Tuesday, March 19, 2013

ይበርዳል ይሞቃል


          ይበርዳል ይሞቃል
ጥንት ዘር ማንዘሯ የተፈጠረበት
ፀሐይና ዝናብ የሚፋረቅበት
የአየሩ ሁኔታ ፕላስ ከሆነበት
የበረዶ ክምር ከማይታይበት
የቀዝቃዛ አየር ፍጹም ከሌለበት
ይህንን ይመስላል የተፈጠረችበት
አምላክ በጥበቡ እርሷን ከፈጠራት
ከምድር ማዕፀን እግዜር ካስቀመጣት
ከተራራ ግርጌ ሰው ከማይደርስበት
ሊቃውንት በጥበብ ፈልገው አግኝተው
የማዕድኑን ዋሻ ቆፍረው አውጥተው
የወርቅ ቡችላ መሆኗን አረጋግጠው
ከወንዝ ውስጥ ከተው በውሃ ፈትገው
ዘርዋ እንዳይበረዝ በእሳት አንጥረው
አፈሩን ገሠሡን ከእርሷ አስወግደው
ወርቅ ወርቅ እንደሆነች በእሳት ፈትነው
በማሽን ውስጥ ከተው ጌጣጌጥ አድርገው
የፍጥረት ዓለሙ በጣት የሚያጠልቀው
ሀብታሙም ደሃውም ደረቱ ላይ ያለው
የሚወዳት ሁሉ ስም ሰጥቶ የሚጠራት
ወርቄ ነች እያለ የሚያቆላምጣት
ደሃው በስሜቱ የራሱ ሊያደርጋት
ማዕለቅ ሳይከፍል ገንዘብ ሳይሰጥባት
በምኞት በመሳብ ወርቂነሽ የሚላት
አንዳንዱ በጣቱ ሌላው በእግሩ የሚያስራት
ወርቅ አልቦ አድርጎ ሰውን ሊስብባት
ውበቱም እንዲታይ በአፍንጫው የሚሰካት
የተረፈው ደግሞ በባንክ ያስቀመጣት
ያከበራት ሁሉ በሙዳይ ያኖራት
ጥቅሟን ላላወቀ የሸቀጥ ዕቃ ናት
ለእኔ ግን ብርቅ ነች እኩያ የሌላት
የወርቅ ቀለበቴ በጣቴ ያጠልቅኳት
የእኔ የሆነችው ጠዋት ማታ የማያት
ከጊዜ በኋላ ከረጅም ዓመታት
ከምሥራቅ ከምዕራብ እያንከራተቷት
ወርቅነሽ አልማዝ ነሽ ብለው እያታለሏት
አዙረው አዙረው ካናዳ አመጧት
ሸቅጠው ሸቃቅጠው አርቲ አደርጓት
ካናዳ እንደሆን የአየሩ ሁኔታ
የተለያየ ነው ጠዋታና ማታ
ደመናው ሲደምን ቅዝቃዜ ሲመጣ
በመዳይ እያለች ወደውጭ ሳትወጣ
ታማርረው ገባች የአየሩን ሁኔታ
ትዘክር ጀመር የትውልዷን ቦታ
የተፈጠርኩበት የኖርኩበት አገር
የአፈጣጠሪ ነገር ውበቴ ሲቀመር
 በጠቅላላው ለእኔ ሁሉም መልካም ነበር
ዛሬ ቁር ሲነካኝ ውበቴን ሲያናጋው
ነሐስ አስመሰሉኝ ሽቅጥቅጥ አድርገው
ከነሐስ ከብር ጋር በአንድነት ሲያነጥሩኝ
አመዳም አድርገው ውበቴን ገፈውኝ
ነጋዴ ሲያታልል ነጭ ወርቅነሽ አሉኝ
አሁንስ ሰለቸኝ ተስፋ አስቆረጡኝ
ወርቅነቴ ቀርቶ አርቲ አደረጉኝ
እስከዛሬ ድረስ ተከብሬ ስኖር
የሁሉም ሚዛኑ የእኔ ውበት ነበር
ከእንግዲህ በኋላ ዘመን መጥቶልኛል
በጋው እየመጣ ክረምቱ ሄዶአል
መቀዝቀዙ ቀርቶ መሞቅ ጀምሮአል
ሰው ከጣለኝ ሥፍራ  የምፈልግበት
ጊዜ መጥቶልኛል ወርቄ የምባልበት
ዘሬ ተሰብስቦ ዘውድ የምሆንበት
በንጉሥ ጭንቅላት የምቀመጥበት
ንጉሥን  በማለት ለእኔም ሚሰግዱበት
ወርቅነሽ ተብዬ ክብር የሚሰጡኝ ዕለት።
                    በቸር ይግጠመን!!
                     ኃይሉ ነኝ May 2009 

No comments:

Post a Comment