ፋሪስ
በኦሪት ዘፍጥረት 38 ላይ የተመሰረተ
ትዕማር ወልዳ ዘር እንዳታስቀር
በሁለት ነገሮች ተፈርዶባት ነበር
በመበለትነት አባቷ ቤት እንድትኖር
ፍሬ እንዳታፈራ እንዳይኖራት ትዳር
ለረጅም ዓመታት በእንደዚህ እያለች
ከዕለታት አንድ ቀን አዲስ ዜና ሰማች
አማቷ ይሁዳ በጎችን ሊያሸልት
ወደዚያ እንደሚመጣ ሰዎች ነገሩአት
ቀኑ ሲደርስ ዕለቱና ሰዓቱ
አውቃ ስትረዳ ይሁዳ መምጣቱ
የመበለትነቷን ልብስዋን አወለቀች
መልኳ እንዳይታወቅ በአይነ ርግብ ሸፈነች
በመምጫው መንገድ ዳር ሄዳ ተቀመጠች
ይሁዳ ሲያያት አማቱን ሳያውቃት
ሁኔታዋን አይቶ ዛሬ እንደር አላት
ጋለሞታ መስላው ለፍቅር ጠየቃት
ትዕማር
ያልከውን ብፈጽም ምን ትሰጠኛለህ?
ለማድርበት ሂሳብ ምን ትከፍለኛለህ?
ወይ ለቃል ስምምነት ምን ትፈጽማለህ?
ይሁዳ ቃል ገባ እንደዚህ በማለት
ከመንጋዬ መካከል አንድ የፍየል ጥቦት
እልክልሻለሁ ነገ በዚህ ሰዓት
የፍየሉን ጥቦት እስክትልክ ድረስ
ምን መያዣያ አልህ ለአንተ የሚሆን ዋስ?
አገሩ የሚያውቀኝ ከተማው መንደሩ
የተከበርኩ ነኝ በመላው አገሩ
ለእኔ ዋስ የሚሆን ኸረ! እህቱ ምንድነው?
ለአንተ መያዥያ ዋስህ የሚሆነው
ፊርማህን መግለጫ በጣትህ ላይ ያለው
የማህተም ቀለበት ከነማሰሪያው ነው
እንዲሁም ምርኩዝህ በእጅህ የያዝከው
መያዣውን ይዛ ለሊቱን አደረች
የኢየሱስ የዘር ግንድ በማዕጸንዋ ያዘች
የምጥ ጊዜዋ ሲደርስ የምውለጃዋ ሰዓት
በጊዜው በሰዓቱ በምትወልድበት ዕለት
ተረጋገጠላት መንታ ልጅ እንዳላት
አዋላጅዋ ደግሞ በምታዋልድበት ጊዜያት
ቀድሞ እጁን ላወጣው ፈትል አሰረችለት
እጁን ወደማዕጸን ወደውስጥ ሲመልስ
ሌላኛው በፍጥነት ለመወለድ ሲደርስ
የማዕጸን በሩ ቢሆንም ጠባብ
ዛራሕ ደግሞ እጁን ወደውስጥ ሲስብ
ፋሬስ ግን ለመውጣት ጊዜውን አልፈጀም
ሊወለድም ደግሞ ፋሪስ አልቸኮለም
ጊዜና አጋጣሚ ሁሉም ሲገጣጠም
በነገሩ ተገርማ ጥሰህ ውጣ አለች
በስም አሰያየም ፋሪስ ብላ ጠራች
በቸር ይግጠመን!!
ኃይሉ ነኝ!