Tuesday, July 1, 2014
Monday, March 17, 2014
Sunday, March 16, 2014
አጀንዳችን ምንድነው?
አጀንዳችን ምንድነው?
የካናዳ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት
በ1993 ዓም በዚሁ በካልጋሪ ከተማ ተመሰረተ ። ዛሬ ከአስራ ስድስት ዓመት በኋላ በፊላድልፍያ የእግዚኣብሔር ጉባኤ ቤተክርስቲያን
ጋባዥነት በካልጋሪ ከተማ (Lake Louise) ስብሰባ ያደረጋል እንደ እግዚኣብሔር ቃል ተሰብስቦ መወያየቱ ለጌታ ሥራ ስለሆነ
የሚደገፍና የሚበረታታ ጉዳይ ነው ። ሕዝበ ክርስቲያኑ ይሰበሰባሉ የሚለው ዜና ሲሰማ ፤ ከተመሰረተ ጀምሮ ድርጀቱ ምን ሰራ ፍሬውስ
ምንድነው? የሚል ጥያቄ በውስጡ ይመላለስ ይሆናል። መቼም የአብያተ
ክርስቲያናቱ ኅብረት የሰራውንና የወሰነውን በተውካዮቹ ፓስተሮች በኩል ሳይገለጽ የቀረበት ጊዜ ያለ አይመስልም ። ፊላድልፍያ መጽሔት
ዛሬ ለአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ልታሳስበው የምትፈልገው ሃሳብ አላት ። ከዚህኛው መጽሔት በፊት በታተመው እትም ለአንባቢዎችዋ
እንደገለጸችው ። በእግዚኣብሔር ለተመረጡ ለእግዚኣብሔር ወገኖች የምትለው ፤ በአገራችን ሁኔታ የወደፊት አጀንዳችን ምንድነው ?
የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ ከኋላ ቀርነታቸው የተነሳ ትምህርት ቤት ፤ መገናኛ ፤ የንፁህ የመጠጥ ውሃ የለውም ከዚህም በላይ በኑሮ
ውድነትና በተለያየ ጊዜ በረሃብ እየተጠቃ ነው ። እኛ ደግሞ የምናተኩረው በወንጌል ላይ ብቻ ነው ። በእርግጥ በወንጌል ላይ ማተኮራችን
ዋናውና አስፈላጊ ነገር ነው ። ግን የእግዚኣብሔር ቃል እንደሚናገረው ጌታ ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ ሕዝቡ የእግዚኣብሔር ቃል እየሰሙ
ስለዋሉ ፤ ተርበዋል የሚበሉትን ስጡአቸው አላቸው ። እዚህ ላይ እንደምንመለከተው የእግዚኣብሔር ቃልና ቁስ የሆነው ርሃባቸውን የሚያስወግዱበት
ምግብ ባርኮ ሰጣቸው ። እንደዚህ ባለው ጉዳይ ላይ ማተኮር ደግሞ ግዴታችን ነው ። ዛሬ በተለያየ ዘርፍና በተለያየ ሁኔታ የሀበሻውን
ሕዝብ ለማገልገል ከውስጡ በወጡት ልጆቹ በጎ አድራጎቶች እየተቋቋሙ ነው ። እነርሱም በአብያተ ክርስቲያን ኅብረት አባላት ቤተ ክርስቲያን
ሥር እየተደራጁ ነው ። ሥራው አንድ የእግዚኣብሔር መንግሥት የሚያስፋፋ መሆኑን ተረድቶ በሚያስፈልገው ሁሉ ሊረዱአቸውና ሊያበረታቷቸው
ይገባል የቤተክርስቲያንም አንድ አካል አድርገው ሊመልከቱአቸው ያስፈልጋል ። ሞቅ ሲል የሚታቀፉ ሙቀታቸው ዝቅ ሲል ደግሞ የሚጣሉ
መሆን የለባቸውም ። የካናዳ አብያተ ክርስቲያን ኅብረትም ይህንኑ ጉዳይ የሚከታተል ኮሚቴ አቋቅሞ በማደራጀትና በማበረታታት ሃሳቡን
በተግባር ሊያካሄደው ይገባል ። የተቀደሰ ዓላማ ስለሆነ ዋናው አጀንዳ ቢያደርገው መልካም ነው ። ተያይዘን አገራችንን በተቻለ አቅም
እንርዳት ሃምሳ ሎሚ ያለው አንድ ሰው ሸክሙ ፤ ለሃምሳ ሰው ጌጡ ነውና ።
ጌታ ይባርካችሁ!!
የመስቀል ወፍ
የመስቀል ወፍ
በአገራችን በምድራችን
በወንዛችን ተራራችን
ያኔ ሳንመጣ ካናዳ
እንደዛሬ ሳንሆን ባዳ
ለነገሩ ሳንሆን እንግዳ
በአበሾቹ ቀዬ መንደር
የምናስታውሰው ያለ የነበር
ዘመን አልፎ ሲመጣ ዘመን
ሁልጊዜም የሚታሰበን
በሕልማችን በሃሳባችን
በምናባችን የሚታየን
አሮጌው ዘመን አልፎ
አዲስ ዘመን አሸንፎ
ከዘመን ዘመን አልፈን
አዲስ ዓመት እውን ሲሆን
ሐምሌ ነሐሴ ክረምቱ
ሲያልፍ ጭጋግ ወራቱ
ያኔ በአገራችን በቀያችን
በገጠር ከተማ መንደራችን
በአንድነት ሆነው ሴቶቻችን
የኮባ ግልድም አገልድመው
ፀጉራቸውን ሳዱላ ተሰርተው
ቅቤ በአደስ ተቀብተው
ወርቀ ዘቦ ካባ ደርበው
ተመራርጠው በዕድሜያቸው
ጎራ ከፍለው እንደእኩያቸው
እርስ በእርሳቸው
ሴቱ በአንድነት ሆነው
ዘመን ሲለወጥ በዕለቱ
ሰው ከሰው ሳይገናኝ
በጠዋቱ
እማማና አባባ ሳይነሱ ከመኝታ
እንደተሰማ የወፍ ጫጫታ
ሳምንት ወር የተሟሸውን
በእሳት በቅቤ የቀለጠውን
ሴትዋ እየደለቀች ከበሮዋን
ለተቀባያዋ ስታቀነቅን ዜማዋን
ታቅፋው አደይ አበባዋን
ቄጠማ አክርማውን
እንኳን አደረሳችሁ ለማለት
ሲሽከረከሩ በየሰዉ ቤት
ያዜሙ ነበር እንደዚህ በማለት
አበባዮሽ ለምለም
በአባብዬ ቤት ለምለም
ቁሙ በተራ ለምለም
አበባ ለምለም ወሸባ ለምለም
እንደርስዎ ጌታ የለም
ከብረው ይቆዩ ከብረው
ለዓመት ወንድ ልጅ ወልደው
ሰላሳ ጥጃ አስረው
ከብረው ይቆዩ ከብረው
ይህንን ብለው አዜመው
የመልካም ምኞት ገልጸው
ምርቃት ለሕዝብ ሁሉ ሰጥተው
ወር ሳምንት ሳይሞላው
ክረምቱን መውጣቱን አስልታ
የአደይ አበባውን መፍካት አይታ
የደመራውን እሳት ተመልክታ
ውብ ዜማዋን እያዜመች
መምጣቷን እየተናገረች
ትመጣ ነበር የመስቀል ወፌ
እንድኖር ክረምት ወጣ ብዬ አርፌ
ዛሬ ዘመን ቢያልፍም
ክረምቱ ቢፈጸምም
ብሩህ ሰማይ ቢታይም
ፀሐይዋ እንኳንብትወጣም
ከዘመን ዘመን ብንሻገርም
ወፌን አላየዋትም
ወፌን አላያችሁም ወይ እንዳልል
ሁሉም ይናፍቃታል
ለራሱ ይመኛታል
መምጣቷን ይጠብቃል
ቢያያት ያከብራታል
ለሚስጢር ይፈልጋታል
በቤቱ ያስቀምጣታል
ወፌ የዘንባባ ዝንጣፌ አላት
ሰላምን የምታበስርበት
ፍቅርን የምትገልፅበት
ብትመጣ ጊዜዋን ጠብቃ
እንደዚህ እላታልሁ በቃ
እነሆ ክረምት አልፎአል
ዝናቡ ቆሞ በጋ መጥቶአል
በየመስኩ ኣዳይ አበባ አብቦአል
የአበባው ሽታ ምድርን ሞልቶአል
የአዝመራው ጊዜ ደርሶአል
የመስቀል ወፌ ከሄድሽበት
ርቀሽ ከኖርሽበት
ድምፅሽን ልስማው
ዜማሽን ላዳምጠው ስላት
ብትሰማኝ ብትመጣልኝ ልንገራት
ወፌ የመስቀል ወፍ
ኃይሉ ገቢ Jan 7/2007
ዜግነት
ዜግነት
ገና በሕጻንነት ሳለሁ በት/ቤቴ
ፊደል አስቆጣሪዬ የት/ቤት አባቴ
የሕብረተሰቡ አካል እንዲሆን መሰረቴ
ፊደል አስቆጠረኝ እንዳውቅ ስለዜግነቴ
አስተማሪው ሲያስተምረኝ
እንደዚህ ብሎ አለኝ
ደሙን ያፈሰሰ ልቡ የነደደ
በአገር ፍቅር ስሜት ጠላት ያስወገደ
ጠላትህ መሀይምነት ነው
ሕዝቡ እንዳያውቅ ያደረገው
ባለጋራህ በሽታ ነው
ሕዝቡን በሞት የሚቀስፈው
አንተ ተምረህ ካስተማርከው
ዜግነት ማለት ያ ነው
ዜጋ ዜግነት የሚባለውን
የአገር መሰረት የሆነውን
እንደ ማህተሜ በጉያዬ
በደረቴ ላይ አንጠልጥዬ
አስተማሪው ባስተማረኝ
ዜግነትን ስለተረዳሁኝ
በስርዓቱ ስለሄድኩኝ
ሕዝቡን ስላስተማርኩኝ
አቅጣጫውን ስለነገርኩኝ
በሽታውን ታምሜ ቁስሉን ስለጠገንኩኝ
የሚራበውን ተርቤ ሕዝቡን ስላስተማርኩኝ
አንዱ መጥቶ ሲያስረኝ
ሌላው ደግሞ ሲፈታኝ
ዘመኔን አሳለፍኩኝ
ዜጋ እሱ ብቻ መሰለኝ
ዜግነት እንደሌለኝ ቆጠርኩኝ
ስለዚህ መናገር ካልቻልኩኝ
ሕዝቡን ካላስተማርኩኝ
የቁም እስረኛ ከሆንኩኝ
ዜግነትን ከተገፈፍኩኝ
አገሬን የማገለግልበት ሰዓት
እስኪ መጣ የምፈለግበት ዕለት
ለአገሬ አንድ ቀን ብቆይላት
ይህንን ከልቤ ጋር አስቤበት
ሄድኩኝ ወደ ባዕድ መሬት
የደረስኩበት ምድር
አሁን የምኖርበት አገር
እትብቴ የልተቀበረበት
ዘር ምንጅላቴ የልኖረበት
የዘር ዐረጌ የሌለበት
ሰጠኝ የመኖር ነፃነት
ስናፍቀው የነበረው ዜግነት
ተምሬ እንዳስተምር
ሰርቼ እንድከብር
ከአንዱ ቦታ ወደ አንዱ ለመዘዋወር
በነጻነት በሁሉም ቦታ እንድኖር
አለኝ ነጻነት የተሟላ
ሥራ ቢሆን ከለላ
ምን ያደርጋል !!!
ሁሉም ነገር ቢሟላልኝ
ተትረፍርፎ ሁሉን ባገኝ
የሰላም አየር ብተነፍስ
ሁሉም ቢቀየር እንደአዲስ
አገሬ ትናፍቀኛለች እትብቴ የተቀበረበት
አያት ቅድመ አያቴ የሞቱላት
እናትና አባቴ የኖሩበት
አፈር ፈጭቼ ያደግኩበት
በየኔታ ቤት የተማርኩት
ፊደል የቆጠርኩበት
አገሬ ትዝ ትለኛለች
የታሪክ ቁንጮ የሆነች
ወሎ ላሊበላ ጎንደር
አክሱም እንደዚሁም ሐረር
ሉሲ የተፈጠረችበት
የታሪክ ምዕራፍ የተገለጸበት
አባይ አዋሽ ያለበት
የተከዜ ፏፏቴ የሚፈስበት
ዘርዝሬ የማልገልጸው
አውርቼ የማልጠግበው
በየትም ቦታ የማላፍርባት
በአደባባይ የምናገርላት
ባንዲራዬን የማውለበልብላት
አሁንም እናፍቃታለሁ
ኢትዮጵያነት ለእኔ ዜግነት ነው
ኃይሉ ገቢ Oct 25/2007
ኢትዮጵያችን
ኢትዮጵያችን
አማራ ጉራጌ ሳንል
በዘር ትብታብ ውስጥ ሳንውል
ሁሉም በአንድነት በጋራ
ማንም ሳይቀር ከኤርትራ
ቦታ ሥፍራ ሳንለይ
ሳይኖርብን ከልካይ
በሂዋርዝ ጥላ ውስጥ ሆነን
ብርጅን እኩሌታ አጋምሰን
ዘመን ከዘመን ለመሸጋገር
ሚሊንየምን ለማክበር
ከፍ አለች ባንዲራችን
ተውለበለበች ሰንደቃችን
እኔም የሥራ ልብሴን አውልቄ
የሰንበቱን ልብስ አጥልቄ
እንደ እንቁጣጣሽ ደምቄ
ይዤ አደይ አበባዬን
ዘመን መለወጡን ማብሰራዬን
እንቁጣጣሽ ዘመን ያምጣሽ ለማለት
ሕዝቡን በሩቁ አሻግሪ ስመለከት
ባንዲራዬን አየዋት ጠገብኳት
በልጅነቴ ሰንደቅ ዓላማችን ያልኳት
ትግርኛ ጉራጌኛው አማርኛ ጭፈራው
ዳንሱ እስክስታ ሽለላው
የማይጠገበው የአበባዮሽ ጨዋታ
ልባችንን ሞላው በደስታ
ያኔ የአገር ቤታችን ሕይወት
በሰው መንፈስ ውስጥ አየሁት
እኔም በምናቤ ተመለከትኳት
የእትብታችን መቃብር ቤታችን
ውብ አገር መመኪያችን
እኛን ያፈራችው አገራችን
ምድረ ገነት ኢትዮጵያችን
ኃይሉ ገቢ መስከረም1/2000- Sep11/2007
ቃል ኪዳን
ቃል ኪዳን
በአንቺና በእኔ መካከል የነበረ
ቃል ኪዳኑ የተፈራ የከበረ
ትዝታውን ካልረሳሽው ካልካድሽው
ለደቂቃ ለሰኮንድ አስታውሼው
ከሥራ ቦታ እኔን ለማየት
አኔም አንቺን ለመሸኘት
እኔ ሥራ ላይ ከሌለው ጭንቀት
በፊትሽ ላይ የነበረው
ምን ሆኖ ይሆን የት ሄደ
እስኪሉሽ የወደደና ያበደ
ቃል ኪዳን የእህትነት
በንፁህ ፍቅር ስሜት
ያን ሁሉ አውርተን ተጨዋውተሽ
ዛሬ እንዴት ጠፋ ከሕሊናሽ
ለፍላፊ ያልሽኝ ምን ብዬ
ምን አጥፍቼ ምን በድዬ
ወሽካታ ያልሽኝ ምን ዋሽቼ
ምን ተናገርኩኝ ኽረ! መቼ
አውርቼ ይሆን ዘላብጄ
የሰደብሽኝ ውድ ወዳጄ
እኔን ሰድበሽ አስቀይመሽ
እንደ አለንጋ አንቺ ገርፈሽ
አናደሽ ጭራ አስበቅለሽ
አሁን ደግሞ ትሸሼያለሽ
እባክሽን ቃል ኪዳኑን አስታውሰሽ
እንታረቅ እንስማማ ሁሉን ትተሽ
ኃይሉ ገቢ 15/6/1975
Subscribe to:
Posts (Atom)