Tuesday, January 14, 2014

Jesus save from death.


Friday, April 26, 2013

ወደ ግባችን ለመድረስ


                 ወደ ግባችን ለመድረስ
እያንዳንዳችን እግዚኣብሔር ሲጠራን ከዓላማና  ከግብ ጋር ነው ። እያንዳንዳችን የምንደርስበት ግብ አለን ፤ ዓላማውን እግዚኣብሔር ይሰጠናል ለዚሁም እግዚኣብሔር ከመወለዳችን በፊት ጀምሮ ያውቀናል ፤ ከተወለድንም በኋላ መድረሻችን ፤ ግባችንን ያውቀዋል ። ያንን ደግሞ ልንደርስበት ፤ ልናገለግልበት ፤ ልንወርሰው ግድ ነው ። ማንም ሰው የእኔ ግብ የተጠራሁት ክርስቲያን መሆን ብቻ ነው ብንል ተሳስተናል ። እግዚኣብሔር ሲጠራን ለከፍተኛ ግብ ነው እርሱን መታዘዝና ማገልገል ። በኦሪት ዘፍጥረት ከምዕራፍ 12 ጀምሮ እንደምናነበው እግዚኣብሔር ለአባታችን ለአብርሃም አንድ ግብ መዳረሻ ሰጠው ። ከአገርህ ከወገንህና ከአባትህ ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ ብሎ ነገረው ። አብርሃም ይህንን ራዕይ ከእግዚኣብሔር ሲቀበል ትርፌ ምንድነው ብሎ ጠይቆ ይሆን ? !! እግዚኣብሔር ግን አንድ ተስፋ ገባለት እኔ ወደማሳይህ ምድር ስትወጣ ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ ፤ እባርክህማለሁ ነው ያለው እዚህ ላይ እንመልከት አብርሃም ወደሚፈልገው አቅጣጫ አይደለም የሚወጣው ለመባረክ እግዚኣብሔር ወደሚፈልገው አቅጣጫ ብቻ ነበር መውጣት የነበረበት እግዚኣብሔር ወደአሳየው ምድር መውጣቱ ግቡ ወይም መዳረሻው የብዙዎች አባት መሆን ነበር ። መባረክ ነበር ። አብርሃም ምንም ልጅ ሳይኖረው የብዙዎች አባት ለመሆን ከአባቱና ከወገኖቹ ተለይቶ ወጣ ። የተስፋው ቃል ይፈጸም ዘንድ ለሃያ አምስት ዓመት ያህል ጠበቀ ፤ እግዚኣብሔርም  እንደተስፋ ቃሉ ፈጸመ ። ክርስቲያን ወንድሜ የሰጠህ ግብ ወይም መዳረሻ አለህ ያም እግዚኣብሔርን ልታገለግል የምትችልበት ራዕይ ተሰጥቶአል ። ያ ልታገለግልበት የተሰጠህ ስጦታ ምንድነው? ያለ ፍሬ ዝም ብለህ እንዳትቀመጥ እግዚኣብሔርን በጸሎት መጠየቅ ያስፈልግሃል ። በነገራችን ላይ ሕልም ከእግዚኣብሔር ሲሆን የወደፊቱን ግባችንን የምናይበት መንገድ ነው ሕልም ከስጋና ከድካም ካልሆነ የግባችን አመልካች ሊሆን ይችላል፤ ሕልም ከእግዚኣብሔር ሲሆን በተደጋጋሚ ልታየው ትችላለህ ያየህውን ሕልም አትረሳውም እግዚኣብሔር የወደፊቱን ግብ ከገለጠባቸው መንገዶች አንዱ ሕልም ነው ። ከእግዚኣብሔር ቃል ስለዮሴፍ የሕይወት ታሪክ በምናነብበት ጊዜ ፤ ከዕለታት በአንደኛው ዕለት ሕልም አለመ ። ወይም በሌላ አባባል በእንቅልፍ ልቡ ራዕይ ተመለከተ ። ያንን ያየውን ሕልም ወንድሞቹ ሁሉ በተሰበሰቡበት ሥፍራ እንዲህ ብሎ ነገራቸው ። በአንድነት በጋራ ሆነን በትልቅ ማሳ ውስጥ ነዶ እያሰርን ነበር ። የእኔ ነዶ በድንገት ቀጥ ብላ ቆመች ፤ የእናንተ ነዶ ደግሞ በአንድነት ለእኔ ነዶ ሰገዱላት ብሎ ነገራቸው ። ዮሴፍ ሕልሙን ሲነግራቸው ትርጉሙ የገባቸው ትላልቅ ወንድሞቹ ፤ እኛ እያለን ለአንተ ልንሰግድ ፤ አንተ በእኛ ላይ ልትነግስ በፍጹም አይደረግም በማለት ሊጠይቃቸው በመጣ ጊዜ ጉድጓድ ውስጥ ከተቱት ፤ ቆይተው እስማኤላውያን ነጋዴዎች በመንገዱ ሲያልፉ በተመለከቱ ጊዜ ጉድጓድ ብንከተው ምንም አይረባንም ትርፍም የለውም ስለዚህ ንጉሥ ነኝ ብሎ ላለመው፣ ባሪያ ሆኖ እንዲኖር በእኛ ላይም ገዥ እንዳይሆን ከዓይናችን ይጥፋ ብለው ወደግብፅ እንዲወስዱት ለእስማኤላውያን ሸጡት ። የዮሴፍ ወንድሞች እግዚኣብሔር ወደሰጠው ራዕይ ለማድረስ በመሸጥ ገፉት ። አንዳንድ ጊዜ ሳታስቡትና ሳትገምቱትእግዚኣብሔር ወደ ሰጣችሁ ራዕይ  የአካባቢው ሁኔታ ወደግባችሁ ሊያመራችሁ ይችላል ። ያኔ ማስተዋል ያለብን አገልግሎቱን ከመጀመራችሁ በፊት በጌታ ፊት በጸሎት መጠየቁ መልካም ነው። እግዚኣብሔር መልካም ነውና ትክክለኛ መሆኑን ይገልጽልናል ። እግዚኣብሔር የሰጣችሁ ግብ አለ ልታገለግሉበት የሚገባ ያ ምንድነው ? ጸልያችሁ አግኝታችሁታል ? እግዚኣብሔር ለቤተክርስቲያን የተለያዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ሰጥቶአል ። ለአንተም ልታገለግልበት የሚገባህ ስጦታ አለህ ፤ ለእኔም ፤ ለአንቺም ፤ ለእነርሱም ፤ ለሁላችንም የተለያየ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ተሰጥቶናል  ታዲያ የተሰጠህ ስጦታ ምንድነው ? በዚያ የማገልገል ግዴታ አለብህ ። ዝም ብሎ ያለ ፍሬ ክርስቲያን መሆን ይቻላል? ። ጌታ ኢየሱስ በዮሐንስ ወንጌል 15 ፥ 16 (እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም ፤ እንድትሄዱና ፍሬ ልታፈሩ ፍሬያችሁም እንዲኖር) ይላል ዝም ብሎ ያለ ፍሬ ክርስቲያን መሆን አይቻልም ምክንያቱም ጌታ ኢየሱስ በቃሉ እንደሚናገረው እኔ የመረጥኋችሁ ፍሬ ልታፈሩ ነው ይላል የተመረጥነው ፍሬ ልናፈራ ነው ። ፍሬ የምናፈራው እንዴት ነው? ፍሬ ልናፈራ፣ ወደግባችን ልንደርስ የምንችለው እግዚኣብሔር በሰጠን ራዕይ ብቻ ነው ። በሮሜ 12 ፥ 13(እንደተሰጠን ጸጋ የተለያዩ ስጦታዎች አሉን …ትንቢት መናገር ፤ ማገልገል ፤ ማስተማር ፤ መምከር ፤ መለገስ ፤ ማስተዳደር ፤ ምሕረት ማድረግ ….እግዚኣብሔር ከሰጠን ራዕይ ውጪ ለማገልገል ብንነሳ ለምሳሌ ስጦታህ ማስተዳደር ሆኖ በማስተማር አገልግሎት አገለግላለው ብትል ፍሬ ላታፈራ ትችላለህ እንዲያውም መንገዱ ሸካራ ሊሆን ይችላል ።ወደግብህ መዳረሻ አገልግሎት ስትጀምር ፤ እግዚኣሔር በበረከት ይሞላሃል ። አገልግሎቱም የተቃና ይሆናል ። ዛሬ በሮሜ 12 ፥ 13 (ችግረኛ ለሆኑ ቅዱሳን ካላችሁአካፍሉ ፤ እንግዶችን ተቀበሉ) የሚለውን ነጥብ እናያለን ። ችግረኛ መርዳት፤ እንግዶችን መቀበል ። አገልግሎቶች ሁሉ በእግዚኣብሔር ፊት ሁሉም እኩል ቢሆኑም እነዚህ ሁለቱ አገልግሎቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከፍተኛ ጥንካሬንና ትዕግስት የሚያሻቸው ሰማያዊ ስጦታ ናቸው ። ይህንን ጥቅስ በምመለከትበት ጊዜ ፣ ሁልጊዜም ትዝ የሚሉኝ ማዘር ትሬዛ ናቸው ።  ማዘር ትሬዛ በኦገስት 26/1910 በአልባኒያ ተወለዱ ።  ማዘር ትሬዛ በትውልድ አልባንያዊ ፤ በእምነት የሮማን ካቶሊክ መነኩሲት ፤ በዜግነት የሕንድ ዜጋ የነበሩ ናቸው ። በ1919 አባታቸው በአልባንያ ፖለቲካ ውስጥ በመካፈላቸው ። ከፖለቲካው ስብስባ በኋላ በጣም ታመው ስለሞቱ እናታቸው ለሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን አበረክቱአቸው ። ማዘር ትሬዛ አስራ ሁለት ዓመት ሲሆናቸው ከልባቸው ጋር ተማክረው በሃይማኖት ፣ በእምነት ሥር ለመኖር ወሰኑ በ18 ዓመታቸው መነኩሲት ሆነው ለመኖር እንደሚሽነሪ ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጋር ተቀላቀሉ ። ማዘር ትሬዛ ለቤተክርስቲያን የተሰጡበትን በተግባር ለመፈጸም መነኩሲት ሆኑ ። በ1929 ሕንድ ሄማልያ ተራራ አካባቢ በአስተማሪነት ለማገልገል ሄዱ ። በአስተማሪነታቸው በጣም ቢደሰቱም ። በ1943 ዓም በካልካታ አካባቢ ረሃብ፤ ችግርና ሞት ፤ በኦገስት 1946 የሂንዱ/ ሙስሊም ከተማውን ማጥፋትና አስቸጋሪ ወረራ በመመልከታቸው ሀዘን በውስጣቸው ገባ ። እነዚህ የተጠቀሱት ሁኔታዎች እግዚኣብሔር ወደሰጣቸው ግብ አመራቸው ። የሕንድን ሕዝብ ለመርዳት ተነሱ፤ በመጀመሪያ በትንሹ ሰዎችን መርዳት ፤ ስለሰዎች ማዘን ፤ የታመሙትን መጎብኘት ነበር ። እንደዚህ ያለውን የተቀደሰ ሥራ በማሳደግ (Missionaries of charity ) የሚባለውን የበጎ አድራጎት ድርጅት አቋቁመው ፤ ለአርባ አምስት ዓመታት አገልግለው መርተዋል ። የበጎ አድራጎቱ ዋና ዓላማ ድሆችን መደገፍ ፤ እናትና አባት የሌላቸውን ማሳደግ ፤ በሞት ለሚቀሰፉት አደጋው ከመስፋቱ በፊት ደርሶ መርዳት ነበር ። ይህ ድርጅት በመጀመሪያ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው ለሕንድ ሕዝብ ብቻ ነበር ነገር ግን የእንደዚህ ዓይነቱ ችግር በዓለም ዙሪያ ስለሆነ ራዕያቸውን በማስፍት በ610 ጣቢያና በ123 አገሮች በጎ አድራጎቱ ተስፋፋ ፤ ይህንን በጎ አድራጎት ድርጅት የሚረዱትና ከጎናቸው የተሰለፉ 4000 መነኮሳት (sisters) ፣ 300 መነኩሴዎች (Brothers ) አባላት ሲሆኑ ፤ ከ100,000 በላይ ፈቃደኛ አገልጋዮች አሉት ። ማንኛውም ሰማያዊ ስጥታ ከእግዚኣብሔር ሲሆን ወደግባችን የምንደርስበት ጎዳና የሰመረ ይሆናል ከላይ እንዳነበብነው ማዘር ትሬዛ ደስ ያላቸውን የአስተማሪነት ሥራ ቢቀጥሉ ይህን ያህል ለዓለም የተረፈ ፍሬ ሳያፈሩ የመንደር አስተማሪ ሆነው በቀሩ ነበር ። በሕንድ አገር በተከሰተው ችግር ምክንያት ወደግባቸው ስለመራቸው  አገልግሎታቸው የሰመረ ሆኖአል ። ተመልከቱ ዓለም ሊያከብራቸውና አገልግሎታቸውን ሊደግፍ የቻለው እግዚኣብሔር ወደ ሰጣቸው ግብ በመጓዛቸው ነው። ማዘር ትሬዛ እግዚኣብሔር የሰጣቸውን ራዕይ ፈጽመው በ1997 በሰማንያ ሰባተኛው ዓመታቸው አርፈዋል ።
        ሌላው በእግዚኣብሔር ቃል ተገልጾ የምናየው  ደግሞ  እንግዶችን መቀበል የሚለው ሰማያዊ ስጦታ ነው ። እንግዶችን የመቀበል አገልግሎት ራዕይ የሚሰራው ከፍቅር ጋር ነው ። ፍቅር ካልተጨመረበት አገልግሎቱ ከበድ ያለ ነው ታዲያ እግዚኣብሔር እንግዶችን የመቀበል አግልግሎት ሸክም አድርጎ የስጠው ሰው ምነኛ የተባረክ ነው ። በአገልግሎቱ የሚቀበለው በረከት ሰፊ ነው ። እንግዶችን በሚቀበልበት ጊዜ እግዚኣብሔር ያላሰበው በረከት ይሰጠዋል ። ከእግዚኣብሔር ቃል በ2 ነገሥት 4 ፥ 10 ላይ ስለምትገኘው ሱናማዊት ሴት እንመልከት ፤ የእግዚኣብሔር ቃል ከዕለታት በአንደኛው ቀን ኤልሳ ወደሱናማ ሄደ ይላል ። በሱናማ የምትኖር አንዲት ሀብታም ነበረች ። ስለዚህ ኤልሳን ባገኘችው ጊዜ ቤቷ ገብቶ ምግብ እንዲመገብ አጥብቃ ጠየቀችው ። እንግዳ ነህና ማረፊያም የለህምና ቤቴ ገብተህ እረፍና ምግብ ተመገብ ብላ አለችው ። ይህንን ምዕራፍ ስንመለከት እንግዶችን በዘልማድ ሳይሆን በፍቅር መቀበል እንዳለብን ፤ የሀብታሟ ሴትይዋ ሁኔታ ያሳየናል ። አጥብቃ የጠየቀችው በእርግጠኛነት የእግዚኣብሔር ሰው መሆኑን ተቀብላ ነው ። የእንግዳ መቀበል  ራዕይ ያለን ሰዎች በምናደርገው አገልግሎት ከእንግዳችን ትርፍ ለማግኘት ሳይሆን እግዚኣብሔር እንደሚባርከን አምነን ነው ልናገለግል የሚገባን ። ምክንያቱም ተዘጋጅተን የምንጠብቀው እንግዳችን በሰው ሰውነቱ ብቻ አይተን የምንቀበለው ከሆነ በብዙ ከስረናል ። ከእግዚኣብሔር ካልተሰጠን ባናገለግል ይሻለናል ። የዚህ አገልግሎት  ራዕይ አለን ካልን ልናውቀው የሚገባን ነገር ያ ሰው ፣ በሰው አምሳል መጣ እንጂ በእንግድነት ሲመጣ እግዚኣብሔር ልኮት ፤ የእግዚኣብሔርን ሥራ ሊሰራ እንደሚመጣ አውቀን ልንረዳ ይገባናል ። እንደአባቶቻችን ባህልና አባባል እንግዳ እግዚኣብሔር ነው ይሉ ነበር  ። ዛሬስ ጌታ ኢየሱስን አዳኛችን ብለን ተቀብለን ራዕዩ እያለን በበለጠ ልንቀበለው ይገባል ። በዚህ መንፈስ ተረድተን ከአገለገልን እግዚኣብሔር በብዙ በረከት ይባርከናል ።ይህንን አገልግሎት ሳይሰለቹ የሚያገለግሉትን ከፍተኛ አድናቆት አለኝ ። ዕብ 13 ፥ 2 (እንግዶችን መቀበል አትርሱ አንዳንዶች ሲያደርጉ ሳያውቁ መላእክትን አስተናግደዋልና ) እንግዳ መቀበል ፀጋው የተሰጠን እንግዳ መቀብሉን በፍቅር እንድናደርገው  ቸል እንዳንል ቃሉ ይነግግረናል ። ምክንያቱም እንግዳ መቀበል ልምድ ያላቸው ሰዎች ሳያውቁት መላእክትን ተቀብለዋል ። ዛሬስ መላእክት በእንግድነት አይመጣም ብለን እንጠራጠር ይሆን ? በምንም ዓይነት አንጠራጠር መላእክት በእንግድነት ሊመጡ ይችላሉ ። ከሁሉም በላይ እንግዳን መቀበል ፣ ማስተናገድ በረከት አለው ። በኦሪት ዘፍጥረት 18 ላይ አብርሃም በድንኳኑ ውስጥ ሳለ አሻግሮ ሲመለከት ሶስት እንግዶችን ተመለከተ ይላል ። አብርሃም በእንግድነት ሊቀበላቸው የወጣው ሥጋ ለባሽ ሰው መስለውት ነበር ።  እንዳሰበው አልነበረም በገሃዱ ዓለም ወደ እርሱ የመጡት ሥጋ የለበሱ ሰዎች ቢሆኑም በአብርሃም ቤት በእንግድነት የተገኙት ግን ሳራ የዛሬ ዓመት በዚህን ጊዜ ወንድ ልጅ ትወልዳለች ብለው በረከት  ሰጥተው ሊሄዱ ጎራ ያሉት ሶስት ስላሴዎች ነበሩ ። እንግዳችን የምንቀበለው ለይምሰል ሳይሆን በፍቅር ከሆነ እንዳደርግነው መጠን በብዙ ፀጋውን  ያትረፈርፍልናል ። ሱናማዊት ሀብታም ሴት ለባላዋ ይህ አዘውትሮ በደጃችን የሚያልፈው ቅዱስ የእግዚኣብሔር ሰው መሆኑን አውቃለሁ ። ስለዚህ በሰገነት ላይ አንዲት ትንሽ ክፍል ቤት ሰርተን አልጋና ጠረጴዛ ወንበርና ፋኖስ እናስገባለን ከዚያም ወደእኛ በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ ማረፊያ ትሆነዋለች አለችው ። ኤልሳ ከሚኖርበት መንደር ወደሱነማ በሚወርድበት ጊዜ የእግዚኣብሔር ሰው እንዳይንከራተት ከእውነተኛ መንፈስ ተነስታ በፍቅር የሚያርፍበትን ክፍልና በውስጡ የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ አዘጋጅታ ሁል ጊዜ በዚያ ሰገነት አንዲያርፍ አደረገችው ። ምን ዓይነት ልብ ነው ያላት ለእግዚኣብሔር ሥራ የተነሳሳ የምትደርስበትን ግብ የገመተች ነች ። ሁሉም ነገር የተሳካ ስለሆነ በሱነማ የኤልሳ አግልግሎት የተሳካ ሆነ ። እግዚኣብሔር ደግሞ የእርሱን ሥራ ስትሰራ እግዚኣብሔር ደግሞ የእርሷን ሥራ ሰራ በሚያስፈልገው ሁሉ ባረካት ። እግዚኣብሔር በሰጣችሁ ራዕይ በአገልግሎታችሁ ሳታሰልሱ ብታገለግሉት ፍሬው ሰማያዊ ብቻ ሳይሆን ምድራዊ በረከት ጭምር ነው ። በኢዮብ መጽሐፍ 31 ፥ 32 ላይ (ነገር ግን ቤቴ ለመንገደኛው ዘውትር ክፍት ስለነበረ መፃተኛው በጎዳና ላይ አያድርም ነበር ) ምናልባት ሰይጣን ይህንን አይቶ ይሆን ኢዮብን በእግዚኣብሔር ፊት የከሰሰው ። ስለመልካም ተግባሩ በኢዮብ ላይ ችግር ቢደርስበት እንኳን እግዚኣብሔር ስለ መልካም ሥራዎቹ ሲል በሰማይ ሳይሆን በምድር  እጥፍ ድርብ አድርጎ  ባረከው ። እግዚኣብሔር ስለምታደርጉት መልካም ነገር ሲል ይባርካችኋል  በሁለቱም አገልግሎት የምትሳተፉትን ለእግዚኣብሔር ስትሉ ስለሆነ የምታገለግሉት ጌታ ራዕያችሁን ያብዛላችሁ ይባርካችሁ እላለሁ
                                      ጌታ ይባርካችሁ!!
                                           ኃይሉ ነኝ!!!


የትውልድ አደራ


                  የትውልድ አደራ
ለአገራችን ወንጌልን ለማድረስ የውጪ አገር ሰዎች የእግዚኣብሔርን ምሪት በመቀበል፣ ረጅሙን መንገድ በባሕርና በየብስ በማቆራረጥ በሚስዮን ድርጅት አማካይነት የጌታ ኢየሱስን ወደ ዓለም ሁሉ ሄዱ የሚለውን የወንጌልን ትህዛዝ ለመፈጸም በአንድ እጃቸው ስጦታ ማለትም የሕክምና መሳሪያዎችና የትምህርት ቤት ማቴሪያሎችን፤ በሌላ እጃቸው መጽሐፍ ቅዱስ የመዳን ወንጌል ይዘው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለማድረስ ከኢጣልያ ወረራ በፊት ጀምሮ በኢትዮጵያ ምድር በተለያየ ጠቅላይ ግዛት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ከኢጣሊያ ወረራ በፊትና በኋላ የትራንስፖርት መገናኛ በሌለበት ገጠር በእግርና በበቅሎ ጀርባ እየሄዱ፣ የሕዝቡን ኑሮ እየኖሩ፣ በሽታውን እየታመሙ፤ ክሊንክና ቤተክርስቲያን በአንድ በኩል የሕክምናና የትምህርት አገልግሎት በሌላ በኩል የሕይወታቸውን አዳኝ የሆነውን ጌታ ኢየሱስን ያስተምሩአቸው ነበር። በተለይም ከጠላት ወረራ በኋላ በተለያየ ዕውቀት የተመረቁ የጌታ ወገኖች ምቾታቸውን በመተው በሚስዮናዊነት ዕውቀታቸውንና ልምዳቸውን ለመስጠት በሙያ ዘርፋቸው ተሰማርተው ዶክተሮችና ነርሶች ሆስፒታሎችና ክሊንኮችን አቋቁመው በመስራት፤ የተግባረ ዕድ ባለሙያዎች በግንባታ መስክ በመሰማራት ትምህርት ቤቶችን፤ ለተቸገሩ ቤቶችንና የምንጭ ውሃ በመጥለፍ ንጹሕ ውሃ ለሕዝቡ እንዲደርስ ያደርጉ ነበር። የትምህርት ባለሙያዎች ደግሞ መንግስት እስከፈቀደላቸው ደረጃ ድረስ የቀለምና የሙያ ትምህርት ሕዝቡ እንዲማር አድርገዋል። በንጉሡ ዘመን በትምህርት፤ በሙያ፤ በጤና ዘርፍ ሲያገለግሉ የነበሩት የፊላንድ ሚስዮን፤ ሱዳን ኢንተርየር ሚሽን፤ ሚኖናይት ሚሽን፤ ኒዌሪጂያን ሚሽን፤ ሉተራን ሚሽን ሲሆኑ፤ እስከደርግ መንግሥት መቋቋም ድረስ ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ከዚያ በኋላ የሕዝብ ንብረት ሆነዋል በሚል ትህዛዝ ሲወረሱ አገልግሎታቸው 99% ተቋረጠ። ብዙዎቹ ተፅህኖ ስለበዛባቸው ወደተለያየ የአፍሪካ አገሮች ለወንጌል አገልግሎት ተሰማሩ። ከ1983 ዓም በኋላ ወደ ቀድሞ አገልግሎታቸው የተመለሱት የሚስዮን ድርጅቶች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። አሁንም የሕዝቡ ችግር በባሰ ሁኔታ ነው። የኑሮ ውድነት በጣም ከፍ በማለቱ በየዕለቱ ከፍ የሚለውን የዋጋ መናር አልቻለውም፤ በአየር ንብረት ምክንያት በተደጋጋሚ በረሃብ እየተጠቃ ነው። የንጹሕ ውሃ አገልግሎት  ባለመዳረሱ ዛሬም በተቅማጥ በሽታ ይጠቃል። ትምህርት ወደሰፊው ሕዝብ ያልተዳረሰ ስለሆነ የቀለምና የሙያ ትምህርት ቤቶች ያስፈልጉታል። ለእነዚህ ሁሉ ችግር መፍትሔ መስጠት የሚችለው ማነው? ዛሬም ሚስዮናዊያንና የውጪ መንግሥታትን እጅ እንጠብቅን? አይደለም አሁን ደግሞ የትውልድ አደራ በራሱ በአበሻው ሕዝብ ላይ ተጥሎአል። እግዚኣብሔር ከምድራችን አውጥቶ ወደዚህ ምድር ያመጣን እግዚኣብሔር ዓላማ ስላለው ነው። አመጣጣችን ከሁሉም የአገሪቱ ክፍል ስለሆነ የመላው አገሪቱ ችግር የእያንዳንዳችን ችግር ነው። ያንን ሳይማር ያስተማረንን፤ ተርቦ ግብር እየከፈለ ያስተማረንን ሕዝብ ርሀቡን ተርበን፤ ችግሩን ተቸግረን ልንረዳው፤ በሁሉም ነገር ከጎኑ ልንቆም የትውልድ አደራ ግድ ይለናል። ዛሬ ደግሞ ከአበሻው ሕዝብ መካከል እንደዚህ ያለውን እግዚኣብሔር የሰጣቸውን ራዕይ ለማስፈጸም ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል።  እግዚኣብሔር ራዕዩን ስለሰጣቸው ከዚህ ትርፋቸው እግዚኣብሔርንና ሕዝቡን ማገልገል ነው። እንደዚህ ከሆነ እግዚኣብሔር የሰጣቸውን ራዕይ ብንደግፍ በወገናችን ላይ ከሚደርስበት ችግር ድርሻችንን እንቀርፋለን ማለት ነው። ያንን ስናደርግ ደግሞ እግዚኣብሔር ይባርከናል። የትውልድ አደራ አለብንና ወገናችንን እንርዳ!!                           
                                       ጌታ ይባርካችሁ!!

Sunday, April 21, 2013

ርብቃ ደግ ናት


ርብቃ ደግ ናት
አብርሃም አርጅቶ ስለሸመገለ
ለቤቱ ሐላፊ እንደዚህ ብሎ አለ
ከከነዓን ሴቶች ለልጄ አትምረጥ
በእነሱ ቆንጆዎች ልብህ አይናወጥ
የወደድከው ቢኖር ዓይንህ አይቀላውጥ
ቆንጆ ሴት ብታገኝ ከከንዓን አትውሰድ
ከተወለድኩበት ወደዚያ በመሄድ
በዚያ ተመካክረህ ከወገን ከዘመድ
እኔ አምልሃለሁ በስመ እግዚኣብሔር
ይዘህለት አምጣ የምትሆነው ለትዳር
የአብርሃም ሎሌ አስር ግመሎችን
ከእንስሳት መካከል ጥሩ የሆኑትን
ጉትቻ ቀለበት እንዲሁም አምባሩን
ጠቅልሎ ተነሳ ለአማጭ የሚያሻውን
ጉዞውን ቀጥሎ ወንዝ ተራራውን
ሲዳክር ዋለና ዳገት ቁልቁለቱን
ፀሐይዋ ልትጠልቅ ወደማታ ሰዓት
ለይስሐቅ የምትሆን ርብቃን አገኛት
ለብቻው ሆኖ በሚሄድበት ወቅት
የአብርሃም ሎሌ እንደዚህ በማለት
ይጸልይ ጀመረ ወደአምላክ ፀባዖት
በውሃ ምንጭ ዳር እኔ እቆማለሁ
እዚህ ከምትመጣው አንዷን እጠይቃለሁ
አንተ ጠጣ ግመሎችህንም እኔ አጠጣለሁ
የምትለኝ ቆንጆ እርሷን እመርጣለሁ
ጌታ ሆይ አድርገው እለምንሃለሁ
አምላኩን ለምኖ ፀሎቱን ሲያበቃ
ውሃውን ልትቀዳ ስትመጣ ርብቃ
ከተፍ አለችለት ይዛ የውሃ ዕቃ
ጥያቄ ጠየቃት ውሃ እንድታጠጣው
ርብቃ መለሰች ውሃ ነው የምትፈልገው
ለአንተ ይህው ጠጣ ግመሎችህንም አጠጣቸዋለሁ
የምትፈልገውንም እኔ አደረጋለሁ
ማደሪያም ከሌለህ ቤታችን ሰፊ ነው
ያልከኝን በሙሉ እኔ እታዘዛለሁ
ለእግዚኣብሔር እንግዳ ሁሉን እፈጽማልሁ
መልካሙን ለማድረግ ርብቃ ደግ ነች               
ከጥያቄ በላይ ሁሉን ታደርጋለች
እንስራውን ሞልታ ውሃ ታሰጣለች
ከምንጭ ውሃ ቀድታ ግመል ታጠጣለች
ለእግዚኣብሔር እንግዳ ርብቃ ደግ ነች
                  በቸር ይግጠመን!!!
                  ኃይሉ ነኝ! 2006