ፍቅር የሚገለጸው
ተርቤ ተጠምቼ ጥሩ ቤት የሌለኝ
ኑሮዬን በሙሉ በዱር ያሳለፍኩኝ
ቤት አለችኝ ብዬ ለሰው የማላወራው
መቃብር ይሞቃል ከእኔ ቤት ደሳሳው
ልስኑ ወላልቆ ለመውደቅ ተቃርቦአል
ለቤቴ ማሰሪያ ገንዘብ ከእጄ ጠፍቶአል
ሌላው እንዳይረዳኝ ከእኔ መች ተሽሎአል
አንጀቱ እያረረ ጥርሱን ያሳየኛል
ያዘነው ቢጤዬ ከንፈሩን ይመጣል
ክረምቱ ሲመጣ ሲበዛ ውሽንፍር
የሚነድ ማገዶ በቤት ውስጥ ቢከመር
መቼ ያስተኛኛል የቀዳዳው ችግር
በልብስ እንዳልከላከል የቀዳዳውን ችግር
ያለችው አንድ ነች ለክትም ለክብር
ልብሴም ተበጫጭቆአል
መጣፊያ በዝቶታል
ውሃ የለኝ የምጠጣው
ፊልተር የማደርገው
እኔ የምጠጣው መረሪ አፈር ነው
የከብቶች ርጋጭ ከነሱ የተረፈው
እኔስ ቢያመኝ እኔ እችለዋለሁ
ልጆች ሕጻናቱ ይህንን ጠጥተው
በተቅማጥ በተውከት እየተቸገሩ ነው
ገንዘቡ ችግር ነው ሐኪም እንዳልወስዳቸው
ጤና ጣቢያም ቢሆን መድሃኒትም የለው
ልጆቼን ለማስተማር አቅም በማጣቴ
ተማሪ ቤት አጥተው ውለዋል ከቤቴ
ትምህርት ቤት ቢሆን ከከተማ ያለው
እዚያ ሄዶ ለመማር በጣሙን ችግር ነው
ዳገት ቁልቁለቱን ወንዝ ተራራውን
ጠራርጎ የሚወስደው የወንዝ ሙላቱን
መጠበቅ ይሻላል ኑሮ ብሩህ እስኪሆን
ኽረ!!
የሰው ያለህ
ኸረ!!
የሰው ያለህ
በአውሮፓ በእንግሊዝ በጀርመን ያላችሁ
በስፔን በፈረንሳይ ኑሮ መስርታችሁ
በሰሜን አሜሪካ የተደላደላችሁ
በመላው ካናዳ ሕይወትን ያያችሁ
ወገን ዘመዶቼ ሀበሻ የሆናችሁ
ለዚህ ሕብረተሰብ መከታዎች ናችሁ
በዕድሜ ትላልቅ አባት እናቶቼ
በዕድሜ አምሳያ እህት ወንድሞቼ
ሃምሳ ሎሚ ያለው ለያዘው ሸክም ነው
ለአንድ ሰው ጌጡ ነው ብንከፋፈለው
እርዱ እንረዳዳ አውጡኝ ከዚህ ችግር
እኔም እንደእናንተው በሕይወት እንድኖር
እንድትመልሱኝ ካስፈሪው መቃብር
ልጆቼም ተምረው ሁሉን ተመራምረው
ለአገር ተረካቢ ጥሩ ዜጋ ሆነው
በሰላም እንዲኖሩ ምድሪቱን ጠብቀው
ስማኝ ወንድምዬ!!
በእንደዚህ መንገድ ነው ፍቅር የሚገለጸው።
በቸር ይግጠመን!!!
ኃይሉ ነኝ!!
2007
No comments:
Post a Comment