Thursday, April 4, 2013

አብስሩ ዜና


አብስሩ ዜና
የምሥራቹን ቃል ለዓለም ለማድረስ
ቃል ኪዳን የገባችሁ ሕዝቡን ለመመለስ
ጊዜና ሁኔታ ስላልተመቻችሁ 
ጊዜን በመጠበቅ ምንም ያልሰራችሁ
ከራስ ከሥጋ ጋር ፍትጊያ የያዛችሁ
ራስን ለመግለጥ አቅምን ያጣችሁ
በልውጣ አልውጣ መካከል ያላችሁ
ጊዜን በመጠበቅ ጊዜ የጠፋባችሁ
በእንደዚህ ያላችሁ ስንት ፋሪስ ናችሁ
ክረምት አልፎአል ውብ በጋ መጥቶአል
ጨለማው ተገፎ ለሊቱ ነግቶአል
አስፈሪ ጨለማን ብርሃን ትክቶታል
ወንጌልን ለማድረስ ጊዜ መጥቶለታል
በፍርሃት ማዕጸን ውስጥ ሆናችሁ
ሳትንቀሳቀሱ ዝምታ ውጦአችሁ
በመንቲያነት በሆድ ውስጥ ያላችሁ
ቀድማችሁ ውጡ ከመንቲያችሁ
ጥሳችሁ ሄዱ አሸንፋችሁ
እኔን ባይነት አስወግዳችሁ
ወገባችሁን ጠበቅ አርጋችሁ
የወንጌልን ቃል ተሸክማችሁ
ባርኮት ከጌታ ተቀብላችሁ
ብረሩ ወደፊት እንደወፊቱ
አብስሩ ዜና እንደእርግቢቱ።
           በቸር ይግጠመን!!!
           ኃይሉ ነኝ!!

Tuesday, March 26, 2013

ፋሪስ


ፋሪስ
በኦሪት ዘፍጥረት 38 ላይ የተመሰረተ

ትዕማር ወልዳ ዘር እንዳታስቀር
በሁለት ነገሮች ተፈርዶባት ነበር
በመበለትነት አባቷ ቤት እንድትኖር
ፍሬ እንዳታፈራ እንዳይኖራት ትዳር
ለረጅም ዓመታት በእንደዚህ እያለች
ከዕለታት አንድ ቀን አዲስ ዜና ሰማች
አማቷ ይሁዳ በጎችን ሊያሸልት
ወደዚያ እንደሚመጣ ሰዎች ነገሩአት
ቀኑ ሲደርስ ዕለቱና ሰዓቱ
አውቃ ስትረዳ ይሁዳ መምጣቱ
የመበለትነቷን ልብስዋን አወለቀች
መልኳ እንዳይታወቅ በአይነ ርግብ ሸፈነች
በመምጫው መንገድ ዳር ሄዳ ተቀመጠች
ይሁዳ ሲያያት አማቱን ሳያውቃት
ሁኔታዋን አይቶ ዛሬ እንደር አላት
ጋለሞታ መስላው ለፍቅር ጠየቃት
ትዕማር
ያልከውን ብፈጽም ምን ትሰጠኛለህ?
ለማድርበት ሂሳብ ምን ትከፍለኛለህ?
ወይ ለቃል ስምምነት ምን ትፈጽማለህ?
ይሁዳ ቃል ገባ እንደዚህ በማለት
ከመንጋዬ መካከል አንድ የፍየል ጥቦት
እልክልሻለሁ ነገ በዚህ ሰዓት
የፍየሉን ጥቦት እስክትልክ ድረስ
ምን መያዣያ አልህ ለአንተ የሚሆን ዋስ?
አገሩ የሚያውቀኝ ከተማው መንደሩ
የተከበርኩ ነኝ በመላው አገሩ
ለእኔ ዋስ የሚሆን ኸረ! እህቱ ምንድነው?
ለአንተ መያዥያ ዋስህ የሚሆነው
ፊርማህን መግለጫ በጣትህ ላይ ያለው
የማህተም ቀለበት ከነማሰሪያው ነው
እንዲሁም ምርኩዝህ በእጅህ የያዝከው
መያዣውን ይዛ ለሊቱን አደረች
የኢየሱስ የዘር ግንድ በማዕጸንዋ ያዘች
የምጥ ጊዜዋ ሲደርስ የምውለጃዋ ሰዓት
በጊዜው በሰዓቱ በምትወልድበት ዕለት
ተረጋገጠላት መንታ ልጅ እንዳላት
አዋላጅዋ ደግሞ በምታዋልድበት ጊዜያት
ቀድሞ እጁን ላወጣው ፈትል አሰረችለት
እጁን ወደማዕጸን ወደውስጥ ሲመልስ
ሌላኛው በፍጥነት ለመወለድ ሲደርስ
የማዕጸን በሩ ቢሆንም ጠባብ
ዛራሕ ደግሞ እጁን ወደውስጥ ሲስብ
ፋሬስ ግን ለመውጣት ጊዜውን አልፈጀም
ሊወለድም ደግሞ ፋሪስ አልቸኮለም
ጊዜና አጋጣሚ ሁሉም ሲገጣጠም
በነገሩ ተገርማ ጥሰህ ውጣ አለች
በስም አሰያየም ፋሪስ ብላ ጠራች
             በቸር ይግጠመን!!
             ኃይሉ ነኝ!

Sunday, March 24, 2013

ዓይን


ዓይን
ዓይን የተፈጠረው ሁሉንም ለማየት
ብለው ተናግረዋል አባቶች  በተረት
እግዚኣብሔር አምላክ ዓይናችንን ሲፈጥረው
ብዙ ጥቅሞችን እንዲሰጥ አድርጎ ነው
ዓይን በብሌኑ ነገር ተመልክቶ
በነገሮቹ ላይ ትኩረቶችን ሰጥቶ
መልካም የሆነ ሲያይ ከልቤ ጋር ተስምምቶ
ለመላው አካላት መልእክቱን አድርሶ
ክፉ የሆነውን ከአእምሮ ደምስሶ
ለሕይወት የሚበጀውን ወደ ደም አምጥቶ
ከሰራ አካላት ጋር ለመስራት ተስማምቶ
ዓይን አስፈላጊ ነው ለማየት አጥርቶ
ይጠቅማል ለመኖር ዓይን ሁሉን አካቶ
                 በቸር ይግጠመን!!!
                ኃይሉ ነኝ!!!

Thursday, March 21, 2013

ምስክርነትና ውጤቱ


           ምስክርነትና ውጤቱ

በዚህኛው እትማችን  ምስክርነትና ውጤቱ በሚል ርዕስ አንድ ሰው እንዴት መመስከር እንዳለበት ስለምስክርነት ከተሰጠ ጥናታዊ ትምህርት ለመጽሔት እንዲመች አድርገን ያቀርብነው ስለሆነ በተለይም በምስክርነት አገልግሎት ለሚያገለግሉ ወገኖችና በምስክርነት አገልግሎት ለማገልገል የመንፈስ ቅዱስ ምሪት የምትጠባበቁ ይህ ጽሑፍ አቅጣጫውን ስለሚያሳይ አውጥተነዋል። ወደ ትምህርቱ ከመግባታችን በፊት ከትምርህቱ ጋር የተያያዘ ጥያቄ ጠይቀን ወደ ትምህርቱ እናልፋለን።  ስለጌታ ኢየሱስ አዳኝነት የምንመሰክረው ለምንድነው? ዓላማውንና ግቡን ተረድተን ነው የምንመሰክረው? በዚህ አገልግሎት የተሰማራችሁ ጌታ ይባርካችሁ!! በማለት ወደ ትምህርቱ እናልፋለን።
                           ምስክርነት ምንድነው?
  ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ሲያከናውን የነበረውን አገልግሎት ፈጽሞ ወደ አባቱ ከመሄዱ በፊት ለአስራ ሁለቱ ደቀመዛሙርት በማርቆስ ወንጌል 16 ፥15 (ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ  ለሰው ሁሉ ወንጌልን  አስተምሩ )እንዲሁም  በሐዋ.ሥራ 1 ፥ 8 ( መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ በኢየሩሳሌም በይሁዳና በሰማርያ ሁሉ እስከ ምድር ዳርቻ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ) አላቸው። ከእዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ዋና ሃሳብ ወንጌልን አስተምሩና ምስክሮቼ ትሆናላችሁ የሚሉት ናቸው። እነዚህን ሁለት ቃላት ግባቸውን ስንመለከት አንድ ዓይነት ሃሳብ አላቸው። ወንጌልም የእግዚኣብሔር ቃል ነው ኢየሱስም ወደ ምድር የተላከ የእግዚኣብሔር ቃል ነው ምክንያቱም ቃል ሥጋ ሆነ ብሎ የእግዚኣብሔር ቃል ስለሚናገር ሁለቱ ቃላት ምንም ልዩነት የላቸውም። በጠቅሉ ምስክርነት  በሃዋርያት ሕይወት ውስጥ አቢይ ስፍራ እንዲኖረው ጌታ ኢየሱስ  አደራ ብሎ ካስገነዘባቸው። ለእኛ ደግሞ ምስክሮቼ ናችሁ ልዩ ሥፍራ ሊኖረው ይገባል። ለዚሁም የሐዋ 2፥32, 5፥32 , 10፥39-42 , 13 ፥ 31 ,22 ፥15 እነዚህን ማጠቅሻ ጥቅሶችን በምናነብበት ጊዜ ምስክርነት ምን መሆኑን በግልጽ ያስረዳናል። ምስክርነት ምንድነው ለሚለው ጥያቄ ግልጽ ለማደረግ ከዚህ በመቀጠል አንዳንድ ሃሳቦችን እናያለን ።
 እንግዲህ ምስክርነት አንድ ነገር ሲከናወን ወይም ሲፈጸም በቦታው ላይ በአጋጣሚም ሆነ አውቆ የተገኘው ሰው በስፍራው ላይ ላልነበረው ሰው ወይም ትክክለኛ ፍርድ ለመስጠት እንዲያመች ለሕግ አካል የሚሰጥ ቃል ነው ለዚህ ሃሳብ ሐዋ 5 ፥ 30 -32 እናያለን (እናንተ በእንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን፤ የአባቶቻችን አምላክ ከሙታን አስነሳው እርሱም ለእስራኤል …. እኛም ለእነዚህ ነገሮች ምስክሮች ነን.) እዚህ ላይ ድርጊትና ውጤት አለ። ጌታ ኢየሱስ በእንጨት እንደተሰቀለና እግዚኣብሔር በትንሳኤ እንዳስነሳው ያ ድርጊት ደግሞ ትክክል መሆኑን በስፍራው ተገኝተው በዓይናቸው የተመለከቱ ሊያስረዱ የሚችሉ  ምስክሮች  ነበሩ፤  እነዚያ ምስክሮች  በዓይናቸው ያዩትንና በተግባር የነበሩበትን ላልነበሩ ወገኖች ሲያስረዱ አይተናል ስለዚህ ተጨባጩን ሁኔታ ማስረዳት  ምስክርነት ይባላል  ።
  በእውነት ላይ ተመስርቶ ያየውንና የሰማውን ነገር ለሌላው  ትምህርትና መረጃ እንዲሆን ለሁለተኛ ወገን ማስተላለፍ ማስረዳት ምስክርነት ነው። ወንጌላዊው ዮሐንስ በ1ኛ መልእክቱ  ምዕራፍ 1፥1- 2 እንዲህ በማለት ጠቅሶታል ( ስለሕይወት ቃል ከመጀመሪያ የነበረውን፤ የሰማነውን፤በዓይኖቻችን ያየነውን፤ የተመለከትነውንና እጆቻችን የዳሰሱትን እንናገራለን። ሕይወት ተገለጠ ፤ እኛም አይተነዋል፤ እንመሰክርለታለንም።) ዮሐንስ ከመጀመሪያ ጀምሮ የጌታ ደቀ መዝሙር ነበር። ብዙ ጊዜ ከጌታ ኢየሱስ ጋር ያሳልፍ ስለነበር የተመለከትነውና እጆቻችን የዳሰሱትን እንናገራለን ይላል። ይህንን የምስክርነት ቃል ሲጽፍ እንኳን በዕድሜ ትልቁ ደቀመዛሙርት እርሱ ነበር ። ታዲያ በሕይወቱ የነበረበትን ጉዳይ እኛ ለማናውቀው ስለጌታ ይመሰክርልናል። እንግዲህ ምስክርነት ማለት የኖሩበትን ሕይወት ትክክለኛነቱን ለማያውቅና ሊረዳ ለሚፈልግ  ግለሰብ ወይም ሕብረተሰብ  መግለጽ፤ ማስረዳት፤ መናገር ማለት ነው ።
                     ማነው መመስከር ያለበት ?
ምስክርነት ማለት ምን መሆኑን ከተረዳን ፤ መመስከር ያለበት ማነው? ጌታ ኢየሰስ ክርስቶስን እንደግል አዳኙ ተቀብሎ ከዓለም ዝባዝንኬ ነፃ የወጣና እውነተኛ ለነፍሳት ፍቅር ያለው፤ ሕዝቦች ወደ ንስሐ መምጣት አለባቸው ብሎ የሚያምን መመስከር አለበት። የምስክርነት አገልግሎት ለተወሰኑ የቤተክርስቲያን መሪዎች የተሰጠ ሸክም አይደለም። የመጀመሪያቱ ቤተክርስቲያን የወንጌል ስርጭት ወደ ዓለም ሁሉ የወጣው ወይም የተሰራጨው በተበታተኑ አማኞች አገልግሎት ነበር። ጌታ ኢየሱስ ወደ ዓለም ሁሉ ሄዱ ወንጌልን ለፍጥረት ስበኩ ወይም በሌላ አነጋገር ያያችሁትንና የሰማችሁትን ላልሰሙት መስክሩላቸው ባለው መሰረት መንፈስ ቅዱስ እስኪሞሉ ድረስ ቆይተው፤ በሉቃስ ወንጌል 24፥45-47 እንደተገለጸው በኢየሩሳሌም በሰማሪያና በዓለም ዙሪያ ወንጌል ሊዳረስ ቻለ። በሐዋ ሥራ 8፥ 1-4 እንደተገለጸው እያንዳንዱ በጌታ ኢየሱስ ያመኑት፣ ለሕዝቦች ሆነ ለግለሰብ ስለ ጌታ ኢየሱስ ምስክርነት መንፈስ ቅዱስ ሲያዛቸው ወደ ታዘዙበት ሥፍራ በመሄድ ይመሰክሩ ነበር። በስደቱ ምክንያት ወደተለያየ ሥፍራ የተበታተኑት፣ ወንጌልን ጌታን ለማያውቁት ይናገሩ ነበር። ዛሬም በዘመናችን ስለጌታ ኢየሱስ መመስከር ያለበት ያመነ ምዕመን በሙሉ ነው ። ምስክርነት መስጠት ያለበት የተወሰነ አካል ወይም ክፍል  እንዳልሆነ  የእግዚኣብሔርን ቃል ስንመረምር፤ ጴጥሮስ ደቀመዝሙር ነበር በሁሉም ስፍራ እየተዘዋወረ ስለ ጌታ ኢየሱስ መስክሮአል፤ ጳውሎስ ከደቀመዛሙርት አንዱ አልነበረም እርሱ እንደሚለው እኔ ታናሽ ነኝ ይላል ጌታ ኢየሱስ ለዚህ አገልግሎት ስለመረጠው፣ ከአሳዳጅነት በንስሕ ተመልሶ ጌታን ይመሰክር ጀመረ፤ ጳውሎስ  ( ወንጌልን መስበኬ አያስመካኝም፣ የምሰብከው ግዴታዬ ስለሆነ ነው፣ ወንጌልን ባልሰብክ ወዮልኝ) 1 ቆሮንቶስ 9፥16 አንዲህ ብሎአል ።ምስክርነት በጌታ ኢየሱስ ላመኑት በሙሉ መሆኑን እስጢፋኖስ፤ ጢሞቲዎስ፤ ፊልጶስ ….. እንዚህን ሁሉ ስንመለከት ለእኛ ሕያው ምስክሮች ናቸው። ስለዚህ ለነፍሳት መዳን ሸክም ያለው፤ ጌታን የሚወድና ግቤ መንግስተ ሰማይ ነው የሚል ሁሉ መመስከር አለበት ። 
ለምስክርነት እንዴት እንዘጋጅ ?      
የምስክርነት አገልግሎት ከመጀመራችን በፊት ቃሉን ማጥናት ያስፈልጋል ምክንያቱም የእግዚኣብሔር ቃል ማጥናት አንዳንድ ጊዜ ለሚመጣልን ጥያቄ ያለምንም መጠራጠር ከቃሉ መልስ ለመስጠት ያስችለናል ። ቃሉን ሳናጠና በዘልማድ እንመሰክራለን ብለን ብንሞክር በጣም አደገኛ ነው ። አንዳንድ ሰዎች ሕይወት የሌላቸው ግን ቃሉን የሚያውቁ ስለሚያጋጥሙን መልስ ለመስጠት በጣም ሊከብደን ይችላል። አልፎ ተርፎ ለራሳችንም ሕይወት ጥያቄ ውስጥ ሊያስገባን ስለሚችል በመጀመሪያ ደረጃ ቃሉን ማጥናት ያስፈልጋል። በመቀጠል መንፈስ ቅዱስ ምሬት እንዲሰጠን የጸሎት ሰው መሆን ያስፈልጋል፤ በጸሎት ስንተጋ ብዙ በረከት እናገኝበታለን፤ ቃሉ ይገለጽልናል፣ መንፈስ ቅዱስም ምሬት ይሰጠናል፤ ለዚሁም ምሳሌ የሚሆነንን ፊልጶስ ነው ሐዋ.ሥ 8፥26-40 እንደምንመለከተው ፊልጶስ ለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ  ሊመሰክርለት የቻለው መንፈስ ቅዱስ በሰጠው ጥበብና ምሪት ነው። ሌላው በምንም ዓይነት ድርቅ ያለ ክርክር አያስፈልግም፤ እኛ ዓላማችንና ግባችን የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት መመስከር እንጂ ለመከራከር ስላልሆነ ክርክር ዓይነት ሲጀመር ቀጠሮ ቀጥረህው ተለያዩ እንጂ ወደእኔ እመልሰዋለሁ ብለህ ብዙ ጊዜህን አታጥፋ ምክንያቱም ከክርክሩ የተነሳ ትዕግሥት አጥቶ አድነዋለሁ ያልከው ሰው ወደ ሌላ አዝማሚያ ስለሚሸጋገር ለመመለስ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል ስለዚህ ክርክር ሲነሳ ቀጠሮ ቀጥረህው ተለያዩ፤ በሌላ ቀን ጌታ ልቡን ለወንጌል እንዲከፍተው ጸልየህ ከአንተ የተሻለ የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት ካለው ወንድም ወይም እህት ጋር ወደ ቀጠሮ ቦታ ብትሄድ መልካም ነው። ከምትመሰክርለት ሰው ተገቢ ያልሆነ የቁጣ ንግግር ቢያጋጥምህ ማሸነፍ የምትችለው በትዕግስት ነውና ምስክርነትህ እንዳይሰናከል ትዕግስት የመጀመሪያው ዓላማ ይሁን። ስለጌታ የምትመሰክርለት ካልጨረስክለት ለቀጣይ ቀጠሮ መልካም ፍቃደኛነቱን ጠይቀው፤ መልካም ፈቃደኛ ከሆነ አድራሻውን ተቀበለው ያንተንም የስልክ አድራሻ ስጠው፤ የቀጠሮው ስፍራ ጸጥታና መንፈስን የማይረብሽ ቢሆን መልካም ነው ። ለመመስከር በምትወጡበት ጊዜ ሁለት ብትሆኑ ጥሩ ይሆናል ምክንያቱም አንዱ ስለጌታ ሲገልጽለት ሌላው ለሚጠየቀው ጥያቄዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በማውጣት በቃል ልትረዳዱ ትችላላችሁ፤ በምንም ዓይነት ተጨማሪ ሃሳብ በዚህ ላይ ምን ሃሳብ ካልተባለ በስተቀር ሁለታችሁም ስትናገሩ ምስክርነት ሳይሆን ክርክር ስለሚመስል የሚመሰከርለት ሰው ግራ ስለሚገባው ሁለታችሁም የምትናገሩት በእህምሮው ሊይዝ ስለማይችል አንድ ሰው ብቻ ቢናገር መልካም ውጤት ያመጣል። በመጨረሻ ልናስብበት የሚገባን ነገር ቢኖር አንዳንድ አከራካሪና ሊያጋጩ የሚችሉ ነጥቦች አሉ፤ እነዚያ ነጥቦች ሊነሱ ይችላሉ ስለዚህ በነዚያ ነጥቦች መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል የሚል ጥያቄዎችን በማንሳት እንደሚገባው ማጥናት ያስፈልጋል ምክንያቱም ለሚቀርብልን ጥያቄ መልስ መስጠት ይገባናልና ለምስክርነት ስትወጣ በምንም ዓይነት መጽሐፍ ቅዱስ ሳትይዝ እንዳትወጣ፣ ያለመጽሐፍ ቅዱስ መውጣት ጠላቱን ለመውጋት ያለጦር መሳሪያ ወደ ጦር ሜዳ የሚሄድ ወታደር ማለት ነው።
                               የምንመሰክረው ለማነው?
ጌታ ኢየሱስ በተለያየ የወንጌል ክፍል እንደተናገረው በተለይም በማርቆስ ወንጌል 16፥15 እንደገለጸው ( ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ለሰው ሁሉ ወንጌልን አስተምሩ) ዋና ዓላማው ወደዓለም ሄዶ ወንጌልን ማስተማር ነው። በጌታ ኢየሱስ ትህዛዝ መሰረት ወንጌልን የምንመሰክረው ለፍጥረት ሁሉ ነው። ቋንቋውና ዕውቀቱ ካለን ልንመሰክር የሚገባን ለአንድ ወገንና ለተወሰነ አካባቢ ሳይሆን ዘርና ቀለምን ሳንለይ ለአዳም ፍጥረት ነው። ቃሉን ለመናገር መንፈስ ቅዱስ ሲያዘን ጊዜና ቦታ ልንመርጥ አይገባንም ፤ ሁልጊዜም ልናስብ የሚገባን ነገር ቢኖር ጠላት ብዙውን ሕዝብ ወደ ሞት እየመራው ነው ያንን ሕዝብ ደግሞ ልንታደገው ኃላፊነት ተስጥቶናል። በቅርብ አንድ ክርስቲያናዊ ዌብ ሳይት እየተመለከትኩ ነበር (Stand for GOD) ዛሬ ባለንበት ምድር ጌታ ኢየሱስን የሚያመልኩ ቁጥራቸው እየቀነሰ  ቤተ ክርስቲያን ደግሞ እየተዘጋ መሆኑን እያስረዳ በአንዳንድ ቤተክርስቲያን ያለውን ልዩነት ሁኔታውን በግራፍ ያሳያል።

የቤተክርስቲያኑ ስም      1991  2001  በ%የተቀነሰው
                       
ዩናዩትድ ቸርች    3,098,120   2839,125    -8.2%
አንግሊካን ቸርች  2,188,110   2,035,500   -7.00%
ሉተራን ቸርች      636,205     606,590     -4.7%
ፒሪስፒቲርያን ቸርች     636,295     409,830     -35.6%
ፒንቴኮስታል ቸርች       436,435     369,475     -15.3%
ሰልቬሽን አርሚ ቸርች   112,345      87,785       -21.9%
ሚኖናይት ቸርች  207,970     191,465      --7.9%
ክርስቲያን ሪፎርምድ ቸርች     84,685       76,665       -9.5%
                       
በጠቅላላ     7,400,165   6,616,435   -110.1%

ከዚህ በላይ ያለውን ሰንጠረዥ ስንመለከት ምን ያህል ሕዝብ ወደ ሞት እየሄደ እንዳለ ልንረዳ እንችላለን ፤ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን እየተዘጋ ነፍሳት ወደ ሞት ሲሄዱ ዝም ብለን አንመለከትም፤ የመጣንበት ዓለም ግድ ይለናልና መንፈስ ቅዱስ ሲናገረን በሥራና በተለያየ አጋጣሚ የተገናኘነውን ሰው በጥበብ ልንመሰክርለት ያስፈልጋል። ፊልጶስ ለኢትዮጵያዊ ጃንደረባ በጥበብ እንደመሰከረለት እኛም በጥበብ እንመስክር። ጥበብ ለምስክርነት ዋናው ኃይል ነው።
                           ለምስክርነት ዋና ነጥቦች
ምስክርነታችን በአንድ ሰው ላይ ዘለቄታ ያለው ለውጥ ለማምጣት እስከሆነ ድረስ ከዚህ በታች ያሉትን ነጥቦች ለምንመሰክርለት ሰው ማስጨበጥ ያስፈልጋል።
       እግዚኣብሔር ሰማይንና ምድርን ሲፈጥር ሰውን ደግሞ በነጻነት እንዲኖር አድርጎ እንደፈጠረውና ሞት እንደማይሞት አድርጎ በገነት እንዲኖር አድርጎት እንደነበረ  ኦሪት ዘፍጥረት 1,2 , 2፥17  ማስረዳት፣ ማስተማር፣ መግለጽ ያስፈልጋል።
       ሰው ደግሞ እግዚኣብሔር የሰጠውን ጸጋ ባለመፍቀዱና በገዛ ጎዳናው እንደሄደና ሰው ሁሉ ኃጢያተኛ እንደሆነ ዘፍጥረት ምዕራፍ 3-11 ያለውን ሃሳብ የአዳምና የሄዋን፤ የቃየልን፤ የኖህ ዘመን የጥፋት ውሃ፤ የባቢሎን ግንብ ሥራውንና እንዴት ከእግዚኣብሔር በጣም እንደራቀ ታሪኮችን እየጠቀስክ ንገረው የእነዚያ ከእግዚኣብሔር መራቃቸው ብቻ ሳይሆን በእነዚያ ምክንያት እያንዳንዱ የሰው ልጅ ኃጢያተኛ መሆኑን ሮሜ 3፥11, 3፥23 ከዚህ በመቀጠል ከኃጢያት ሞት መዳን የሚቻለው በክርስቶስ ኢየሱስ በእግዚኣብሔር ልጅ ብቻ መሆኑን ሮሜ 5፥21, 6፥23, 1ዮሐንስ5፥11,12 የሰውን ልጅ ከገባበት ኃጢያት ለማውጣት እጌታ ኢየሱስን እንደሰጠንና መዳን በኢየሱስ ብቻ መሆኑን እንደሚገባ ንገረው በእርሱ የማያምን ግን ፍርድ እንዳለበት በተጨማሪ ጥቅሶችን በማጥናት ማስረዳት ያስፈልጋል።  ዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አንድ እስከነማጥኛው ብናጠናው ለምስክርነት በጣም ሊረዳን ይችላል።
ከዚህ በተጨማሪ ከ1-5 የተገለጸውን ሳትገልጽለት እንዳታልፍ ያስፈልጋል።
1.      ኢየሱስ እውነተኛ የእግዚኣብሔር ልጅ መሆኑን(ሮሜ 1፥4)
1)ክርስቶስ ሰለኃጢያታችን አልፎ እንደተሰጠ (ሮሜ 4፥25)
2)ክርስቶስ ትንሳኤችን ነው ስለዚህም በአብ ዘንድ አማላጃችን መሆኑን (ሮሜ 8፥34)
3)በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያምኑ የዘላለም ሕይወት እንዳላቸው (1ጴጥሮስ 1፥3-5)
4)በጌታ የሚያምኑ እንደ ክርስቶስ በትንሳኤ እንደሚነሱ(1 ቆሮ 15፥49, ፊልጵስዮስ 3፥21 ,1 ዮሐንስ3፥2)
-በሰጠህው ምስክርነት ጌታን የሚቀበል ወይም የተቀበለ ከሆነ ቀጥሎ የተቀደሰ ኑሮ እንዲኖር መምከር ያስፈልጋል፤ እንዳትዘነጋ ከዚህ በኋላ የመስከርክለት ሰው ሕይወቱ በጠላትና በጌታ መካከል ነው። አንዳንድ መጥፎ ልምዶች ቢኖሩበት  እንደመጥፎ ርኩሰት አታጥላላበት፤ የተለወጠ ሕይወት እንዲኖረው፣ያንን መጥፎ ልምድ እንዲያስወግድለት ፀልይለት፤ ለጌታ የሚሳነው ነገር ስለሌለ መጥፎ ልምዱን ያስወግድለታል። ላለበት መጥፎ ልምድ ጌታ እንደሚያስወግድለት የሚከተሉትን ጥቅሶች
ብታስጨብጠው ጥሩ ነው። 2 ቆሮ 5፥17,ኤፌሶን2፥8, ቆላስያስ 3፥9-10ቃሉን በጽሞና አንብበህ አስተምረው።
  አዲስ ክርስቲያን በሕይወቱ እንዲያድግ ምን እናድርግ ?
የመስከርክለት ሰው ወደ ንስሐ ሲመጣ፣ ጌታ ኢየሱስን ሲቀበል አዲስ ክርስቲያን ሲሆን አሳዳጊና ተንከባካቢ ከሌለው እንደሚገባው ሊያድግ አይችልም ስለዚህ ለእንደዚህ ያለ ነፍሳት አሳዳጊ ያስፈልገዋል።
       ከቻልክ መጽሐፍ ቅዱስ ካላገኝህ አዲስ ኪዳን ገዝተህ ስጠው፣ የማግኘቱ ጉዳይ አስቸጋሪ ከሆነብህ ቤተክርስቲያን የምታገኝበት መንገድ ተፍልጎ መጽሐፍ ቅዱስ ብትሰጠው መልካም ነው።
       መጽሐፍ ቅዱስ ወይም አዲስ ኪዳን ካገኘህለት በኋላ ቃሉን እንዲያነብ አበረታታው ፣ እንዴት እንደሚያነብ አስረዳው ለዚህ ደግሞ ዋናው የአዲስ ኪዳን አካል ኮር የዮሐንስ ወንጌል ስለሆነ፣ ስለ ጌታ ኢየሱስ እንዲረዳ ተደርጎ የተጻፈ ስለሆነ የዮሐንስ ወንጌል፣ የማቴዎስ ወንጌል፣ የማርቆስ ወንጌል፣ የሉቃስ ወንጌል፣ በመጨረሻ የዮሐንስ ወንጌል በድጋሚ ተራ በተራ በጽሞና  እንዲያነብ ብትመክረው፤ በቀላሉ ስለጌታ ኢየሱስ አዳኝነት ሊረዳ ይችላል።
       ከዚህ በኋላ ያንተ ምስክርነት ጸንቶአልና የደህንነት ትምህርት ስለሚያስፈልገው የደህንነት ትምህርት ወደሚያስተምሩት አስተላልፈው የደህንነት ትምህርት በሕይወቱ ሌላኛውን ምዕራፍ የሚቀጥልበት  አካል ስለሆነ የደህንነት ትምህርት መማር ግዴታ ነው። ሥራዬን ጨርሻለሁ ብለህ ችላ አትበለው የደህንነት ትምህርት መከታተሉን አረጋግጥ።
       ብቸኝነት ይዞት ወደቀድሞ ሕይወቱ እንዳይመለስ በየሰንበቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመጣ አብረታታው ከሌሎች ወንድሞች ጋርም አስተዋውቀው።
በምስክርነት አገልግሎት በኩል እንደዚህ ለእግዚኣብሔር ሥራ ከተጋን ጳውሎስ በቃሉ እንዳስተላለፈልን የአባሳደርነታችን አግልግሎት ሥራ ፈጽመናልና የድል አክሊል ይጠብቀናል።                                   በቸር ይግጠመን!!
                                                                  ኃይሉ ነኝ!!! 2008