Monday, March 18, 2013

የምዕመን ፀሎት


የምዕመን ፀሎት
ጳውሎስ በመልእክቱ ገልፆ እንደጻፈው
ለቀጣዩ ትውልድ ትምህርት እንዲሆነው
ለወገኖች ሁሉ እንዲህ ይነግረናል
ሁሉም እንዲረዳ ገልጾ ጽፎልናል
ስለወንጌል ብዬ እስረኛ የሆንኩት
ለአሕዛብ ወገኖች በጌታ የታጨውት
የወንጌልን ሚስጢር በደንብ እንድገልጸው
አፌንም ከፍቼ ቃሉን እንዳስተምረው
የተሰጠኝ አደራ በደንብ እንድወጣው
ለዚህ አገልግሎቴ ፀሎት ስለሚያሻው
እንድትጸልዩልኝ አደራ እላለሁ
ዛሬ በዘመናችን በዓለም በምድራችን
የመዳንን ወንጌል ለሕዝብ አስረድቶ
ተናግሮ ተሟግቶ አስተምሮ መርቶ
የሚበላው አጥቶ ራሱ ተራቁቶ
ሕዝቡን ከኃጢያቱ ከሰራው ርኩሰቱ
ነፃ ሲያወጣው በምስክርነቱ
መንጥቆ ሲያድነው ከጠላቱ ጎራ
ጉልበቱን ሳይሰስት ለተሰጠው አደራ
ሌት ከቀን ይታገላል በደስታም በመከራ
ለዚህ የእግዚኣብሔር ሰው ጌታ ለመረጠው
ከጎኑ የሚቆም ኸረ! ተስፋው ማነው?
ወንጌልን ለመግለጽ ቆሞ እንዲናገር
ለዳነም ላልዳነም  ቃሉን እንዲተረትር
ወንጌልን ገልጾለት ያልዳነው እንዲድን
ከኃጢያቱ ወጥቶ የጌታ እንዲሆን
የዳነው ወገኑ በጌታ እንዲቆም
በጠላት ወረርሽኝ ወደዓለም እንዳያዘግም
የምስራቹን ቃል ለሕዝብ የሚያደርሰው
የደህንነት ወንጌል ለጠፋ የሚያበስረው
በእግዚኣብሔር ራዕይ ላይ ለተመሰረተው
በራዕዩ አቅጣጫ በጎኑ የሚሆንለት
ዓላማው እንዲሳካ የሚጸልይለት
ታማኝ ሆነን ጀግና ወደ አምላክ ጸባኦት
ሁሉም ያስፈልጋል ሊንበረከኩለት
ጀግና ለወንጌል አርበኛው
ራሱን ለጌታ ሕይወቱን የሰጠው
ዓለምና ትርፏን ወደኋላ ትቶ
የጌታውን መስቀል በራሱ ተክቶ
ወንጌል ለመናገር ለሕዝብ የተሰጠው
ብንጸልይለት ትርፋ የራሳችን ነው
መንፈስ ቅዱስ መጥቶ በዘይቱ ቀብቶ
የሚያስፈልገውን በእሳቱ ሞልቶ
ምክር ለሚያሻው ቃሉን እንዲነግረው
ሰውንም በድሎ ተግሳጽ ለሚገባው
አንዳችም ሳይፈራ ቃል እንዲያስተምረው
በድፍረት ለመስራት ፍሬውን ለማብዛት
ጠዋት ማታ ያሻዋል የምዕመን ፀሎት
                     በቸር ይግጠመን!!!
                     ኃይሉ ነኝ!!! 2007

No comments:

Post a Comment