Sunday, March 16, 2014

በእርግጥ ይጎበኛል!!!

በእርግጥ ይጎበኛል
ሕዝቦቼ እያለ ጌታ የሚጠራቸው
በአብርሃም ምክንያት ተስፋ የገባላቸው
በኖሩበት ምድር ድርቅ ቢያጠቃቸው
የሚበላ ነገር ቢያጡ ከቤታቸው
እርሻቸው ጦም አድሮ ምግብ ቢያሳጣቸው
ወረዱ ወደግብፅ በተሃቸውን ይዘው
ወደግብፅ ቢጓዙ እህልን ፍለጋ
ዮሴፍ ሰጣቸው ምግብ ያለዋጋ
መኖሩ ሲታወቅ ዮሴፍ በሕይወት
ሁሉም ተሰብስበው ሄዱ ሊጎበኙት
እግዜር ጎበኛቸው ጌታ አሰባቸው
ከመታው ርሃብ ከሞት ታደጋቸው
ሀና በዘመንዋ ልጅ ስላልነበራት
ሁልጊዜም ፀሎትዋ ነበር እንዲሰጣት
ጠዋት ታነባለች ማታም ታለቅሳለች
ሁሌም ንዝነዛዋ ልጅ ስጠኝ እያለች
ምኞትዋ ነበረ ልጅ እንዲሰጣት
ካለባት ተጽዕኖ ነጻ እንዲያወጣት
እግዚኣብሔር እንባዋን ጩኽትዋን ተመልክቶ
ጌታችን ጎበኛት ሳሙኤልን ሰጥቶ
ዛሬም በዘመናችን በአንዳድ ሰው ሕይወት
ችግሩ በዝቶበት ተስፋው ያለቀበት
መቼ ነው እግዚኣብሔር እኔን ሚጎበኘኝ
ከተሸከምኩት ችግር ጌታ የሚያላቅቀኝ
ብሎ የሚያስብ ሰው
ምንም የሌለው ተስፋ የሚጠብቀው
በእርግጥ ይጎበኛል እግዚኣብሔር ታማኝ ነው።
               በቸር ይግጠመን!!!
                ኃይሉ ነኝ!




Saturday, March 15, 2014

ሰውን ማበሳጨት


ሰውን ማበሳጨት

አምናና ካቻምና በፍቅር ስንከንፍ

ምን ተገኝቶ ይሆን እንደዚህ መኳረፍ

ሳልም የነበረ ለዘላለም ደስታ

ለጊዜውም ሳይሆን ሆነ ለበሽታ

ወዳጄ እህቴ የፍቅር እመቤቴ

ልላት የሚገባኝ ነበረችኝ እህቴ

ደስታ የምትሰጠኝ እኔም የምወዳት

ገና ስንዋደድ ችግር ፈጠሩባት

ነግሬአት ነበረ እሷ አልሰማችኝም

ርህሩሀይምሰሉሽ ስለፍቅር አያውቁም

ሄደሽ አታውሬያቸው ደንታ የላቸውም

ልንገርሽ ላስረዳሽ ሰው ለሰው አያዝንም

ብዬ ባስረዳትም እሷ አልገባትም

የፈራሁት ነገር ደግሞም ያልጠብቅኩት

አንድ ቀን በጠዋት ጎህ ሳይቀድ በሌሊት

ኬው አለ ኬል አለ ሳላስብ ድንገት

ስማ እንደምነህ እሁድ የት አሳለፍክ

እኔጋ ሳትመጣ የት ሄደ ነው የዋልክ

መቼም አታጣትም የምትለው ወሬ

ብዙ ነግረህኛል እስካሁን እስከዛሬ

ስማ አንተን ነው ምንድነው የምትለው

ሰውን ማበሳጨት ሁሌም ዓመልህ ነው

       ኃይሉ ገቢ 02/6/1975

ማነው ባለተራ?


ማነው ባለተራ?

በእምቢልታ በገና በውዳሴ መዝሙር

ምስጋና ለማቅረብ ለእግዚኣብሔር ክብር

ብሎ የተነሳው ትንቢተ ኢሳያስ

በቤተመቅደስ ውስጥ ጸሎቱን ሲያደርስ

እግዚኣብሔር በክብሩ ተቀምጦ ሳለ

ኢሳያስ በፍርሃት እንደዚህ ብሎ አለ

በበደሌ ምክንያት ደግሞም በኃጢያቴ

በበዳይ ሕዝብ መካከል እኔ መገኘቴ

እግዚኣብሔርን ደግሞ በዓይኔ በማየቴ

አለቀልኝ በቃ አልኖርም በሕይወቴ

እንደዚህ በማለት ኢሳያስ ሲቃትት

የሠራዊት ጌታ ይህንን በመመልከት

መላእክቱን ላከ ከሱራፌል አንዱን

የኢሳያስ ከንፈር የተቀደሰ እንዲሆን

ሱራፌልም ደግሞ ይዞ የፍም እሳት

በጉጠት አድርጎ አፉን በማስነካት

ኢሳያስ ነፃ ሆነ ከበደል ከኃጢያት

እኔኑን በድለው በጥፋት ውስጥ ላሉት

ኃጢያትን በመስራት በሞት ለሚጠፉት

ማንን እልካለሁ ማንስ ይሄድልናል

ይህንን የሚፈጽም ሰው ያስፈልገናል

ይህንን ጥያቄ እግዚኣብሔር ሲናገር

ኢሳያስ የመለሰው ያኔውኑ ነበር

በአገሬ በምድሬ ነጋሪ በማጣት

ወደሞት እየሄደ  እየጠፋ በኃጢያት

ወንድሜና እህቴ አባቴና እናቴ

በቅርቡም በሩቁ የእኔ ጎረቤቴ

ተመለስ የሚለው ከሞትና ከኃጢያት

ሰው ስላላገኘ ወንጌል የሚሰብክለት

የመንግሥቱን ወንጌል ነጋሪው በመርሳት

ወይ እኔ ከተረፍኩ ይበቃል በማለት

ስንቱ በሞት ሄደ ሳናስበው ድንገት

ወንጌል ተሸክሞ ከምዕራብ ተነስቶ

እስያ አፍሪካ አውሮፓን አካቶ

የምሥራቹን ቃል ተናግሮ አስረድቶ

እስከዛሬ አለ ሕይወት ያህል ሰጥቶ

ዛሬም አላቆመ ስራውን ይሰራል

ለደከመው ጀግና ማንስ ይተካዋል

ለነፍሳት ግድ ብሎት የሚጨነቅ ማነው?

ጌታ ሲናገረው ግልጹን ሲያስረዳው

ማንን እልካለው ማን ይሄድልኛል?

ብሎ ሲጠይቀው በተግባር የሚያውል

ዳገት ቁልቁለቱን ሞትን ሳይፈራ

መስቀል ተሸክሞ የሚወጣ ተራራ

ለጌታ የሚላክ ማነው ባለተራ?

ወንጌልን ለማድረስ የትውልድ ባላደራ

እኔ ወይስ አንተ ማነው ባለተራ?

እኔ ነኝ ባለተራ የሕዝብ ባላደራ

ለመስራት የቆረጥኩ የጌታዬን ሥራ

ይዤ መመሪያዬን የመዳን ወንጌልን

የጠፋው ወገኔን የማድንበትን

ለንስሐ ተዘጋጅ ብዬ የምልበትን

እኔ ነኝ ባላደራ ተረካቢ ትውልድ

ለሕዝቡ ለመድረስ ታሪክ የሚለኝ ግድ

ተራው የእኔ ነው ተራው የአንተ ነው

ተራው የሁላችን የአበሻ ሕዝብ ነው

    ኃይሉ ገቢ  Nov 2009

ማስታወሻ


ማስታወሻ (ሶቭየት ኅብረት እንደነበረች ስላሰራችልኝ ፎቶ )

የእኔና ያንቺ ማስታወሻ

ብዙ አለ ለመናገር ቢያሻ

ለልደት መርካቶ ፒያሳ

ሞልቶአል ማስታወሻ የማይረሳ

የእኔና የአንቺ ፎተግራፍ

የነገራችን ሁሉ ምዕራፍ

የተነሳነው የአንቺና የእኔ

ማስታወሻ ነው የማልረሳው በውኔ

ሶቭየት ኅብረት እያለሽ

የእኔንፎተግራፍ መርጠሽ

ከሰው በሙሉ ለይተሽ

ፎተግራፍ አሰርተሽ

የላክሽልኝ ትዝ ይበልሽ

አሰራሽው በእንጨት

አይደለም እንደሌሎቹ በወረቀት

እስከ ሕይወቴ መጨረሻ

ከልቤ የማልረሳው ማስታወሻ

አመሰግናለው ስለውለታሽ

አልረሳውም ማስታወሻሽ

 ኃይሉ ገቢ 4/4/1976

መቼ!!


መቼ!!

መቼ ትሄዳለች

ኸረ!!መቼ ትሄዳለች

አገር ለቃ ድንበር ትታ

የፍቅራችን ታሪክ ረስታ

ድንበር አልፋ አገር ለቃ

ከወዳጅ ከዘመድ ርቃ

መቼ ይሆን ጊዜው

ከአገር አገር የምንለያየው

ምስጢር አይደል ተናገሪ

የሐዘንና የደስታ ወሬ አውሪ

ከአገር ርቀሽ ወንዝ አቋርጠሽ

በፍቅራችን ትመጪያለሽ  ትቀሪያለሽ

ቁርጡን ብለሽ አረጋግጠሽ

ኸረ!! ሐቁን ፤ ሀቁን ብለሽ

አገር አልፈሽ አገር ጥለሽ

ኸረ!! መቼ ትሄጃለሽ

ልዑል


                                                      ልዕል

እግዘኣብሔር  ከጥንቱ  የተናገረለት፤

ኢሳያስ  ሚክያስ  የተነበዩለት፤

ዳዊት  በውዳሴ  ለእርሱ የገለፀለት ፤

ዮሐንስ ጎዳና ጠርጎ ያዘጋጀለት፤

የምሥራቹን ቃል  ሱራፌል መላእክት

ተወልዶአል ብለው የመሠከሩለት፡፡

ልዑል የእግዚኣብሔር ልጅ

መሲህ  የዓለም ወዳጅ

ተወልዶአል  አማላጅ፡፡

ገና  ጥንት  ከዘመናት   በፊት

እግዚኣብሔር  ለዳዊት ቃል እንደገባለት

ጦረኛ  ስለሆንክ  ስላለ በእጅህ  ደም

ቤቴን ልትሰራ አንተ አትችልም

ቤቴን የሚሰራው  ከአብራክህ  የሚወጣው

ያንተ ልጅ ብቻ  ነው

ከአብራክህ  የሚወጣው አንተ የምትወልደው

ልዑል የእግዚኣብሔር  ልጅ  ተብሎ ሚጠራው

ዙፋኑ ዘለዓለም  የማይናወጥ  ነው

የሰው ልጅ  አዳኝ ነው ከአንተ  የሚገኘው፡፡

ስለእርሱ የገለፀው ነቢዩ  ሚክያስም

አንቺ  ቤተልሄም  ታናሽ ብትሆኝም

 ከቁጥር ባትገቢም ሰው ባያስብሽም

የእስራኤል ገዥ ከአንቺ ይወለዳል

የእግዚኣብሔር ክብር በአንቺ ይገለፃል፡፡

ከብዙ  ዓመታት ከዘመናት በፊት

እንደተናገረው ኢሳያስ  በትንቢት

እነሆ ድንግል ልጅን ታረግዛለች

ወን ድ ልጅም ደግሞ እርሷ ትወልዳለች

ስሙን አማኑኤል ብላ  ትለዋለች

የእግዚኣብሔር ክብር በእርሱ ይገለፃል

ሰው ሁሉ በአንድነት ልዑሉን ያዩታል፡፡

አዳምና ሄዋን በገነት ውስጥ ሳሉ

የተከለከለውን በለስ ስለበሉ

ኃጢያትን በደልን በመፈፀማቸው

አትብሉ ተብለው ያን በመብላታቸው

ልዕል እግዚኣብሔርን በማሳዘናቸው

ሁለተኛ ጥፋት  እንዳይገኝባቸው

ከገነት አባሮ በሩን ዘጋባቸው

በአዳም ምክንያት ደግሞም በበደሉ

አዳምና ሄዋን ፍጥረታት በሙሉ

ከእርግማን በታች ሁሉም  በመዋሉ

እግዚኣብሔር አምላክም ይህንን በመመልከት

ሊያድነው ፈለገ  ከተፈረደበት 

ፍጥረት እንዲሻገር ከሞት ወደ ሕይወት

በዋኔስ  ሞከረ   አልተሳካለትም

ከሞት ወደ ሕይወት አልተሸጋገረም

ባደረገው  በጎ  ከመሞት  አልዳነም

በጥቦት  ባውራ በግ በፍፁም አልሆነም

በሁሉም ሙከራ ሰው ነጻ አልወጣም፡፡

ስለዚህ መፍትሔው የአዳም መዳኛው

ልጁን  ላለም ፍጥረት በመስጠት ብቻ ነው፡፡

ስዓትና  ጊዜ  ዕለታቱ  ሲደርስ

የአዳም ዘሪያ ከሞት ለመመለስ

ተወለደ  ልዑል አዳኝ የእግዚኣብሔር ልጅ

የፍጥረታት ጌታ የሰው ልጅ አማላጅ፣፣

ሰባ  ሰገሎች  የምድር ጠቢባን

የተነገረው ቃል ተግባራዊ እንዲሆን

ከምሥራቅ ተነስተው  በኮከቡ ምሪት

ቤተልሔም ድረስ እሱ እስካለበት

ዕጣንና  ከርቤ  ወርቅ አልማዝ  ስጦታ

ይዘው መጥተውለት  ለሕፃኑ ለጌታ

በእግሩ ሥር ሰገዱ ተገቢውን ሰላምታ፣፣

   ተወለደ ልዑል ተወለደልን

   ከኃጢያትና ከሞት እኛኑን ሊያድን

   በአነስተኛ ሥፍራ እርሱ የተወለደው

   ልዑሉ  ተዋርዶ  እኛን ሊያከብር ነው፣፣

   ታዲያ?

  የእግዚኣብሔር ልጅ በልብህ ተውልዶአል?

   ልዑሉን  በልብህ ሥፍራ ሰጥተህዋል?

   በእርግጥ በአዳኝነት ተቀብለህዋል?

  ወይስ በዘልማድ ጉዞ ጀምረሃል!!

ልዑል በሕይወትህ ሊወለድ  ይገባል፣፣

                        Dec 24/2008.

                           ኃይሉ ገቢ

Friday, March 14, 2014

ልውሰዳት!


ልውሰዳት

ጽጌረዳ የአበባ ውብ

ከሩቅ ወደእሷ የምትስብ

ሮዝ ቀይ ጃኖ ለብሳ

በአጋም መካከል ተኮፍሳ

ወደ እርሷ ልጠጋ ወድጄ

ልዳስሳት ልነካት በእጄ

መስሎኝ ሳያት ፤ እሾህ ያላት

ብዙ ራቅኳት ፤ ተለየኋት

ጽጌረዳ ጣፋጭ ስዊት

 የአበቦች ዓለም ንግሥት 

ውብ መዓዛ ያላት ለዛ

ዘመን የሚያመጣውን አይቼ

ከዘመን ጋር የሚሄደውን ሸኝቼ

የጀርባዬን እኔነቴን ተመልክቼ

ቁጭ ብዬ ባለሁበት ሰዓት ተዝናንቼ

በአበባ መካከል ቁጭ ብላ

ከፊት ከኋላ ኖሯት ከለላ

ፅጌረዳን አየኋት አገኘኋት

እንዳልርቃት ከአደይ አበባዬ ጋር ናት

እንዳልተዋት እንዳልረሳት ታስጎመጃለች

ፍሬ አላት አበባ ነች

ራስዋን ቀና አድርጋ

ፅጌ ረዳ ሆና የበጋ

ፈገግታዋን እያሳየች

እንዲህ አለች

ትወስደኛለህ !!?? አለች

አትወስደኝም ዳግም ተናገረች

እንደ ውዳሴ ማርያም እየደገመች

የማልሸኛት እርሷ መስሎአት

እኔም አልኳት ልቤም አላት

የውስጤን የልቤን ነገርኳት

አንቺን ያልወሰድኩሽ

የልቤ የውስጤ ያላደርግኩሽ

ፅጌረዳዬ ብዬሽ

ከአበቦቼ መካከል አስቀምጪሽ

ጠዋት ማታ ታቅፌሽ

በአደባባዬ ተክዬሽ

ለፍሬ ለአበባነት አድርሼሽ

ለቤቴ ውበት ሰጥተሽ

የእኔ የራሴ አድርጌሽ

እኖራለሁ ከአንቺጋር

ውበትሽ ሳይከስም በክብር

ይህንን ገልጪ ብነግራት

እኔ ቋንቋ አላውቅም በማለት

እየጣረች ነው እንዳልወስዳት

በምን ቋንቋ ላስረዳት

የመውሰድ ትርጉሙን ትጠይቃለች

እያስረዳች ፤ ግን ትሰነጣጥቀዋለች

እንጨት ይመስል ትፈልጣለች

ፊደል ቋንቋውን ትናገራለች

ከፋ ይሁን ሔረርጎታ

ምናልባትም አሳይታ

የበቀለችበት ቦታ

ቤተልሔም ይሁን ናዝሬት

ፊደል ሐዋርያ የቆጠረችበት

እኔ ከቋንቋ ምን አለኝ

ከቀዬ ምን ሊተርፈኝ

እኔ የምፈልገው ፅጌረዳነት

ከምትሰጠው መሀዛ ውበት

ፅጌረዳዬን በአበባዬ መካከል አድርጌአት

በዓይኔ ሸኘዋት አደረስኳት

እንዳለችው አልወሰድኳት

በእቅፌ አላደረግኳት

ልቤ ግን ተከተላት

 ከአበቦች መንደር አደረሳት

ብቻ ብቻ ልቤ ተረዳት

ውሰደኝ ካለች ልውሰዳት

ኃይሉ ገቢ August 12/2006