የጠፋው በግ
እስከ ስምንተኛ ዓመት ባለው ዕድሜዬ ፊደል የቆጠርኩት በየኔታ ቤት ነበር ። ትምህርት ቤቱ የሚገኘው በቤተ ክርስቲያን ወይም በደብር ሥር ሰለነበረ ሳምንቱን በሙሉ ውሎዬ በቤተክርስቲያን ዙሪያ ነበር ። ታዲያ ከቀኖች ሁሉ ለእኔ ደስ የሚለኝ እሁድ ነበር ። ምክንያቱም በዚያን ዕለት ከየት እንደሚመጡ የማላውቃቸው ሁለት ሰዎች ስለ ሕጻናት ትምህርት ካስተማሩ በኋላ ትናንሽ ፎተግራፍ ሥዕል ይሰጡናል እነዚያን ፎተግራፎች ከመውደዴ የተነሳ ሳምንት እሁድ ቶሎ እንዲመጣ እናፍቅ ነበር ። በየሳምንቱ የተለያዩ
ፎተግራፎች ብወስድም አንድ ፎተግራፍ ግን እስከዛሬ ልቤ ተቅርቅሮ ያለ ነው ፤ (የጠፋው በግ) በዚህ ርዕስ የተሳለ ስዕል ሲሆን ሥዕሉ እንደዚህ ነው አንድ እረኛ በግ እንደ ነበረችውና ይህች በግ ጠፍታ በማታውቀው መንገድ ሄዳ፤ ገደል ወድቃ እየተሰቃየች ነው ፤ የበጊቱ እረኛ ደግሞ በጊቱን ከዚያ አዘቅት ለማውጣት ሐረግና ቆንጥር ይዞ እየታገለ ያሳያል በሌላ በኩል ጭልፊት ፣ ጥንብ አንሳ በግዋን ከእረኛው ቀድሞ ለመውሰድ ከገደሉ ስር ያንዣብባል ። ሰዓሊው በጥሩ ሁኔታ ገልጾ ሥሎታል ፣ ድንቅ ስዕልና ሰዓሊ ፣ ሁልጊዜም ይህንን ስዕል ስመለከት ፈጥኖ የሚታሰበኝ ፣ምን ዓይነት ተንኮለኛ በግ ነች ? ለምን እዚህ ገደል ውስጥ ገብታ እረኛውን
ታስቸግራለች እያልኩ ነበር ። ዛሬ ግን ለእኔ ብዙ ለውጥ አለው ስለጠፋው በግ በተለያየ መልኩ በብዙ ቦታ ተፅፎ ይገኛል በኦሪትና በአዲስ ኪዳን ፣ ለዚህ ለተነሳውበት
ሃሳብ ግን የማቴዎስ ወንጌል 18 ፡ 12 ዋና መንደርደሪያዬ
አደርገዋለሁ ። ይህንን ምሳሌ ጌታ ኢየሱስ ያነሳበት ምክንያት በሉቃስ ወንጌል እንደተገለጸው ቀራጮችና ኃጢያተኞች የሚናገረውን ቃል በጽሞና ያዳምጡት ስለነበረ ፣ ፈሪሳውያንና ጻፎች ደግሞ ከኃጢያተኞችና ከቀራጮች ጋር ይበላል በማለት ስላጉረመረሙ ነው ። ጌታ ኢየሱስ ለፈሪሳውያን እንዲህ አላቸው አንድ ሰው መቶ በጎች ቢኖሩትና ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋበት ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋውን ለመፈለግ አይሄድምን? ብሎ ጥያቄ ይጠይቃቸዋል ። Tyndale Bible ሲያብራራው እንደዚህ ይላል (ዘጠና ዘጠኙን ትቶ አንድ በግ ሊፈልግ የሚሄድ እረኛ ሞኝ ይመስላል ፣ ነገር ግን ዘጠና ዘጠኙ በሜዳ ላይ ሲተዋቸው ምንም ችግር እንደሌለባቸውና ማንም እንደማይነካቸው ያውቃል የጠፋችው በግ ግን አደጋ ላይ ነች ምክንያቱም
እያንዳንዱ በግ ከፍተኛ ግምት አላቸው) ትርጉም የእኔ ነው፤ ነገሩን ስንመለከት አንዲቷ በግ ጠፍታለች ፣ቆንጥር ይዟት ይሆናል ወድቃ ተሰብራ ሊሆን ይችላል አስቸጋሪ ገደል ውስጥ ገብታ መውጫ አጥታ እየተሰቃየች ነው ። መልካም እረኛ የጠፋችውን አንዲቱን በግ ፈልጎ ማግኘት አለበት ፣ ሞት እያንዣበባት አደጋ ላይ ያለችውን ፣ አውሬ ሳይበላት በፊት ማግኘት አለበት ፤ ጥንብ አንሳ ፣ ጭልፊት በበረሃ
የተጎዳውን ለማንሳት ስለሚያንዣብቡ ያለምንም ጥርጥር ብቻዋን ሆና ሲያገኙት ሊቀራመቷት ስለሚችሉ ፣ አደጋው ከመድረሱ በፊት በየጫካውና በየወንዙ ባለፈባቸውና ባገደመባቸው ሥፍራ ሁሉ ሊፈልግበት ወደ ሚገባው አስቸጋሪ ቦታ መሄድ አለበት ፣ ስለዚህ እስኪያገኛት ድረስ ይፈልጋታል ። ስለ ጠፋው በግ ምሳሌ ስንመለከት ፣ እግዚኣብሔር ለእያንዳንዱ የሰው ልጅ ፍቅር እንዳለው ያሳየናል ፣ በትንቢተ ኤርሚያስ 50 ፡ 6 ላይ (ሕዝቤ እንደጠፉ በጎች ሆነዋል)ይላል ። እግዚኣብሔር ከማዘኑ የተነሳ፣መንከራተታችንን ተመልክቶ ነው ሕዝቤ ብሎ በማቆላመጥ እንደጠፉ
በጎች ናቸው በማለት በቃሉ የተናገረው ፤ የጠፋ በግ ምን ያህል እንደሚንከራተት በሃሳብ ተመልከቱ ፤ እግዚኣብሔር አዳምንና ሔዋንን ፈጥሮ በመልካም ሥፍራ በገነት ውስጥ እንዲኖሩ አደረጋቸው ፣ በገነት ውስጥ ያለውን ማንኛውንም ነገር መብላት እንደሚችሉ ፣ ነገር ግን መልካሙንና ክፉውን የምታስታውቀውን ዛፍ እንዳይበሉ አዘዛቸው ፣ ኣዳምና ሄዋን ግን የኃጢያት ምንጭ የሆነውን ፍሬ በመብላት ከእግዚኣብሔር ተለዩ ከገነት ተባረሩ የመንፈስ ሞት ሞቱ ከዚያ በኋላ መንከራተት ጀመሩ በቃየል የተጀመረው ውሸት ዓለምን ሁሉ ሞላ ስለዚህ ምድር በእግዚኣብሔር ፊት በክፉ ሥራ ረከሰች በአመጻም ተሞላች በዚህ ምክንያት በዓለም ሁሉ ተበታተነና መንከራተት ጀመረ ። በሕዝቅኤል የትንቢት መጽሐፍ እንደተጻፈው በጎቼ በየተራራው ሁሉና በየኮረብታው ላይ ተንከራተቱ በማለት
ምን ያህል እንዳዘነልን ይገልጸዋል ፣ በጎች ምንጊዜም እረኛቸውን ተከትለው ነው የሚሄዱት ፣ እረኛውን ካልተከተሉ መንገዳቸውን ስተዋል፣ አቅጣጫቸውን ቀይረዋል ፣ በጉድባ ውስጥ ወድቀዋል ፤ እነዚህ መንገዳቸውን የሳቱትን
ወደ መንጋው ለመመለስ ለበጎቹ ግድ የሚለው መልካም እረኛ ያስፈልጋል መልካም እረኛ ለእያንዳንዱ በግ ግድ ይለዋል ፤ እግዚኣብሔር በማቆላመጥ በጎቼ ያለውን ሕዝብ ከዚያ ከመርገምና ከኃጢያት ለማውጣት የግድ አንድ ነገር ያስፈልግ ነበር ። ፈላጊ ፤ እረኛና ፤ ጠባቂ ። በእረኛነት ጉዳዩን ሊያስፈጽሙ ብዙዎች ተላኩ ፣ ለተንከራተተው በግ መፍትሔ ሊሆኑ አልቻሉም ፤ መፍትሔው ደግሞ አንድ ነበር እረኛው እግዚኣብሔር የጠፋውን በግ ከጠፋበትና ከኮበለለበት ወደ መንጋው መመለስ ለዚህ ደግሞ ራሱ እግዚኣብሔር ልጁን ጌታ ኢየሱስን ወደ ምድር ልኮ የጠፋውን በግ መመለስ ፣ ነጻ ማውጣት ፣ በሕይወት እንዲኖር ማድረግ ነበር ዓላማው ፤ ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ለዓለም ተሰጠ ጌታ ኢየሱስ ደግሞ ተልዕኮው ከሌሎቹ የተለየ መሆኑን ለማሳየት መልካም እረኛ እኔ ነኝ ፣ መልካም እረኛ ነፍሱን ስለበጎቹ ይሰጣል በማለት ደሙን አፍስሶ የሰውን ልጅ ሞት ሞቶ ድሉን ከጠላት ላይ ከወሰደ በኋላ የአዳምን ዘር ከሞትና ከኃጢያት ነጻ አውጥቶ በመንፈስ ከመንጋው ጋር ቀላቀለው፤ ከዚህ በኋላ እያንዳንዱ የራሱ ምርጫ አለው ከመንጋው ተለይቶ ወደ ገደልና ቆንጥራማ መሄድ ወይም ከመንጋውና ከእረኛው ጋር መኖር ምንጊዜም ጌታ ኢየሱስ ለሚንከራተቱት ያዝናል፤ በቃሉ (ሕዝቡም እረኛ እንደሌለው በግ ተጨንቀውና ተመልካች የለሽ ሆነው ባየ ጊዜ አዘነላቸው) ይላል አዎ!! ጌታ ኢየሱስ የሌላቸው በዲያብሎስ
እጅ ሆነው ወደ ሞት እየመራቸው ያሉ ስንቶች ናቸው? ከዚህስ በኋላ ወደ ሕይወት እንዲመለሱ የማድረግ ሐላፊነቱ የማነው? እረኛ እንደሌላቸው በጎች ለሚንከራተቱት ማን ፈጥኖ ይድረስላቸው ? ጌታ ኢየሱስ አንድ ትህዛዝ ሰጥቶአል ወደዓለም ሁሉ ሄዱ ለፍጥረት ወንጌልን ተናገሩ፤ የጠፉትን ነፍሳት ከሞት፣ ከሸለቆ፣ ከጠላት ወጥመድ ነፃ ሊያወጣ የሚችል የተላከ ብቻ ነው፣ ተልከሀል? አዎ ተልከናል እኛ የክርስቶስ አምባሳደሮች ነን አምባሳደር ደግሞ ለአገሪቱ ተወካይ ነው እኛም የሰማይ አገር ተወካይ ስለሆንን ስለተውከልንበት ሰማያዊ አገር ወንጌልን ልንናገር፣ ልናስረዳ፣ ልንመልስ የሚገባውን የአምባሳደርነት ሥራ ልንሰራ ሐላፊነት አለብን፣ የአምባሰደርነታችንን ሐላፊነት ባንፈጽም ተጠያቂ ነን፤ በጌታ ኢየሱስ በደሙ የተዋጀ ክርስቲያን የአምባሳደርነት ሥራውን መፈጸም አለበት፣ እረኛ እንደሌላቸው ሲባዝኑ ለሚታዩ ሕዝቦች ወንጌልን ልናደርስላቸው ግዴታችን ነው። ሹመቱን ብቻ ሳይሆን ሥራውንም መስራት አለብን ጳውሎስ እንደተናገረው ወንጌልን ባልናገር ወዮልኝ እንዳለውና እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ቃሉን በአደባባይ እንደመሰከረው እኛም ለጠፉት ነፍሳት ግድ ብሎን ወደ ሕይወት እንዲመለሱ ወንጌሉን እንናገር!!
በቸር
ይግጠመን!!!
ኃይሉ ነኝ!!! 2008