Sunday, March 16, 2014

ቃል ኪዳን

ቃል ኪዳን
በአንቺና በእኔ መካከል የነበረ
ቃል ኪዳኑ የተፈራ የከበረ
ትዝታውን ካልረሳሽው ካልካድሽው
ለደቂቃ ለሰኮንድ አስታውሼው
ከሥራ ቦታ እኔን ለማየት
አኔም አንቺን ለመሸኘት
እኔ ሥራ ላይ ከሌለው                                                                       ጭንቀት በፊትሽ ላይ የነበረው
ምን ሆኖ ይሆን የት ሄደ
እስኪሉሽ የወደደና  ያበደ
ቃል ኪዳን የእህትነት
በንፁህ ፍቅር ስሜት
ያን ሁሉ አውርተን ተጨዋውተሽ
ዛሬ እንዴት ጠፋ ከሕሊናሽ
ለፍላፊ ያልሽኝ ምን ብዬ
ምን አጥፍቼ ምን በድዬ
ወሽካታ ያልሽኝ ምን ዋሽቼ
ምን ተናገርኩኝ ኽረ! መቼ
አውርቼ ይሆን ዘላብጄ
የሰደብሽኝ ውድ ወዳጄ
እኔን ሰድበሽ አስቀይመሽ
እንደ አለንጋ አንቺ ገርፈሽ
አናደሽ ጭራ አስበቅለሽ
አሁን ደግሞ ትሸሼያለሽ
እባክሽን ቃል ኪዳኑን አስታውሰሽ
እንታረቅ እንስማማ ሁሉን ትተሽ

ኃይሉ ገቢ 15/6/1975

ትዝታ

ትዝታ
አንቺ ሶቭየት ኅብረት ለመሄድ
እኔም አንቺነትሽን በመውደድ
ሳይነጋ በሌሊት አንቺን ለመሸኘት
በሰላም ያግባሽ ለማለት
ሄድኩኝ ቦሌ መሸኛው  ድረስ
 ሸኝቼሽ ወደ ሥራ ለመመለስ
ብጠብቅ የሚመጣው ሌላ
መንፈሴ ተጨነቀ ሰውነቴ ተጉላላ
ውድ እህቴ ሄዳ ይሆን
ሳንተያይ ዓይን ለዓይን
ሰው አገኝ ነበር ሄዳ እንኳን ቢሆን
ብዬ በሃሳብ ስብከነከን
ድንገት ዓይኔን ወደኋላ ስመለከት
አንቺን አየው የእኔ እመቤት
በሩቅ ሆነሽ ጃኖ ለብሰሽ
ደብተር ብዕር በእጅሽ ይዘሽ
 አውለብልቤ ሰላም አልኩሽ
በዓይኔ ብቻ አንቺን ሸኘውሽ
አይሮፕላኑ ተሻገረ
አመረረ እየበረረ
ወደ ሰማይ ገብቶ ቀረ
ይህ ለእኔ ትዝታ ነው
ምንጊዜም የማልረሳው

ኃይሉ ገቢ1981

ሳቀች

ሳቀች
እንደሞናሊዛ አይደለም ፈገግታ የለበትም
ለማስመሰል ይመስላል እኔን አላረካኝም
ሳቀችብኝ ቅዳሜ ማታ
እኔን አይታ ተመልክታ
ሳቀች እኔን እያየች
ምን ይናገረኝ እያለች
ድሮ ጥንት ስንተዋወቅ
እኔን እንደዛሬ ሳትንቅ
ሩጫ መሮጥ ስትጀምር  
ተስፋ እንዳትቆርጥ ስንመካከር
መስኮብ እሄዳለሁ ስትለኝ
የሞራል ድጋፍ እያደረግኩኝ
ሞራሏ እንዳይሰበር እየመከርኩኝ
አልጄሪያ ኬንያ ሞምባሳ ስትሄድ
አገር ውስጥም ለሥራ ስትገደድ
ናዝሬት ደብረ ዘይት ለሥራ
ሲቻለኝ እየሄድኩ ማንንም ሳልፈራ
አወይ የሰው ነገር
ምንም ሳልናገር
ሳቀች ተንተከተከች
የተበደለ  እየመሰለች
አይደል እንደሞናሊዛ ፈገግታ የለበትም
ተንተክትካ ሳቀችብኝ እኔ ግን አልበደልኳትም
በእኔስ ብትስቂ አይገርመኝም
ወንድምሽ ነኝ ምንም አላጠፋሁም

                         ኃይሉ ገቢ 1973

የምሥራች

ማስታወሻ                                                        
 ከዚህ በታች የሚገኙት ግጥሞች ከ1973 -1975 ባሉት ጊዜያት ከጻፍኳቸው ሲሆኑ ከማስታወሽዬ ውስጥ ያገኘዋቸው ናቸው።
የምሥራች
ደስታዬን ተካፈሉ እልል በሉ
ዘመድና ወዳጆቼ በሙሉ
አኩርፋኝ የነበረች ጓደኛዬ
መንምኖ የነበረው ተስፋዬ
አንድ ቀን በምሽት
ዘመድ ወዳጆቼ ባሉበት
ላንቀያየም በአንዳች ነገር
ማንም ላያጠፋ ካለን በምድር
ያለፈውን ይቅር ብለን
ለሚቀጥለው በሰላም ለመሆን
ታረቅን ዘመዶቼ
እልል በሉ ወዳጆቼ
የእኔን መጥፎ የማትወደውን
የእሷን ጉድለት የማልሻውን
ጓደኛዬን ወድ እህቴን
አይቻት የማልጠግባትን
ታረቅን እንደ በፊቱ ልንሆን

       ኃይሉ ገቢ 1973

ያረጀ አንበሳ

ያረጀ አንበሳ
ጥንት ዓለም በእግዚኣብሔር ሲፈጠር
አዳም ከሄዋን ጋር በገነት እንዲኖር
እንስሳት አራዊት እንዲያስተዳድር
ሊገዛ ሊመራ የአምላክ ፈቃድ ነበር
አዳም አጠፋና ከገነት ሲባረር
ሁሉም እያረጀ ሁሉም ይሞት ጀመር
በሕይወት እየኖረ አርጅቶ እንዲሞት
አዳም በማጥፋቱ ጌታ ፈረደበት
አንበሳ አርጅቶ ማደን ሲያቅተው
ጉልበቱ ይደክምና ነገር ግራ ሲገባው
የዝንብ መጫወቻ የዓይን አር ማከማቻ
ተከታዩ ጠፍቶ መሆን ነው ለብቻ
ጸሐይ ወጥታ ስትከር ዕዳር ታሀሳስ ጥር
ክረምት ሳይገባ ሲመጣ ግንቦት ወር
ከተማው ሲገማ ቆሻሻ ሲከመር
ዝንብ ይፈለፈላል ለማጥፋት ለመብረር
ሲበር ሲያጠፋ ያገኛል አንበሳ
ጊዜ የጣለውን ኮሳሳ ሬሳ
አንበሳ ሲያገሳ ያላየችው ዝንብ
ዓይኑን ታወጣለች መስሎአት የዕለት ምግብ
ጀግና ነበር አንበሳ የአራዊቶች ንጉስ
ዛሬ ግን ተነሳች እሱን ለመደምሰስ
መላ አከላቱን ዓይኖቹን ለማፍረስ
ዝንብ የአንበሳን ጉልበት ዙፋኑን ለመውረስ

      ኃይሉ ገቢ 1985

ዓለም በቃኝ

 ዓለም በቃኝ
ዓለም በቃኝ ወህኒ ቤቱ፤ማሰሪያ ቤት
የምንሊክ ልጅ ዘውዲቱ ያስገነቡት
አምና ካቻምና ድሮ ጥንት
ስንቱ አለፈ ከዚህ እስር ቤት
በግርፋት ቁም ስቅሉን ተመልክቶ
ስንቱ ወጣ ከዚህ እስር ቤት ተሰቃይቶ
በትኋኑ በበሽታው በዝናቡ በወጨፎ
ስንቱ ሞተ ስንቱ ተርፎ
ዛሬ ዛሬ ይህ ሁሉ ነገር ቀርቶ
ት/ቤት ፕሮጀክቱ ተመስርቶ
ላብራቶሪ  ጤና ጣቢያ አቋቁመን
ዓለም በቃኝን ውብ አድርገን
መታጠቢያ፤ ሽንት ቤቱ ፤ የፅዳቱ
አቤት ስንቱ የእስር ቤቱ ማስደሰቱ
ቢንጎ ፤ካፍቴሪያ፤ ሕብረት ስቁን
ዳርት፤ቴኒስ መጫወቻ አሰባስበን
ሰው አስተምረን በተራችንም ተምረን
ለዓመታት ሰው አስታርቀን                                                                          የበደሉንን ይቅርብለን
ሕዝቡን ብለን ሕዝብን መርተን
ሻማ ሆነን ብርሃን ሆነን ተቀጣጥለን
እስረኛውን አሳሪውን አስደስተን
የሄደውን እየሸኘን የመጣውን እየተቀበልን
ዛሬም እኛ እዚያው አለን
በማማችን ላይ ሆነን
ተራችንን እንጠብቃለን

         ኃይሉ ገቢ 1990

አውለብልቡት ሰንደቃችሁን

አውለብልቡት ሰንደቃችሁን
ዘመን አስቆጥራችሁ
የፈረሰውን ገንብታችሁ
ሰው ሳታዩ የሚያያችሁ
አምላክ ይበልጣል ብላችሁ
ስድብና ግልምጫውን ችላችሁ
በጌታ ጎን የቆማችሁ                                                                                     
በልደት በዓል ሳጣችሁ
ትክዝ ብዬ አንብቼ
የምጠይቀውን ሰው አጥቼ
ብጠብቅ ዘመኑን አልፌ
በሳምንቱ ብመጣ ከንፌ
ማንን ልጠይቅ
የትኛው እንደሚለጥቅ
ትምህርት ቤት እንደተማርነው
ሰላሹ ኸረ! ማነው ?
ጊዜ ወር አለፈኝ
ምጤን እያማጥሁኝ
የሚነግረኝ ስላጣሁኝ
ግራ ቢገባኝ አዘንኩኝ
ከሁሉ ጌታ ይበልጣል አልክኝ
ዛሬ ስትጀምሩ አገልግሎቱን
ማምለክ ማስመለክ ስራችሁን
እንዴት ደስ አለኝ መሰላችሁ
በመድረኩ ላይ በመቆማችሁ
በርቱ እግዚኣብሔር ይርዳችሁ
አውለብልቡት ሰንደቃችሁ

 ኃይሉ ገቢ Jan27/2007