ከየትኛው ወገን ነሽ?
ዓለም ካፈራቸው ድንቃ ድንቅ
ሴቶች
በሁለት ይመደባሉ በትላልቅ ክፍሎች
ጀግና በጣም ጀግና የወንጌል አርበኞች
መብራትዋ ጠፍቶባት ዝም ብላ የተኛች
አንቺ ከየትኛው ነሽ ምድብሽ የቱ ነው
በጌታ ውስጥ ያለሽ እስከምን ድረስ ነው
ቃሉ እንደሚለው እንደሚናገረው
ሁለት ዓይነት አሉ መብራታቸውን ይዘው
ጌታን ሚጠብቁ ቀን ከሌሊት ተግተው
ወይም የሚገኙ እንቅልፍ አንቀላፍተው
መብራታቸውን ይዘው ጌታን ሚጠብቁ
ወይም በሥራቸው ከእውነት የራቁ
ብልህ የሆኑ ሴቶች ሞራለ ጠንካራ
ድል የተጎናጸፉ ሲመጣ መከራ
አሸንፈው ወጡ ከእግዚኣብሔር ጋራ
ሩትና ዖርፋን የኖአሚን መራቶች
በአንድነት የኖሩ ለብዙ ዓመታቶች
ኖአሚን ሞተባት ባልና ልጆችዋ
በጣሙን ተከዘች በረታ ሀዘንዋ
በነዚህ ምክንያት ሀዘን ስለገባት
ስለተደረበባት መጥፎው ብቸኝነት
ወደጥንት መኖሪያዋ ልትሄድ ፈለገች
ለሁለቱም መራቶች መርዶውን ነገረች
ሩትና ዖርፋን ሁለቱም ተነሱ
ወደምትሄድበት ወደዚያ ሊደርሱ
ነገሩን በሙሉ በግልጽ እያስረዳች
ኖአሚን እንዲህ አለች
ከእንግዲህ በኋላ ባል ለእናንተ የለኝም
እኔ አርጅቼለሁ መውለድም አልችልም
ብትከተሉኝም ምንም አታገኙም
ዛሬ እንኳን ብወልድም
ለእናንተ አላደርስም
ስለዚህ ለእናንተ ምድራችሁ ይሻላል
ለኑሮአችሁም ቢሆን እዚህ ይመረጣል
እኔ በራሴነት ምን እጠቅማችኋለሁ
እናንተ እዚህ ቆዩ እኔ አገሬ እሄዳለሁ
አንገትዋን ደፍታ በጣም እያዘነች
ሩት እንዲህ አለች
ለምን ትገፊናለሽ ከአንቺ ጋር እንዳንሄድ
አብረን እንዳልኖርንን እንዳልሆንን ዘመድ
አንቺ እናታችን ነሽ እግዚኣብሔር የሰጠን
በባላችን ቢሆን አንድ አካል የሆንን
በምትሄጅበት ከአንቺ ጋር እሄዳለሁ
አምላክሽ አምላኬ እኔ አደርገዋለሁ
ሕዝብሽም ሕዝቤ ነው ተቀብዬዋለሁ
ይህንን ውሳኔዬን ለአንቺ እገልጻለሁ
እንዳታስቸግሪኝ እለምንሻለሁ
በቁርጥ ውሳኔዋ ጌታ እርሷን አስቧት
ከባርኮቱ በላይ ቦኤዝን አጋባት
አሕዛብ ስትሆን ኢዮቤድን ሰጣት
ከጌታ ኢየሱስ ዘር አንዱ አደረጋት
መከራ ሲመጣ ሞትን ሳይፈሩ
ፈተናውን ለማለፍ የተገዳደሩ
ከእነዚህ አንደኛዋ መጽሐፈ አስቴር ነች
ለእስራኤላውያን ብላ ሞትን ያሸነፈች
በመርደክዮስ ድርጊት ነገሩን ሲያስበው
ሃማ ተናደደ ለካስ ይሁዳ ነው
ታጠቀ ወገቡን ይሁዳን ሊያጠፋ
አዋጅ አዋጅ አለ በጣም የሚያስከፋ
አዋጁን የሰማው ይሁዳዊ መርደክዮስ
መልእክት ላከባት ለዚህ ሕዝብ እንድትደርስ
አንቺ በንጉሥ ቤት በሰላም ስላለሽ
ከሌላው ይሁዳዊ ቢመስልሽ የተሻልሽ
አንቺ ጋ መድረሱን ይህንን ተረድተሽ
አዋጁን ለማፍረስ ታገዬ ተነስተሽ
እንደዚህ ባለሰዓት ብትቆይ ዝም ብለሽ
እኛ እንድናለን አንቺ ትሞቻለሽ
በአሁኑ ሰዓት አንቺ ንግሥት የሆንሽው
ይህን የእግዚኣብሔር ሕዝብ እንድትታደጊው
ከወጣበት አዋጅ እንድታድኜው ነው
መልእክቱን ስትሰማ አስቴር ደነገጠች
አሸንፈዋለሁ ጸልዩልኝ አለች
ከፆመች በኋላ በሶስተኛው ዕለት
ቀረበች በድፍረት ንጉሱ ዙፋን ፊት
የሚያስፈልገውን ለንጉስ ነገረች
ጠላቷን ድል መታች ሞገስ ስላገኘች
እንደ አስቴር ያሉ ቆርጥ እመቤቶች
በዓለም ተፈጥረዋል የእምነት ጀግናዎች
የእስራኤል ልጆች የእግዚኣብሔር ምርጦች
በጌታ አምላክ ፊት ቢሰሩ በደሎች
በከንዓን ንጉሥ በአሶር በነገሰው
በኢያቢስ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው
የሰራዊቱ አለቃ በአርሶት የተቀመጠው
ጨካኙ ሲሠራ አለቃው እርሱ ነው
ከስቃዩ በላይ ግፍ ስለበዛባቸው
ወደ እግዚኣብሔር ጮኹ አነቡ እንባቸው
ትፈርድ የነበረው ዲቦራ ተነስታ
የትንቢቱን ቃል ከእግዚኣብሔር ሰምታ
የኢቢኒኤምን ልጅ ባራቅን አስጠርታ
በጥብቅ ነገረችው ሲሠራን እንዲመታ
ዛሬ ድል ያንተ ነው ከጎንህ ነው ጌታ
ሲሠራ ሲሸነፍ መፈርጠጥ ጀመረ
በሁለት ቤቶች ሰላም ስለነበረ
ወደ ኢያኤል ድንኳን በፍጥነት በረረ
ኢያኤል ስታየው ቶሎ ግባ አለችው
ማንም እንዳያውቀው ፊቱን ሸፈነችው
ውኃ ጠማኝ ሲላት ወተት አጋተችው
ደክሞት ስለነበር መኝታ ሰጠችው
የድንኳን ካስማ ከድንኳን ነቀለች
መዶሻውን ደግሞ በሌላው እጅዋ ያዘች
ቀስ ብላ በዝግታ ወደ እርሱ ቀረበች
እንቅልፍ እንደያዘው በደንብ አስተዋለች
በጆሮግንዱ ላይ ካስማን ቸነከረች
እንደዚህችም ያሉ የእግዚኣብሔር ሴቶች
ለያዙት ዓላማ ሞራለ ጠንካሮች
ተፈጥረው አልፈዋል ጀግና እመቤቶች
ከየትኛው ወገን ነሽ ልጠይቅሽ እቱ
ደረጃሽ ምንድን ነው ያለሽ በእምነቱ
ጀግና ነሽ የጀግና ሚስት ልክ እንደዲቦራ
እግዚኣብሔር ሲናገር ለእግዜር የምትሰራ
በምትሰራው ሥራ ጌታን የምትፈራ
ለአምላካችን ሥራ ሞራለ ጠንካራ
ወደዚህ ስንመጣ ወደ አዲሱ ስርዓት
ዮሐና ሶስና ማርያም መግደላዊት
የሄርዶስ አዛዥ እርሷ የኩዛ ሚስት
በገንዘብ በጉልበት ሲያገለግሉት
በቃኝን ሳያውቁ ሞራል እየሰጡት
ከእርሱ ጋር ተጉዘው ኢየሱስን ረዱት
ሁሉም ሴቶች ናቸው ከእርሱ ጋር የቆዩት
ጰርስቅላና አቂላ ወንጌልን ነገሩት
አጵሎስ እንዲያውቅ መንገዱን አሳዩት
እቱ የእኛይቱ ከየትኛው ወገን ነሽ
መብራት ከጠፋበት ወይ እያበራሽ ያለሽ?
በቸር ይግጠመን!!
ኃይሉ ነኝ
No comments:
Post a Comment