ሳወጣና ሳወርድ ማጥናት መቀመሩን
ውሳኔ ላይ ደረስኩ ለእኔ የተሻለውን
ገበያ ወጥቼ መነገድ ብጀምር
ሥራ ስለማላውቅ ገንዘቡን ባከስር
ጌታዬ ሲመጣ እሱ የሚያደርገው
መክሰሬን ሲያውቅው ወህኒ ሊያወርደኝ ነው
ስለዚህ ገንዘቡን እኔ ምን ላድርገው
በጨርቅ ጠቅልዬ አልጋ ውስጥ ላስቀምጠው
አይሆንም ሃሳቡ ሳስቀምጥ ያየኝ ሰው
በሌለውበት ሰዓት ገንዘቡን ቢሰርቀው
ጌታዬ ሲመጣ እኔ ምን እላለሁ
እሱ እንደሆነ ጨካኝ አለቃ ነው
ማድረግ የሚገባኝ ለእኔ የሚሻለው
ሰው ሳይምለከት ጉድጓድ ውስጥ ብቀብረው
ጌታዬ ሲመጣ አውጥቼ እሰጣለሁ
የእኔ ምርጫዬ የሚመስለው ይህ ነው
አንተስ ከየትኛው ወገን ነው ያለህው?
የምትጠቀም ነህ መክሊቱን መንዝረህ
ወይስ እንደእኔ መክሊት ቀብረህ ያለህ ?
ጌታችን ኢየሱስ ሲሄድ ከምድራችን
ለእያንዳንዱ ምዕመን ሰጥቶናል መክሊትን
ነግደን አትርፈን ዘር እንዲበዛልን
አንዱ ለማስተማር ሌላው ለመዘመር
የመዳንን ወንጌል ለሕዝብ ለመናገር
ሌላው ማስተዳደር ነገሩ እንዲሰምር
ደግሞም  በሓዋርያነት ያጠፋን ለመምከር
ሁሉም ተሰጥቶታል በጌታ ቤት ሲኖር
መክሊቱን ተጠቀም ለዘላለም ሕይወት
ድንገት ጌታ መጥቶ እንዳትሄድ ወደሞት
                  በቸር ይግጠመን!!
                  ኃይሉ ነኝ! Jan2009 

Sunday, March 3, 2013

ታጥቄአለሁ!!


ታጥቄአለሁ
እንዲሁም “ወደ መላው ዓለም ሂዱ ለሰው ሁሉ
ወንጌልን አስተምሩ    ማርቆስ 16 ፡ 15

ገና በሕጻንነት በጨቅላነት ሳለሁ
ወንጌል ለመናገር ነበር የማስበው
እያደግኩህ  ስመጣ በአህምሮ ስበስል
ጌታ በሰጠኝ በር እርሱን ሳገለግል
እርሱ የሰጠኝን ለሕዝብ ሳካፍል
በሕዝብ በወገኔ ሞገስን ሲሰጠኝ
ፈረንጅ አገር ሄዶ መኖሩ አማረኝ
ታግዬ ላልጥለው ከአምላክ ጋር ታገልኩኝ
ፈርምልኝ ስለው አይጠቅምህም ሲለኝ
የመውጫ መንገዴን  ዲቪዬን መረጥኩኝ
በሥጋ ዬ ፈቃድ ድንበር ተሻገርኩኝ
ድንበር ተሻግሬ መች በቅጡ ኖርኩኝ
ሥራ ሥራ እያልኩ ጧት ማታ ስዳክር
ፍጹም ረሳሁት መስጠት ለጌታ ክብር
አሁንስ ተነሳው ታጥቄ ወገቤን
በተቻለኝ አቅም ልረዳ ወገኔን
             በቸር ይግጠመን!!
             ኃይሉ ነኝ! Nov 2009